ወንዶች ሆይ ቀኑ ከፍቷልና መቀመጫችሁን ጠብቁ /እውነተኛ ገጠመኝ/ – ዘሐዲስ አየለ አበራ

ወንዶች ሆይ ቀኑ ከፍቷልና መቀመጫችሁን ጠብቁ
/እውነተኛ ገጠመኝ/

ከቦሌ ወደ ሳሪስ በሚወስደዉ መንገድ ላይ ከመሼ ታክሲ እየጠበኩ ነበር፡፡ ስዓቴን ስመለከት ሁለት ሰዓት ተኩል ይላል፡፡ የተከራየሁበት ግቢ በር ሦስት ሰዓት ላይ ተቆልፎ ስለሚዘጋ በሠላሳ ደቂቃ ውስጥ መድረስ አለብኝ፡፡

በጭንቀት በቆምኩበት በዚህ ወቅት የመኪና ክላክስ ከበስተጀርባዬ ሰማሁ፡፡ ዞሬ ስመለከት ሁለመናዋ ጥቁር የሆነች የቤት መኪና ቁማለች፡፡ የባለስልጣን መኪና ትሆናለች ብዬ ትኩረቴን ታክሲ መጠበቄ ላይ አደረኩ፡፡

የመኪናዋ የበር መስታወት ተከፈተና የወጣት ሴት አንገት ብቅ አለ፡፡ ሁኔታዉን በአትኩሮት ስመለከት በእጆቿ ጠራችኝ፡፡ ወደእርሷ ስቀርብ “ከመሼ ታክሲ እየጠበክ ነው?” አለችኝ፡፡ ዘመናዊነት ያሳበዳት በሃያወቹ እድሜ ክልል የምትገኝ ወጣት ናት፡፡ በአዎንታ ራሴን ነቀነኩ፡፡
“የት ነው ሠፈርህ ሊፍት ልስጥህ?” አለችኝ፡፡
ሰዓቴን ተመለከትኩና ሳላቅማማ “እሽ” አልኳት፡፡
“ከኃላ ግባ” ብላ አዘዘችኝ፡፡ አመስግኜ የኃላ በር ከፍቼ ስገባ ወፈር ያለ ወንድ ቁጭ ብሏል፡፡ ጥሩ ስሜት አልተሰማኝም ነገር ግን የመኪናዋን በር ዘጋሁኝ፡፡ መኪናዋ ጉዞ እንደጀመረች በጥርጣሬ አንድ ጊዜ ሴቷን ሌላ ጊዜ ወፍራሙን ሰውዬ ስመለከት “አይዞህ ተጫወት” አለና እጆቹን ጭኔ ላይ አስቀመጠ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ትከሻ እያለ ጭኔ ላይ ምን እጁን ያስቀምጣል? ያነሳል ብዬ ስጠብቅ ይባስ ብሎ ይዳብሰኝ ጀመር፡፡

ምን አይነት ወጥመድ ውስጥ እንደገባሁ ዘግይቼም ቢሆን ተረዳሁኝ፡፡ አሁን የማምለጫ ዜዴ መፈለግ አለብኝ አለዚያ በሌሎች ላይ የሰማሁት ታሪክ በራሴ ላይ ሲፈጸም ማየቴ ነው፡፡

ወፍራሙ ሰውዬ አሁን መደባበሱን ቀጥሎ ሊያቅፈኝ ይታገላል፡፡ ይቺ አዲስ አበባ እውነትም ተበላሽታለች፡፡ በአንድ በኩል እንዳይዘኝ እያታገልኩ በሌላ በኩል በምን መልኩ ከዚህ ወጥመድ ማምለጥ እንዳለብኝ እያሰላሰልኩ ሳለ ወፍራሙ ሰውዬ “በላይኛው መስመር ንጂውና ቶሎ እናምልጥ” ሲል ወጣቷን አዘዛት፡፡

ነገሩ የጠነከረ እንደሆነ ሲገባኝ ጌታ ከዚህ አሳዛኝ መከራ እንዲያወጣኝ በውስጤ ፀሎት አይሉት ቁጣ አልጎመጎምኩ፡፡ በዚህ ቅጽበት ነበር የቅንጅት ምልክት ትዝ ያለኝ፡፡ በፍጥነት ሁለቱን ጣቶቼን ወደጉሮሮዬ ሰደድኳቸዉ፡፡ ከሰኮንዶች በኃላ መክሰስ የበላሁትን ፓስታና ዳቦ ከሚታገለኝ ወፍራሙ ሰውዬ ላይ ዘረገፍኩት፡፡

ወፍራሙ ሰውዬ “መኪናውን አቁሚዉ” ሲል ጩኸቱን ለቀቀው፡፡ ነገሩ ያልገባት ወጣቷ መኪናውን በፍጥነት አቆመችው፡፡ በዚች ቅጽበት የመለቀቅ እድል ስላገኘሁ የመኪናዋን በር ከፍቼ ተፈተለኩ፡፡ ከኃላዬ የተከተለኝ ባይኖርም የልቤ ምት ቀጥ እስኪል ድረስ በደመነፍስ ሮጥኩኝ፡፡

አሁን የግቢያችን በር ስለተቆለፈ ጓደኛዬ ቤት ነኝ፡፡ ከዚህ ጉድ ያወጣኝ ፈጣሪ ምስጋና ይግባው፡፡ እናም ወንዶች ሆይ ቀኑ ከፍቷልና መቀመጫችሁን ጠብቁ፡፡ ሊፍት አገኘን ብላችሁ ከማታውቁት ሰው መኪና ፈጽሞ እንዳትገቡ፡፡

ዘሐዲስ አየለ አበራ