የስንክሳሩ መጨረሻ ገፅ ታጠፈ – ሙሉጌታ ሉሌ አለፈ! ታሪኩ አባዳማ

የዚህ ታላቅ ሰው ድንገተኛ ዜና-ዕረፍት ህሊናዬን ዘልቆ አናውጦታል ፣ ለጥቂት አፍታዎች ተደነባብሬ ነበር፣ እስከ አሁንም ውስጤን በምናቤ ሳሰላስለው የሰቀቀን ስሜት እንደ ዋጠኝ አለሁ። ታላቅ ዋጋ የምትሰጡት ፣ ፋይዳ ያለው የአገር ፣ የህዝብ እና የታሪክ ስንከሳር የታጨቀበት ግዙፍ መርከብ በማእበል ተመቶ ባህር ውስጥ የመስመጥ አደጋ ደረሰበት የሚል ዜና የሰማሁ መሰለኝ። የዕውቀት ክምችት ፣ የዳበረ ልምድ ፣ የአገር የወገን ፍቅር ፣ የጋዜጠኛነት ጥበብ ፣ ለሙያ ባልደረቦቹ አለኝታነት… ሁሉም ተጠቃሎ መርከቡ ላይ እንደተጫነ ሰመጠ… ሙሉጌታ ሉሌ በሞት አመለጠ…

… ሙሉጌታ ሉሌ ዳግም ላይፅፍ ጣቶቹ በመላከ ሞት ታሰሩ ፣ ዳግም ላይናገር ዝም አለ።

ስለ ሙሉጌታ ሉሌ ከየት ጀምሮ ይነገር? በቅርብ ሳያውቁት በሩቅ ሆነው ብዙ ስም የሚያወጡለት እንዳሉ ታዝበናል። ከሩቅ ሆነው ፍርድ ለመስጠት የሚዳፈሩ አንድም በተፈጥሯቸው የሌላውን ስኬታማ ህይወት በበጎ የማየት ህሊና ያልታደሉ ወይንም በተራ አሉባልታ አራጋቢነት የተካኑ ደካማ ግለሰቦች ናቸው። ጋሽ ሙሉጌታን ለመግለፅ ከርሱ ጋር በቅርብ መተዋወቅን ፣ መወያየትን ቢቻል መሰነባበትን ይጠይቃል።

ዛሬ ከመካከለኛ እድሜ ዘመን ያለፍኩ ነኝ ብልም ከጋሽ ሙሉጌታ ለመማር ግን ሰንፌ አላውቅም ፣ እንደርሱ ካለ በምሳሌነት ከምትከተለው ሰው የምትቀስመው ትምህርት መቸም ቢሆን አያልቅም ፣ ሁሌም አዲስ ነው። በፖለቲካ ትንተና ፣ የታሪክ እውቀት እና የሙያ ብቃቱ ብሎም ለሌሎች የሚሰጠው ክብር እና ዋጋ አገራችን ካፈራቻቻው ጋዜጠኞች አውራ ከሚሰኙት ተርታ አሰልፎቶታል። ሙሉጌታ ሉሌ የንብ መንጋ ሲቀስመው ቢውል ቢያድር የማይጠወልግ አበባ ማለት ነበር። ከሙሉጌታ በቀሰምከው ጥበብ የህይወት ማር ትጋግርበታለህ።

ላለፉት ሀያ ስምንት ዓመታት በቅርብ አውቀዋለሁ። ከዚያ ቀደም ሲል ደግሞ ስለ ሙሉጌታ ሉሌ ዝና ስሰማ ነበር ያደገኩት። ነጎድጓድ ድምፁን በራዲዮ ፣ የተባ ብዕሩን በጋዜጣ እና መፅሔቶች ላይ ሳነብ ስመገብ ነው ያደኩት። እንደኔ ዝናውን ስትሰሙ አድጋችሁ ከዕለታት አንድ ቀን አውሮፕላን ላይ ከዚያ ሰው ጋር ጎን ለጎን ተቀምጣችሁ እያወጋችሁ ለተመሳሳይ ተልእኮ መጓዝ ምን ስሜት ያሳድርባቹሀል? እንደዚያ ነበር የሆነው። ቀኑን በውል በማላስታውሰው ወረሀ የካቲት 1980 (እንደ አገራችን አቆጣጠር) ወደ ጦር ግንባር ጉዞ ላይ አጠገቡ የመቀመጥ ዕድል አጋጥሞኝ የጀመርኩት ወዳጅነት ልምዱን ፣ ዕውቀቱን ፣ ሰብአዊ አመለካከቱን ፣ ፍፁም ኢትዮጵያዊነቱን ፣ ተሰምተው የማይጠገቡ ጨዋታውን እያጣጣምኩ እነሆ እስከ መስከረም 2008 ድረስ ዘልቄያለሁ።

እኔ ጋዜጠኛ ለመሆን ዝንባሌ ያደረብኝ ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ነበር። ስድሰተኛ ክፍል ሆኜ በትምህርት ቤት የመፅሔት ክበብ ተሳታፊ ነበርኩ። እንዲያ እያለ ሁለተኛ ደረጃ ስደርስ ትምህርት ቤታችን የትያትር እና መዝናኛ ክለብ ስር በረፍት ሰዓት በድምፅ ማጉያ ልዩ ልዩ ቁምነገር አዘል ጉዳዮችን ከሙዚቃ ጋር አጅበን ማቅረብ ጀመርን – እናም አስረኛ ክፍል ስደርስ አብዮት ‘ፈንድቶ’ ዕድገት በህብረት ዘመቻ ወጣሁ… ዘመቻ ፣ ዘመቻ … ዘመቻ

በዘመቻ ዘመን እና በመልሱ ላይ ሁሉም ነገር ድብልቅልቁ ወጣ – በዚያ አዲስ የህይወት ጉዞ ራስህን ፈልገህ ለማግኘት እና ራዕይህን ለመከተል መሞከር ደግሞ ከቶ አዳጋች ነበር። አድሀሪ ፣ ተራማጅ አብዮታዊ ጋዜጠኛ ፣ አድር ባይ ጋዜጠኛ… አድሀሪ ሰዓሊ ፣ ተራማጅ ሰዓሊ (አፈወርቅ ተክሌ የሳላት እናት ኢትዮጵያ አድሀሪ ተብሎ የተፈረጀበት ዘመን)… በወቅቱ ገንኖ የወጣው የግራ ፖለቲካ ሁሉንም ነገር በመደብ ከፋፍሎ የፈረጀ እንደመሆኑ ለፈጠራ እና ለምርምር የሚተጋ አይምሮ እንዲሸማቀቅ የተደረገበት ዘመን…

በዕድገት በህብረት ዘመቻ የተለከፍኩ ሰው አስራ ሰባት ዓመት ሙሉ አንዴ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ ሲባል ፣ የበቆሎ ምርት መሰብሰብ ዘመቻ ፣ የመልሶ ማቋቋም ዘመቻ… የጦር ግንባር ዘመቻ… እንዲያው ካንዱ ዘመን ዘመቻ ወደ ሌላው እንደ ኳስ ስላጋ ለጋ ዕድሜየን አገባድጄ ሳበቃ በመጨረሻ በስደት ተገላገልኩ። እና ጦር ሜዳ ዝመት ተብዬ ስዘምት ነበር ጋሼ ሙሉጌታን በቅርብ የተዋወቅሁት።
ዛሬ በጦር ሜዳ ውሏችን ስላየነው እና ስለ ሰማነው ልነግራችሁ አልፈልግም። የጦር ሜዳ ልምድ አስደንጋጭ ፣ አሳዛኝ ፣ አስደሳች ብሎም አስቂኝ ሁኔታዎች የሚፈራረቁበት መድረክ ነው። ሲቪል ሆኖ ጦር ሜዳ ምሽግ ይዞ ስራ ማከናወን ደግሞ ከወትሮው አሰራር እጅግ የተለየ በመሆኑ የመንፈስ ጥንካሬን ይጠይቃል። ይኼ በይደር ይቆየን።

ከጦር ሜዳ ግዳጃችን መልስ ከጥቂት ወራት በሁዋላ ዘማችነታችንን የሚያረጋግጥ ሜዳልያ ሊሰጠን መወሰኑን ሰማን። ነገሩ ውነት ነበርና ጥሪ ተደርጎልን መከላከያ ሚኒስቴር አደራሽ ተገኘን። ከፍተኛ ወታደራዊ እና ሲቪል ባለስልጣናት በስነስርዐቱ ላይ ተገኝተዋል። ከዛሬ ሀያ ስምንት ዓመት ገደማ ስለሆነ ጉዳይ ነው የማወጋችሁ። በቅድሚያ የመከላከያው ፣ ከዚያም በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አብዱልሀፊዝ ዩሱፍ አድናቆት የተመላበት ንግግር አደረጉ። አቶ አብዱልሀፊዝ በንግግራቸው መሀል ‘ይህ ዛሬ የምትቀበሉት ሜዳልያ ለላቀ ግዳጅ እና ሀላፊነት የሚያዘጋጃችሁ ነው…’ ሲሉ ተናገሩ።

ዘማች ጋዜጠኞችን ወክሎ የመልስ ንግግር ያደረገው ጀግናው ሙሉጌታ ሉሌ ነበር። ንግግሩ ተቀርፆ ስለነበር የሆነ የድምፅ ወይንም የፊልም ማከማቻ ውስጥ ሊገኝ ይችላል ብዬ ገምታለሁ። የተናገረውን በሙሉ ቃል በቃል ላስታውስ ባልችልም በህሊናዬ ተተክለው የቀሩ ሁለት ቁምነገሮች ነገሮች ግን አሁንም ትዝ ይሉኛል።

ከሞላ ጎደል እንደማስታውሰው ጋሽ ሙሉጌታ ሲናገር “… በዚህ ዘመን ጋዜጠኛ መሆን ማለት የገና ዳቦ አይነት ነው… ከላይ እሳት ከታች እሳት። መንግስት አቋሜን አራምድበታለሁ ሲል ከላይ ፤ ህዝብ ውነቱን ንገሩኝ ብሎ ለመብቱ ሲሟገት ከታች ድምፁን ያስተጋባል። ውነቱን በመናገራችን መንግስት ሲከፋ ፣ መረጃ ስናጣምም ህዝብ ሲቆጣ በመካከሉ እኛ ጋዜጠኞች እንደ ገና ዳቦ እያረርን ነው።’ በማለት ንግግሩን በመቀጠል ‘ዛሬ የምትሰጡን የጦር ሜዳ ውሎ ሜዳልያ ለተልእኳችን ማረጋገጫ ነው ቢባልም በአናታችን ላይ የእሾህ አክሊል እንዳጠለቃችሁብን ያህል ይሰማኛል። ስራችንንም ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል…”
ነበር ያለው።

ይህን አይነቱን ድፍረት የተመላበት ንግግር አድርጎ ተቀመጠ። ከስነስርዓቱ ማብቂያ ላይ ሻይ ቡና ተብሎ ወደ ቢሯችን ተመለስን። እኔም ቢሮ ገብቼ ስለ ጋሽ ሙሉጌታ ንግግር ሳሰላስል የቢሮዬ በር ተንኳኳ። የመስሪያ ቤቱ ተላላኪ አንድ ኤንቨሎፕ ይዞ ወደ ጠረጴዛዬ ተጠጋ። ከፍቼ አነበብኩት – “አገሪቱ በገጠማት ወሳኝ የህልውና ጥያቄ የተነሳ በድጋሚ ወደ ጦር ሜዳ እንዲዘምቱ የተወሰነ መሆኑን እንዲያውቁት…”

ምን? ጦር ሜዳ? እንደገና?

ኦ – ሚኒስትሩ አቶ አብዱልሀፊዝ ቅድም ሲናገሩ ‘… ሜዳልያው ለላቀ ግዳጅ የሚያዘጋጃችሁ…’ ያሉት ይህንን ነበር እንዴ? ለጋሽ ሙሉጌታ ስልክ ደውዬ ነገርኩት። በጣም ደነገጠ ግን እንዳላውቅበት ሁኔታውን በረጋ መንፈስ እንድይዘው መከረኝ። ትንሽ ተወራጨሁ። – ግን ተመልሼ ዘመትኩ። እነ ጋሽ ሙሉጌታ ሌላ የራት ግብዣ አዘጋጅተው በቸር ይመልስህ ብለው ሸኙኝ…

ጋሽ ሙሉጌታ አምላክ ነብስህን በዘላለማዊ ሰላም አክብሮ ያኑር!!