የ50 ዓመታት የከያኒ ህይወት- ከኮረዳነት እስከ እማወራነት!
“እኔ በቁሜ ብሸለምም ሽልማቱ ለሌሉት ባልደረቦቼም ነው” (አርቲስት ዙፋን)

“ቆንጆ ቆንጆ ሴቶች ፈልጉ” ተብሎ ነው፤ተመርጬ የተቀጠርኩት
· ተወዛዋዥነት ለዘመናት ተንቆ የኖረ ሙያ ነው ትላለች
የ50 ዓመት የኪነ ጥበብ ጉዞሽ እንደሚዘከር ቀደም ብሎ መረጃ ነበረሽ? በሰማሽ ወቅት ምን አልሽ? የአንጋፋ አርቲስቶችን የረዥም ዘመን የኪነጥበብ አገልግሎት መዘከር የተለመደ ይመስላል፡፡ ትክክል ነኝ?
የተሰማኝን ነገር እንኳን ልነግርሽ አልችልም፡፡ እግዚአብሄር እራሱ ሲፈቅድ ነው ሁሉም የሚሆነው፡፡ እኔ በቁሜ እያለሁ ይሄ በመደረጉ ከምነግርሽ በላይ ደስ ብሎኛል (በስሜት እያለቀሰች) ምክንያቱም የውዝዋዜ ሙያ እንደ ሙያ፣ ሙያተኛውም እንደ ሙያተኛ ሳይቆጠር ዘመናት አልፈዋል፡፡ መጀመሪያ የ50ኛ ዓመት በዓሉ ሊከበር የነበረው መስከረም 27 ነበር፡፡ በመንግስት ስብሰባዎች ምክንያት ወደ ጥቅምት ሁለት ተዛወረ፤ ከዛ በኋላ እንደገና ወደ ጥቅምት 11 ተዛውሮ፣ እናትና ልጁ ሲፈቅዱ (ክርስቶስንና ማሪያምን ማለቷ ነው) ያው በዚህ ቀን በልዩ ሁኔታ ተከበረ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ባህልና ቱሪዝምን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ የብሔራዊ ቴአትር የባህል ማዕከል ሰራተኛ የሆነችውን ወ/ሮ ብርሃንንም አመሰግናታለሁ፤ ብዙ ደክማለች ለዚህ በዓል፡፡ ድካምና መሰላቸት ሳይሰማት ለዚህ ክብር አብቅታኛለች፡፡ ለዚህ ክብረ – በዓል ብዙ የለፉትን ሌሎችንም ሁሉ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
የውዝዋዜ ሙያና ሙያተኛው በተለየ ሁኔታ የማይከበሩበት ምክንያት ምን ነበር ?…
እኔ እንግዲህ መንታ አርግዤ እንደተገላገልኩ የምቆጥርባቸው ሁለት ነገሮች አሉኝ፡፡ ሙያውና ሙያተኛው እንደሙያተኛ አለመቆጠራቸውና ክብር አለማግኘታቸው አንዱ ያረገዝኩት ሃሳብ የነበረ ሲሆን ሁለተኛው የምንሰራው ብሔራዊ ቴአትር ይሁን እንጂ እኛ ተወዛዋዦች የመንግስት አልነበርንም፡፡ ስለዚህ የጡረታ መብት አልነበረንም፡፡ ከዚያ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተን፣ የማዘጋጃ ቤት አንድ አርቲስት ህይወቱ አልፎ፣ ስንቱ በሳንጃ ተወግቶ ነው ጡረታችንን ያስከበርነው፡፡ ለ4 ወር ታስረን ሁሉ ነበር፡፡ በደምና በህይወት የተገነባ መብት ነው፡፡ የተወዛዋዡን ጉዳይ በተመለከተ ምንም ክብር አልነበረም፡፡ ቴአትር የሰራ፣ ዘፈን የዘፈነ፣ አሁን ዘመን ያመጣውን ፊልም የሰራ ጭምር ሲሸለም ታያለሽ፡፡ የኛን ሙያ ስታይና ስታስቢው ያሳለፍነው መከራ ይከብዳል፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩ የዘርፉ ባለሙያዎች፤ በትንሽ ብር ደሞዝ ሀብት ንብረት ሳያምራቸው፣ ለሙያው ፍቅር ሲሰሩና መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡ ቀጣዮቹ እኛ ነን፤ ከኛም በኋላ የመጡ አሉ፡፡ ስለዚህ በተሰጠሽ ሙያ ተተኪን ታስተምሪያለሽ፤ ታሰለጥኛለሽ፤ ራስሽም ታገለግያለሽ፡፡ ለምን ብትይ… ያለፉት ለእኛ አስተምረዋል አገልግለዋል፡፡ በሌላ በኩል ተወዛዋዥ የሚሰራው ውዝዋዜ ብቻ አይደለም፡፡ ሁለገብ ነው፤ ቴአትርም ዘመናዊና ባህላዊ ውዝዋዜም… ብቻ ብዙ ነገር ይሰራል፡፡ ይህን ሁሉ የሚሰራው ሙያተኛ ግን አንድም ቀን ስሙ ሲጠራና ሲወደስ አትሰሚም፤ ሲሸለምም አታይም፡፡ ውዝዋዜ የዕድሜ፣ የጉልበትና የወጣትነት ስራ ነው፡፡ ለምን ስሙ አይነሳም? ለምን አይሸለምም? የሙዚቃ ማህበራት፣ የቲያትር ማህበራት፣ የፊልም ሰሪዎች ማህበራት አሉ፤ የውዝዋዜ ግን የለውም፡፡
እነዚህ ሁሉ ነገሮች ይቆጩሽ ነበር?
በጣም ይቆጨኝ ነበር… በጣም! እኔ እንደሚታወቀው፤ ለሚዲያም ቅርብ አይደለሁም፤ ግን አንድ ቀን እድል ገጥሞኝ ይህን ቁጭት እንደምናገረው እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ይሄው እግዚአብሔር ፈቅዶ፣ 50ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ ሲከበር በደንብ ተናገርኩት፡፡ አንደኛ በእንዲህ መልኩ በውዝዋዜ ጥበብ 50 ዓመት ሰርታለች ተብዬ፣ ክብረ በዓሉ መዘጋጀቱ አንዱን አረገዝኩ ያልኩሽን ሃሳብ እንደመገላገል ነው፡፡ ሽልማቱ፣ ክብረ በዓሉና ዝግጅቱ የእኔ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት በዘርፉ ብዙ ሰርተው፣ ምንም ክብርና ሞገስ ሳያገኙ ላለፉት ሁሉ ነው፡፡ አንድ ሰው ግጥም ይጽፋል፣ ሌላው ዜማ ሊደርስ ይችላል፡፡ አቀናባሪው ሙዚቃውን ያቀናብራል፡፡ ከዚያ በኋላ ተወዛዋዡ መድረክ ላይ ይውረገረግበታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተቀናጅተው ነው አድማጭ ተመልካችን በቁጥጥር ስር የሚያውሉት፡፡ እንደ ጆሮ ሁሉ አይንም እኮ ሙዚቃን ማየት ይፈልጋል፡፡ ቪሲዲ የሚሰራው ለዚህ አይደለም እንዴ? ውዝዋዜ ለሙዚቃ የጀርባ አጥንት እኮ ነው፡፡
ከዚህ በፊት የተሸለሙ ተወዛዋዦች የሉም?
እርግጥ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም የኢትዮጵያ የባህል ማዕከል ይህን ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ ለአርቲስት መርአዊ ስጦት፣ ለአርቲስት ደስታ ገብሬም ሲዘጋጅላቸው ነበርኩኝ፡፡ ነገር ግን ደስታ ገብሬ ማለት የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ውዝዋዜ በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ በአፍሪካና በክልል ስታስተዋውቅ ዘመኗን የጨረሰች ናት፡፡ ወዲህ ደግሞ ስትጨፍር አይን የምታፈዝ፣ አጥንት አላት የላትም እየተባለ የምታከራክር ትልቅ ባለሙያ፡፡ ከዚህ አንጻር አንደኛ በህይወት እያለች ባለመሸለሟ፣ ሁለተኛ ደግሞ በዝግጅቱ ቀን ብዙ ሰው ባለመምጣቱ በጣም ቅር ተሰኝቼ ነበር፡፡ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ አበባ ማስቀመጥ፤ ወዲህ ወዲያ ማለት ጥቅም የለውም፡፡ እንደኔ በቁሙ ያለ ሰው፤ እንዲህ አይነት ክብር ሲደረግለት ግን እጅግ ያስደስታል፡፡
ያንቺ የ50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ምን ይመስል ነበር? …
ከጅምሩ ልጆቼና የልጆቼ ጓደኞች ቀኑ ደርሶ ዝግጅቱ ሲጧጧፍ፣ እኔ በሌሊት ፀጉር ቤት ሄጄ ፀጉሬን ተሰርቼ ስመጣ፣ በራሴ መኪና እንደምሄድ ነበር የማውቀው፡፡ ልጆቼም የራሳቸው መኪና አላቸው፡፡ እናም በእናንተ ታጅቤ ስለምሄድ፣ መኪናችሁን አዘጋጁ፤ አገር ልብስም አዘጋጁና ልበሱ ብያቸው ነበር፡፡ ከፀጉር ቤት እንደመጣሁ ትንሿ ልጄ፤ “ማሚዬ፤ ዛሬ እኔ ነኝ ፕሮቶኮል፤ ተረጋጊ” አለችኝ፡፡
ወደ ብሔራዊ የመጣሽው ግን በራስሽ መኪና ሳይሆን በሽንጠ ረጅም ሊሞዚን ነበር—–
ልክ ነው ልነግርሽ ነው፡፡ ከዚያ በቃ ገባሁ፤ ለበስኩና “በሉ እንዳናረፍድ እንውጣ” ስላቸው፣ “ቆይ ማሚ ትንሽ እንቆይ፤ ከዝግጅቱም ቦታ እየደወሉ ነው፤ እኛም በስልክ እየተገናኘን ነው” ይሉኛል፡፡ ልክ ወደ ውጭ ስወጣ፣ የ “ዋዜማ” ድራማ ካሜራ ማንን አየሁት፡፡ እንዴ እዚህ ምን ይሰራል ብዬ ገረመኝ፡፡ “ለምን እዚህ መጣህ ሳሚ?” አልኩት “ማሚዬ፤ ካንቺ ጋር ከቤትሽ ጀምሮ አብሬ መሄድ ፈልጌ ነው” አለኝ፡፡ እኔ አዳራሽ እንዲመጣ ነበር የጠራሁት፡፡ ለካ ከልጄ ጋር ተነጋግረው ኖሯል፡፡ ስወጣ ፎቶ እንዲያነሳኝ ተጠርቶ ነው፡፡ ከዚያ ለባብሼ ጨርሼ ስወጣ፣ ያን ሊሞዚን ተገትሮ አየሁት እልሻለሁ፡፡ ልጆቼና ቤተሰቦቼ ናቸው ሰርፕራይዝ ያደረጉኝ፡፡ ልጆቼ፣ ቤተሰቤና የልጆቼ ጓደኞች፤ በአበባ የታጀበውን ሊሞዚን ከበው እልልል ይባላል፡፡ በጣም ነው ያለቀስኩት! (አሁንም እያለቀሰች)
በደስታ ስሜት —-?
አዎ! አንደኛ ይህን ሁሉ ሳያዩ ያለፉ ተወዛዋዥ አስተማሪዎቼን አስቤ አለቀስኩ፡፡ እኔ የደረስኩበት አልደረሱም፤ ቢያንስ በህይወት ቢኖሩ ጡረታ ይወጡ ነበር፡፡ ለሙያው እየተሰጠ ያለውን ክብር ያዩ ነበር፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች እንዲሁም ቤተሰቤና ልጆቼ ባደረጉት ነገርም በጣም ተደሰትኩኝ፡፡ ከዚያ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ማልቀስ ሲያንሰኝ ነው፡፡ በብሔራዊ ቴአትር፣ የአገር ፍቅር— የባንዲራ ፍቅር—— የብሔር ብሔረሰብ ፍቅር… ያስተማሩን፣ ከአገራችን ወጥተን በዚያው እንዳንቀር፣ አገራችንን እንድንወድ ያደረጉን አንጋፋዎቹ አልፈዋል፤ ይህንን አላዩትም (አሁንም ለቅሶ…) እኔ በህይወት ቆሜ ብሸለምም ሽልማቱ የእነሱም ነው፡፡ በህይወት እያሉ በየጓዳው ተረስተው የቀሩ፣ በውጭም በስደት ህይወታቸውን የሚገፉ፣ ለሙያው መስዋዕትነት የከፈሉ ብዙ አሉ፤ ሽልማቱ የእነሱም ጭምር ነው፡፡
ሽልማትሽ ምን ነበር?
ብዙ ነገር ተሸልሜያለሁ፤ ወርቅ፣ ብርና የተለያዩ ነገሮችን ተሸልሜያለሁ፡፡ ከ “ዋዜማ” ድራማ አዘጋጆችና ተዋንያን፣ እንደ አዋርድ የሚሰጥ ሽልማት ተበርክቶልኛል፡፡ ከተለያዩ አርቲስቶችም በርካታ ሽልማት አግኝቻለሁ፡፡ ከሽልማቱ ይበልጥ የሚያኮራው ደግሞ እያንዳንዱ ሰው፤ ስለኔ የሚያወራውና የሚሰጠው ምስክርነት ነበር፡፡ “አልጋነሽ ማለት ይህቺ ናት፤ እሷ ማለት እንዲህ ናት—” ተብሎ በቁምሽ ስትሰሚ፤ከዚህ በላይ ደስታ የለም፡፡ ይህ ክብረ በዓል ተከታዮቻችንን ያበረታታል፤ ለሙያቸው ፍቅር እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
ከብሔራዊ ቴአትር ጡረታ የወጣሽው መቼ ነው?
ጡረታ የወጣሁት 2001 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ አሁን በግሌ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡
በመሃል ግን ውጭ ቆይተሽ መጥተሻል፡፡ የሄድሽው ለስራ ነበር ወይስ ለእረፍት?
ጡረታ እንደወጣሁ አሜሪካ ሄጄ፣ ሁለት ዓመት ቆይቼ ነው የተመለስኩት፡፡ እንደተመለስኩም፤ በየሻሽ ወርቅ በየነ የተዘጋጀ “ደመነፍስ” የሚባል ቴአትር አስተባብር ነበር፡፡ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ እየሰራሁ ነው ያለሁት፤እግዚብሔር ይመስገን፡፡
በአሁኑ ወቅት “ቃቄ ወርዲዮት”፣ “ዋዜማ” —- ላይ እሰራለሁ፡፡ ይኼው ለብሔራዊ ቴአትር 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ዝግጅትም እየሰራን ነው፡፡ እኔ ጡረታ ብወጣም ከቤቱ አልወጣሁም፡፡ ብሔራዊ ቴአትር፤ ለእኔ አባቴም እናቴም፣ለእዚህ ሁሉ ያበቃኝ ስለሆነ ከዚህ መራቅ አልፈልግም፡፡ ከታላቆቼም ከታናሾቼም… በቤቱ ካሉ የአስተዳደር ሰራተኞችም ጋር ተዋድጄ ነው የምኖረው፡፡
እስኪ ወደ ኋላ ልመልስሽ —– ትውልድና እድገትሽ የት ነው?
ተወልጄ ያደግሁት ጎጃም ውስጥ ነው፡፡ በጣም ትንሽ ሆኜ ነው አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ እዚሁ ነው ያደግኩት፡፡ የጎጃም ተወላጅ ሆኖ አዲስ አበባ የሚኖር ሰው አግብቶ በልጅነቴ ይዞኝ መጣ፡፡ ያው እንደሚታወቀው፣ በዛን ዘመን ልጅ ሆነሽ ትዳሪያለሽ፤ ለአቅመ ሄዋን እስክትደርሺ ባልሽ ጋ ታድጊያለሽ፤ እኔም በዚህ መልኩ አግብቼ ሊያስተምረኝ አመጣኝ፤ አልተመቸኝም፤ ወደ አገሬ ተመለስኩኝ፡፡ ከዚያ ብዙ ሳልቆይ አክስቴ አዲስ አበባ አመጣችኝ ግን የሚያስተምረኝ አልተገኘም፡፡ ከዚያ ወደ ብሄራዊ ቴአትር መጣሁና ተቀጠርኩኝ፡፡ ዋናው ነገር በአሁኑ ሰዓት ደስ የሚለኝ፤ እኔ ያላገኘሁትንና የተቆጨሁበትን ትምህርት፤ በወንድሞቼ፣ በልጆቼ፣ በዘመዶቼ ተወጥቼዋለሁ፡፡ አሁን ያስተማርኳቸው ፕሮፌሰር፣ ዶክተር ወንድሞች አሉኝ፡፡ ልጆቼንም አስተምሬያለሁ፤ ሁሉም በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት፡፡
ብሔራዊ ቴአትር እንዴት ተቀጠርሽ?
ያን ጊዜ የባህልም የዘመናዊም ተወዛዋዥ እንዲኖራቸው አርቲስት አውላቸው ደጀኔ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በባህሉ በኩል የራሳቸው ተወዛዋዦች እንዲኖራቸው ሲፈቀድላቸውም “ቆንጆ ቆንጆ ሴቶች ፈልጉ” ተብሎ፤ተፈልጌ ነው ተመርጬ የተቀጠርኩት፡፡
ያው መልክሽም ቁመትሽም የሰጠ ሆኖ ተገኘሽ? እንዴታ! መልክና ቁመና፣ ቅጥነት ጭምር መስፈርት ነበር፡፡ በወቅቱ ስንፈተን ደግሞ ዝም ብሎ ፈተና እንዳይመስልሽ፡፡ እስከ ላይ እስከ ጭንሽ ድረስ ልብስሽን ገልበሽ፣ አንዲት ጠባሳ በሰውነትሽ ላይ ካለ፣ አታልፊም፡፡ ፈታኙ በወቅቱ አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ ነበር፡፡ ጠባሳው ብቻ ሳይሆን አቋቋምሽም ይታያል፤እግርሽ ቀጥ ያለ መሆን አለበት፤ወልገድ ሸፈፍ ካልሽ አለቀልሽ፡፡
የበረራ አስተናጋጆች እንደሚመለመሉት ማለት ነው?
እንደዚያ ነው! ከባድ ነበር ፈተናው፡፡ ከዚያ ስድስት ልጆች ተመረጥን፡፡ የሚገርምሽ ስድስታችንም በህይወት አለን፡፡
እስኪ እነማን እንደነበራችሁ —– የሌሎቹን ስም ንገሪኝ?
አልማዝ ሀይሌ (ማሚ)፣ አሰለፈች በቀለ፣ ወይንሸት በላቸው፣ አበበች ገ/ሚካኤል፣ አሰለፈች ገሰሰ፣ አልጋነሽ ታሪኩ ነን፡፡ ፍቅርተ ጌታሁን ሰባተኛ ናት፡፡ አሰለፈች ገሰሰና አሰለፈች በቀለ ውጭ ነው የሚኖሩት፤ ሌሎቻችን እዚሁ አለን፡፡ አሁን ለብሔራዊ ቴአትር 60ኛ ዓመት፣ ወገባችንን ስናውረገርግ ለማየት ያብቃሽ እንግዲህ፡፡
ብሔራዊ ቴአትር በስንት ዓመትሽ ነበር የተቀጠርሽው?
ምናልባት 16 ዓመት ቢሆነኝ ነው፤ በጣም ልጅ ነበርኩኝ፡፡
ውዝዋዜ ያቆምሽው መቼ ነው?
ለ24 ዓመት በውዝዋዜ ከሰራሁ በኋላ ነው ያቆምኩት፡፡ ለምን አቆምሽ ብትይ…በድሮ ጠቅላይ ግዛት፣ በአሁኑ ክ/ሀገር ስትሄጂ፣ ውዝዋዜም ቴአትርም ይዘሽ ሄደሽ ነው የምትሰሪው፡፡ ስለዚህ ባህል ትሰሪያለሽ፤ መሀል ላይ ቴአትር ትሰሪና ከዚያ በባህል ትዘጊያለሽ፡፡ ወይም ባህልና ዘመናዊ፣ ከቴአትር ጋር ይዘሽ ትሄጂና በዘመናዊ ዳንስ ትዘጊያለሽ… እንዲህ ነበር የሚሰራው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭ የብሄር ብሄረሰቦችን ስራ እንሰራለን፤ ፈረንጅ ቋንቋችንን ስለማያውቀው፣ማይም የሚሰራበትም ጊዜ አለ፡፡
በዚህን ወቅት መጀመሪያ የውብሸት ወርቃለማሁ ድርሰት የሆነውን “አንድ ለሶስት” ድራማ ሰርቻለሁ፤ “ሀሁ በስድስት ወር” ላይ የለማኝ ገፀ ባህሪ፣ “እናታለም ጠኑ” የጉሊት ሽንኩርት ነጋዴ፣ “ሀኒባል” ላይ ወታደር፣ “ቴዎድሮስ” ላይ የንግስቲቱ ገረድ ሆኜ —— ተጫውቻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ በመዋቅር ዝውውር ወደ ቴአትር ክበብ ገባሁ፡፡
በማስተባበር ደረጃ እነ “ደመነፍስ”ን አስተባብሬያለሁ፡፡ በ “ገመና” አንድ ላይም የቃልኪዳን አክስት ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ አሁን “ዋዜማ” ድራማ ላይ ታማሚዋ ጥሩዬን ሆኜ እየሰራሁ ነው፡፡ ገና ያልታየ “የኔ ዘመን” ፊልም ላይ እየተወንኩ ነው፤ በቅርቡ ተጠናቅቆ ይመረቃል፡፡ “ይግባኝ” ላይም ዳኛ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡
እኔ የምለው —-“ይግባኝ”፣ “የባላገር ፍቅር”፣ “በእንቅልፍ ልብ“፣ “ዋናው ተቆጣጣሪ”፣ የተሰኙት ቴአትሮች ላይ የተወንሽው ወደ ቴአትር ክፍል ከተዛወርሽ በኋላ ነው?
ልክ ነው ግን አሁን ጠፋብኝ እንጂ በማስተባበርም በመተወንም ብዙ ሰርቻለሁ፡፡ “ስሌት” ፊልም ላይም ተውኛለሁ፡፡
ብሔራዊ ቴአትር ውስጥ መኪና የገዛሽ የመጀመሪያዋ አርቲስት አንቺ ነሽ ይባላል፡፡ ይሄ እውነት ነው?
ልክ ነው፤ በ1966 መስከረም 19 ቀን ነው መኪናዬ ከሞኤንኮ የወጣው፤አዝዤ ነው ያስመጣሁት፡፡ በደርግ ጊዜ እሱ መኪና ነዳጅ ይበላል ተብሎ እንዲገባ አይፈቀድም ነበር፤ ላለፉት 40 ዓመታት ነድቼዋለሁ፡፡ አሁን 41ኛ ዓመቱን ይዟል፤እሱ ቀለም እንዲቀባ ጋራዥ ገብቷል፡፡ አሁን ልጆቹ ለልደቴ ኮሮላ መኪና ገዝተውልኝ ነው የምነዳው፡፡ ከብሔራዊ ቴአትር የመጀመሪያ መኪና ገዢ ብሆንም ከሃገር ፍቅር አሰለፈች አሽኔና ዘነበች ታደሰ (ጭራ ቀረሽ) ቀድመውኝ ገዝተው ነበር፡፡
ስንት ልጆች አሉሽ?
ሶስት ሴቶች ልጆች አሉኝ፡፡ በጥሩ ሁኔታ ነው ያሳደግኋቸው፡፡ አንዷ ዲፕሎማና ዲግሪዋን ይዛ የራሷን ስራ ትሰራለች፡፡ አንዷ አግብታ፣ አንድ ልጅ ወልዳለች፤ ሆስተስ ናት፡፡ አንዷም አግብታ አሜሪካ ነው የምትኖረው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡
Adsis Admass