በሀገራችን የተከሰተውን ረሀብ ተከትሎ ህይወት ለመታደግ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ዜግነታዊ ብቻ ሳይሆን ሀይማኖታዊ ግዳጅም አለበት ሲል ድምፃችን ይሰማ ገለጸ፡፡
በሀገራችን የተከሰተውን ረሀብ ተከትሎ ሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የወገኖቹን ህይወት ለመታደግ የመረባረብ ዜግነታዊ ብቻ ሳይሆን ሀይማኖታዊ ግዳጅም አለበት ሲል ድምፃችን ይሰማ ገለጸ፡፡
በሀገራችን የተከሰተውን ረሀብ አስመልክቶ ከ‹‹ ድምፃችን ይሰማ›› የተሰጠ መግለጫ
ድምፃችን ይሰማ
ሙስሊሙ ማህበረሰብ የወገኖቹን ህይወት ለመታደግ የመረባረብ ዜግነታዊ ብቻ ሳይሆን ሀይማኖታዊ ግዳጅም አለበት!
ረሀቡ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተሳትፏችን ሊጎላ ይገባል!!!
ሰኞ ህዳር 6/2008
ሙእሚን ህያው የሆነ፣ ልስልስና አዛኝ ልቦና ባለቤት ነው፡፡ በዚህ ህያው ልቡ ሌሎችን ከማወክ ይርቃል፤ ከወንጀል ይቆጠባል፤ በመልካም ያዛል፤ ከመጥፎ ይከለክላል፡፡ በዙሪያው ላሉ ፍጡራን ባጠቃላይ የበጎ ነገራት እና የሰላም ምንጭ ነው፡፡ ይህንን የሙእሚን ስነ-ምግባር ቁርዓን እንዲህ ይገልፀዋል፡-
‹‹በትዕግስትና (እርስ በእርስ) በመተዛዘንም አደራ ከተባባሉት ሰዎች መሆን ነው፡፡›› (አል በለድ፡ 17)
አንዱ ለአንዱ የመተዛዘን ታላቅ ስነ-ምግባር በሙእሚኖች የእርስ በእርስ ማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ ተፅእኖ በማሳደር ማህበረሰባቸው በእዝነትና በርህራሄ፣ በበጎና በፅድቅ የተሞሉ የተቀደሱ ስሜቶች መፍለቂያ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይህ መተዛዘን ከሰው ልጅ አልፎ ለእንስሳትም ጭምር የሚተርፍ ሊሆንም ይገባል፡፡ ኢስላም ለሰው ልጅ ክብርና ልቅናን ችሮታል፡፡ ምድር ፍላጎቱን እንድታሟላ እንደተገራችለት ያስተምራል፡፡ ‹‹የተፈጥሮ ሀብቶች ውስን ናቸው›› ከሚሉ ስግብግብነትን መፍጠር ከሚሹ ርዕዮተ ዓለሞች በተቃራኒ ለመተጋገዝ፣ መተሳሰብና መተዛዘን ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በተለይም የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት የሆኑት ምግብና መጠለያ በነፍስ ወከፍ ይዳረሱ ዘንድ ከመስበክና ማበረታታት ባለፈ የተራበን ማብላትን በተለያዩ አምልኮአዊ ስነ-ስርዐቶች ላይ ለሚፈጠሩ ጉድለቶች ማካካሻ (ከፋራ) እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የኢስላም የመረዳዳት ፅንሰ ሀሳብ ከአቅም ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ አቅም ያለው በእርዳታ ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ከማበረታትና ማስጠንቀቅ ባሻገር አቅም የሌላቸውም በማስተባበሩ ረገድ መሳተፍ የሚችሉበት ማዕቀፍ እንዳለ አመላክቷል፡፡ አቅም የለኝም ብሎ እርዳታን ከማስተባበር መዘናጋትን በሚከተለው መልኩ የእኩያንን ባህሪ ሲገልጽ እንደጉድለት በማንሳት በፅኑ አውግዞታል፡-
‹‹ድሀን በማብላት ላይም የማያግባባው ሰው ነው፡፡›› (ሱረቱል ማዑን፡ 3)
በተለይም ቁርአን ‹‹የረሀብ ባለቤት›› ሲል በሚጠራው ክፉ ቀን የተራቡን አለማብላት ለሰው ልጅ ከተሰጡት ሃላፊነቶች ውስጥ አንዱን እንዳለመፈፀም ይቆጥረዋል፡፡
‹‹ዓቀበቲቱንም አልወጣም፡፡ ዓቀበቲቱም (መውጣቷ) ምን እንደሆነ ምን አሳወቀህ? ….. ወይም የረሀብ ባለቤት በሆነ ቀን ማብላት (ነው)›› (አል በለድ፡ 12-14)
በሀገራችን የተከሰተውን ረሀብ ተከትሎ ሙስሊሙ ማህበረሰብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ የወገኖቹን ህይወት ለመታደግ የመረባረብ ዜግነታዊ ብቻ ሳይሆን ሀይማኖታዊ ግዳጅም አለበት፡፡ በእርግጥ ህዝበ ሙስሊሙን የሚወክል ተቋም ቢኖር በዚህ ወቅት ህዝብን በማስተባበር ለወገኖች በቀላሉ መድረስ በተቻለ ነበር፡፡ የእርዳታ መስመሩም ቀላል በሆነ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ለዚህ ባለመታደላችንና በመንግስት በተመረጡ ካድሬዎች የተሞላው ተቋማችን ህዝብ ሙስሊሙን መጨቆኛ ሽፋን ከመሆን ባለፈ ይህ ነው የሚባል የረባ ፋይዳ ሊያበረክት የሚያስችለውን መዋቅራዊም ሆነ አስተዳደራዊ ቁመና የተላበሰ ባለመሆኑ መሰል ሀላፊነቶች በግል በምናደርጋቸው ጥረቶች ላይ የተመረኮዙ ናቸው፡፡
ረሀቡ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የጎላ ሊሆን ይገባል፡፡ ከሌሎች ጋር በአጋርነት በሚደረጉ የእርዳታ ተግባራት ላይ መሳተፍ፣ እድርና መሰል ማህበራዊ መዋቅሮችን በመጠቀም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ፣ ከዚህ በፊት በፈጠርናቸው የተለያዩ አደረጃጀቶች በመጠቀምም የአቅማችን ሳንሰስት በመለገስ ለወገኖቻችን አጋርነታችን ልናሳይና ሀገራዊና ሀይማኖታዊ ሀላፊነቶቻችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ይህን መከራን እንዲያነሳልንና ይዞት ከሚመጣው ጉዳት ህዝባችንን ይታደገው ዘንድ ያለመሰልቸት ወደ አላህ (ሱ.ወ) ተደጋጋሚ ዱዐ በማድረግ ሰደቃዎቻችን በረሀብ ለተጎዱ ወገኖች የሚደርሱበትን መንገድ ማመቻቸት የነፍስ ወከፍ ግዴታችን ነው፡፡
ሁላችንም ወገንን ለማዳን እንረባረብ!!!!
ብሄራዊ ጭቆናን አንቀበልም! ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!
