ነፍሴ ስለአባ ኃይለጊዮርጊስ ጉስቁልናና እንግልት አዘነች

በቅድሚያ የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፀጋና ሰላም ከእናንተ ከአባቶቻችን ጋር ይሁን።

በእስራኤል የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ ገዳም አባቶች የቤተክርስቲያኗን ህያዊና ሰማያዊ አጀንዳዋን ሳይዘነጉ የዕለት ተዕለት ብርቱ የመንፈሳዊ ህይወት ተጋድሎ በማድረግ ከሚገኙት አባቶች መካከል አንዱ በፍቅር የምንወዳቸው አበ ብዙሃን ውድ ዋጋ የከፈሉ ትጉህ እረኛ ካህኑ አባ ኃይለጊዮርጊስ ናቸው። አባታችን ቀሲስ አባ ኃይለጊዮርጊስ ዓለምን ንቀው እራሳቸውን ለክርስቶስ ሰጥተው መንጋውን ለማዳን የቅዱሳንን መርህ የተከተሉ ለምዕመናን በማይቀዘቅዝ ፍቅር በደግነትና በትህትና የተሞሉ፣ በየደቂቃው ውስጥና ጊዜ የቤተክርስቲያን ሃሳብ ሁሉ ከብዶባቸው በመንፈሳዊ ህይወት ተገኝተው የሚኖሩ ቤተክርስቲያንን በብቃትና በቅንነት በተሰጣቸው ፀጋ መንፈስ ቅዱስን እያገለገሉ እየባረኩ የሚገኙ የዕድሜ ባለፀጋ አባት ናቸው።

ነገር ግን በእኝሁ አባታችን በቀሲስ አባ ኃይለጊዮርጊስ ላይ እግዚያብሔር በተለያቸውና እግዚያብሔርን በማያውቁ ደቂቀ በለአሞች መቅደም ሲያቅታቸው በፀጋና እምነት የቆሙትን አባት ለመቀጥቀጥ ያደቡ ቀቢጸ ተስፈኞች በቅርቡ በጎብኝዎች ስም በኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን ውስጥ ያደረሱት በደል ጸረ ክርስቲያናዊ የሆነ ሀማዊያን ሴራ ነውና በዓለም ዙሪያ የምንገኝ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው በአፅንኦት ይህ ለቤተክርስቲያን ድፍረት ነውና አጥብቀን እንቃወማለን። በተፈጠረው ነገር ልባችን በሃዘን ከብዷል።

እስከ መቼ አበ ብዙሃን የሆኑ ገዳማዊያን አባቶቻችን ባገለገሉና በእምነትና በፅናት ይህንን ዓለም ንቀው በተቀመጡ እየተንገላቱ እየተዋረዱ ማዶ ለማዶ እየተያየን እንኖራለን? ቢታየንም ባይታየንም እነሆ ድፍረት ልኩን አልፏልና ማንም ሃሳዊ መሲህ የራሱን መንፈሳዊ ኪሳራ በገዳሙ ባሉ አባቶቻችን ካህናት ላያ ሊያራግፍ ከቶ አንፈቅድም። ይህ ድርጊትበጊዜው መቋጫ ካልተበጀለት የሚበጅ ሳይሆን የሚፈጅ ነውና አባቶቻችን ተሳቀው የሰቆቃ ህይወት እንዲገፉና የቤተክርስቲያን በር ተዘግቶና ተከርችሞ እንዲውል የተሸረበ የጥፋት ድግስ ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል። በዚህ ደወል በመንቃት አስቸኳል መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል። እንዳይደገምና አባቶቻችንን ከሌላ መሰሪ ጥቃት ለመከላከል ቱሪስቶች በጉብኝት ስም እስከ ጫማቸው እየገቡ የተቀደሰውን ከማርከስ በስተቀር ምንም ፋይዳ የለውና መላ ይበጅለት ዘንድ የገዳሙን (የመነኮሳቱን ማህበር) እናሳስባለን።

ነፍሴ ስለአባቶች ካህናት ጉስቁልናና እንግልት አዘነች መጽሐፍ ቅዱስም ነፍሴ ስለእስራኤላዊያን ጉስቁልና አዘነች እንዲል፤ “ ዳሩ ግን የትዕግስቴን ቃል ስለጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅህሃለሁ” ራዕይ 3-10 ይላልና የእግዚያብሔር ጥበቃ የትዕግስቱን ቃል ባጠበቁት በአባታችን በካህን አባ ኃይለጊዮርጊስ ላይ ነውና በዚህ እንጽናናለን። “የምንናገረው ብዙ አለን፣ጆሮዎቻችሁ ስለፈዘዙ በቃል ልንተረጉመው ጭንቅ ነው”። ዕብ 5-11 ይላልና ከፈዘዝንበት ፈጥነን በመውጣት በሮቻችንን እናጥብቅ። ነፍሴ ስለአባቶች ጉስቁልናና እንግልት አዘነች።
መንፈሳዊ የልጅነት ሰላምታዬ ባላችሁበት ይድረሳችሁ።

ገብርኤል ብዙነህ

ከአገረ አሜሪካ