የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የምልአተ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር፤ “የመሪ ዕቅድ ጥናቱ ሥራ ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ ሊነጋገርበት ይገባል”

  • መሠረታዊ ችግር ሊኾን የሚችለው ክፍተት ለምን ተፈጠረ የሚለው ሳይኾን ክፍተት መኖሩ እየታወቀ ዝም ብሎ መኖሩ ነው
  • ሕዝበ ክርስቲያኑ ቤተ ክርስቲያኑን ለመደገፍና ለማልማት የሚያደርገው ቀና ትብብር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተሰፋ ሰጪ ኾኖ ይታያል
  • ሐዋርያዊ ተልእኮን ለማስፋፋት በተደረገው እንቅስቃሴ ከምዕራብ አሜሪካ እስከ ጃፓን፤ ከአየርላንድ እስከ አውስትራልያ ቤተ ክርስቲያናችን ክንፎቿዋን የዘረጋችበት ኹኔታ በመፈጠሩ ዓለም አቀፋዊት ወደ መኾን አድጋለች ማለት ይቻላል
  • የሕዝብ እናት የኾነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን አቅሟ የሚችለውን ኹሉ ታደርግ ዘንድ፣ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በጉዳዩ መነጋገር አለበት፡፡

*           *          *

????????????????????????????????????

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ የቤተ ክርስቲያንን ርእይ እና ተልእኮ በግልጽ የሚያሳይ ስትራተጅያዊ የአመራር ሥርዐት በአስተዳደሩ እንዲነደፍና የተሟላ የማሻሻያ ሐሳብ እንዲቀርብ የጠየቁት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በርእሰ መንበርነት በመሩት የግንቦት 2005 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ነበር፡፡ ምልአተ ጉባኤውም፤ ቤተ ክርስቲያን በመሪ ዕቅድ አገልግሎቷን ለማከናወን እንድትችል÷ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንት፣ ምሁራን ምእመናን የሚገኙበት ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን የማጣራትና የማጥናት ሥራውን እንዲቀጥል በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኗል፡፡

በጥቅምት 2006 ዓ.ም. ምልአተ ጉባኤው፣ በዐቢይ ኮሚቴው የመሪ ዕቅድ ጥናቱን ዘገባ መገምገሙን በመግለጫው አስታውቆ፣ በቀጣይ ዕቅዱ ዳብሮ በሥራ ለመተርጎም የሚቻልበት ኹኔታ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ መመሪያ ሰጥቷል፡፡ በተከታዩ የግንቦት 2006 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ የዳበረው የመሪ ዕቅድ ዘገባ በስፋት ለምልአተ ጉባኤው ከተገለጸ በኋላ የመጨረሻው መሪ ዕቅድ “በጥራዝ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ለማስቻል ጥናቱ በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ አስፈላጊው እንዲፈጸም” ሲል መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ይኹንና ከዚህ በኋላ የውሳኔው አፈጻጸም ስላለበት ደረጃ በይፋ የተገለጸ ነገር ሳይሰማ ቆይቷል፡፡ በአጭር ጊዜ የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ቢያዳግት እንኳ ቢያንስ መሠረቱ በአስቸኳይ እንዲቀመጥና አቅጣጫው እንዲቀየስ የታሰበው የለውጥ ሒደትም ተስተጓጉሎ ታይቷል፡፡ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ዕጦትን ከሥሩ በመቅረፍ የፀረ ሙስና ሥርዐት መደንገግን፤ ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት የማስገኘትን ያኽል ቆራጥነት እንደሚጠይቅ የተናገሩት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩም ከዚኽ በላይ እንዲዘገይ ባለመፍቀድ፣ በተጀመረው ዓመት በጀት ተይዞለት በአፋጣኝ ሥራ ላይ ይውል ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶሱ መነጋገር እንዳለበት በዛሬው የምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ንግግራቸው ጠቁመዋል – “እስከ አኹን በይደር የቆየውን የመሪ ዕቅድ በዚህ በጀት ዓመት በጀት ተይዞለት በአፋጣኝ ሥራ ላይ መዋል”

የቅዱስነታቸውን የስብሰባ መክፈቻ ንግግር በማዳመጥ እና የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ በመሠየም ሥራውን የጀመረው ምልአተ ጉባኤውም፤ ከኮሚቴው በቀረበለት መሠረት ካጸደቃቸው የመነጋገርያ ነጥቦች መካከል፤ “የመሪ ዕቅድ በጀት ስለመወሰን” እንደሚገኝበት ለማወቅ ተችሏል፤ የጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዓመታዊ በጀትም ተመርምሮ የሚጸድቅበት ነውና፡፡

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የጥቅምት 2008 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ የመክፈቻ ንግግር ይህንና ሌሎች ዐበይት ጉዳዮችን ያካተተ ሲኾን ሙሉ ይዘቱም የሚከተለው ነው፡፡


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

የአማልክት አምላክ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የአጋዕዝት ጌታ የኾነው እግዚአብሔር አምላካችን፣ ከተለያዩ የዓለም አህጉርና ከሀገራችን አህጉረ ስብከት አሰባስቦና አንድ ላይ አገናኝቶ በመንፈስ ቅዱስ ስለተሰጠን ሐዋርያዊ ተእልኮ ለመወያየት ስለሰበሰበን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይኹን፡፡

ምንተ ይቤ መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት፤ መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርስቲያናትን አስመልክቶ ምን አለ?(ራዕ. 2፡7)፡፡

በጌታችን በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተችው ክርስቶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከበዓለ ኃምሳ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ አመራርና ጥበቃ ሥር እንዳለች ይታወቃል፡፡

ቅዱስ መንፈሰ እግዚአብሔር ዓለም በማያየውና በማያውቀው ረቂቅ ጥበቡ በሃይማኖት አማካይነት በልበ ምእመናን አድሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲመራ ይኖራል፡፡ ከዚህም ሌላ በሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ቅዱስ ቃሉንና ቅዱሳት ምሥጢራቱን ለምእመናን ያድላል፡፡

በመኾኑም ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሪ የኾነው መንፈስ ቅዱስ የሚለውንና የሚናገረውን በትክክል አዳምጠውና ተረድተው ምግብናቸውን ማከናወን እንዳለባቸው ለሰባቱ ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን ዘእስያ የተነገረው ቃለ ተግሣጽ ወምዕዳን በግልጽ ያስተምረናል፡፡

ለተጠቀሱት የቤተ ክርስቲያን ሥዩማን የተላለፈው መልእክት በአጠቃላይ የመንፈስ ቅዱስ ቃል እንደኾነ ለማመልከት፤ ምንተ ይቤ መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት፤ በሚልና ዘቦ ዕዝን ሰሚዐ ለይስማዕ በሚል ኃይል ቃል ሲዘጋ እናያለን፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ለሰብዑ አብያተ ክርስቲያናት ዘእስያ እና ለአለቆቻቸው የተነገረው ኹሉ ዛሬ ያለችው ቤተ ክርስቲያንና አለቆቿን ጭምር በቀጥታ የሚመለከት እንደኾነ ጥርጥር የለውም፡፡

ከአለቆቹ መካከል የተመሰገኑም፣ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙም፣ እንደዚኹም ጠንከር ያለ ተግሣጽ የደረሰባቸው እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡

ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሥራ ሓላፊነት የምንገኝ ሥዩማንም በዚያን ጊዜ በነበረችው ፈታኝ ዓለም ውስጥ የምንገኝ እንደመኾናችን መጠን፤ በዚያን ጊዜ የነበሩ ኩነቶች ኹሉ አኹንም አይኖሩም ማለት አይቻልም፡፡

በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም ቦታ ክፍተት አይፈጠርም ብሎ በሙሉ ሓላፊነት መውሰድ የሚችል ይገኛል ተብሎም አይጠበቅም፤ ነገር ግን የከፋና የባሰ ክፍተት እንዳይፈጠር የተጠናከረ ሥራ በመሥራት መከላከል የሚችሉ፣ በየጊዜው ኹሉ የተነሡ ታላላቅ አበው እንዳሉ እናስተውላለን፡፡

በዚኽ ዘመን የምንገኝ ኖሎትም ምንም ቢኾን ከዚህ እውነታ ውጭ መኾን አንችልም፤ መሠረታዊ ችግር ሊኾን የሚችለው ክፍተት ለምን ተፈጠረ የሚለው ሳይኾን ክፍተት መኖሩ እየታወቀ ዝም ብሎ መኖሩ ነው፡፡ በዚኽ ዙሪያ ይህ ዐቢይ ጉባኤ ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

እንደ እውነቱ ከኾነ በቤተ ክርስቲያናችን መሠራት የነበረባቸው፤ ኾኖም ግን እስከ አኹን በአጥጋቢ ኹኔታ ያልተሠራባቸው የሥራ መስኮች እንዳሉ ባይካድም ጥሩ ውጤት ያስመዘገብንባቸው ነገሮች እንዳሉም መዘንጋት የለበትም፤

በተለይም ሕዝበ ክርስቲያኑ ባለው አቅም ኹሉ ቤተ ክርስቲያኑን ለመደገፍና ለማልማት የሚያደርገው ቀና ትብብር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተሰፋ ሰጪ ኾኖ ይታያል፤

አንዳንድ አህጉረ ስብከትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሚያስደንቅ ሁኔታ የራስ አገዝ ልማት እያካሔዱ ለቤተ ክርስቲያናችን ተጨማሪ የሚኾን ትልቅ አቅም እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

ከኹሉም በላይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለማስፋፋት በዓለም ዙሪያ የተደረገው እንቅስቃሴ በአኹኑ ጊዜ ኹሉንም ክፍላተ ዓለም ማለትም ከምዕራብ አሜሪካ እስከ ጃፓን፤ ከአየርላንድ እስከ አውስትራልያ ቤተ ክርስቲያናችን ክንፎቿዋን የዘረጋችበት ኹኔታ የተፈጠረ በመኾኑ ትልቅ ስኬት ተገኝቶአል ማለት እንችላለን፤ ቤተ ክርስቲያናችንም ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ወደ መኾን አድጋለች፤ ማለት ይቻላል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

የቤተ ክርስቲያናችን ሥራ ሰፊና ዘርፈ ብዙ በመኾኑ አኹንም ቢኾን ትኩረት ተሰጥቶአቸው በቅድሚያ ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች እንዳሉ ማስታወሱ ተገቢ ነው፤ በመኾኑም፤

  • ቤተ ክርስቲያናችን ዘመኑን የዋጀ የአስተዳደር ጥበብ ተከትላ ሀብትዋና ንብረትዋን መጠበቅ የሚያስችሏትን አሠራሮች መቀየስ፤
  • በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ሊዘጋጁ የሚገቡ ልዩ ልዩ ደንቦችን፣ ፖሊሲዎችንና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ሥራዎች ኹሉ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲኖራቸው ማድረግ፤
  • ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረውንና እስከ አኹን በይደር የቆየውን የመሪ ዕቅድ እና የሚዲያ ጥናት በዚህ ዓመት በጀት ተይዞለት በአፋጣኝ ሥራ ላይ ማዋል፤
  • የምእመናንን ፍልሰት ለማስቆም መልካም አስተዳደርን በማስፈን ስብከተ ወንጌልን ማጠናከር፤
  • በውጭ ሀገሮች የሚገኙ አድባራት ከእናት ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ትስስር ማጠናከር፤
  • በኹሉም አቅጣጫ የልማት ሥራዎችን በማስፋፋት ቤተ ክርስቲያናችንን በኢኮኖሚ የበለጸገች ማድረግ፤
  • የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ የኾኑ ሕፃናትና ወጣቶች በሰንበት ት/ቤት በስፋት እየተደራጁ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ተገንብተው እንዲያድጉ ማድረግ፤
  • ለአብነት ት/ቤቶችና ለገዳማት የሚደረገውን ድጋፍ በማሳደግ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግና በመሳሰሉት ሥራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራባቸው ሥራዎች ሊኾኑ ይገባል፡፡
  • በሌላ በኩል በዚህ ዓመት በሀገራችን በተከሠተው የዝናም እጥረት ምክንያት፣ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ድርቅ እንደተከሠተና የምግብ እጥረትም እንዳጋጠመ፣ በሠላሳ አራተኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቀረቡ የየአህጉረ ስብከቱ ሪፖርቶች ለመገንዘብ ተችሎአል፡፡
  • በመኾኑም ለወገን ደራሽ ወገን ነውና በተለመደው ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ባህላችን መሠረት፣ ሕዝቡ ካለው እየከፈለ የተጎዱ ወገኖችን እንዲረዳ ከማስተማርና ከማስተባበር በተጨማሪ፣ የሕዝብ እናት የኾነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን አቅሟ የሚችለውን ኹሉ ታደርግ ዘንድ፣ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በጉዳዩ መነጋገር አለበት፡፡

በመጨረሻም፤ ይህ ሐዋርያዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ዐቢይ ጉባኤ፤ ሐዋርያዊት፣ ህልውተ ኵሉ፣ አንዲትና ቅድስት የኾነችው ቤተ ክርስቲያናችን በኹሉም አቅጣጫ የተሟላ፤ የተስተካከለና ከክርስቶሳዊ አስተምህሮዋ ጋር የሚጣጣም አሠራር እንዲኖራት ከላይ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ጉዳዮች አንሥቶ በመወያየት ጠቃሚ ውሳኔዎችን ያሳልፍ ዘንድ በማሳሰብ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 164 በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የ2008 ዓ.ም የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን ባርከን ከፍተናል፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤችንን ይባርክ፤ ይቀድስ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ