የዶ/ር አክሊሉ ሐብቴ ቡድን በዕርቀ ሰላም ስም ጊዜ ለመግዛት ማሰቡ ተገለጸ

የዲሲ ማርያም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክን በህገወጥ መንገድ ተቆጣጥሮ የሚገኘው  የዶ/ር አክሊሉ ሐብቴ ቡድን በዕርቀ ሰላም  ስም ጊዜ ለመግዛት እየተሯሯጠ  መሆኑን ምንጮቻችን ጠቁመውናል። በተለዋጭ ዳኛ የጊዜያዊ እገዳ (Temporary Restraining Order) ለማድረግ ቀጠሮው October 30, 2015 ስለሆነ ዕለቱ እስኪደርስ ድረስ ከተቻለ የቤተክርስቲያኗ ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ ማዕምራን ዶ/ር ቀሲስ አማረ ካሣዬ ወደ ቀድሞው ስራቸው እንደመለሱና፣  ምክትል አስተዳዳሪውም አብሯቸው እንዲሰራና አንድ ሌላ ገለልተኛ ግለሰብም አብሮ እንዲጨመር  የሚል የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦ እንደነበር ታውቋል ። ነገር ግን ሁለቱ ቡድኖች በዚህ ሐሳብ ላይ ካልተስማሙ ቤተክርስቲያኗ ፍርድ ቤት ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ትዘጋለች የሚል ውሳኔም ነበር።

በአንድ በኩል ቤተክርስቲያኗ ከተዘጋች የበላይነት እንደሚያጡ የተሰማቸው፣ በሌላ በኩል ግን ማምለጫ ያጡት የአድመኞች ቡድን በእርቀ ሰላም ስም ለማምታት አዲስ መሯሯጥ እንደጀመሩ ማምሻውን የደረሰን ዜና ያመለክታል።ምናልባት ሕጋዊ የሆነው የደ/ሰ/ቅ/ማ/ቤ/ክ የባለአደራዎች ቦርድ በዚህ ሁኔታ እርቅ አላደርግም ቢልና ቤተክርስቲያኒቷ ብትዘጋ አሁንም ቦርዱን ለመወንጀል የአቶ አዲሱ አበበ፣ የዶ/ር አክሊሉና የመምህር ተስፋዬ መቆያ ቡድን እየተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጾልናል ። ይህ አካሄድ የቤተክርስቲያንኗን በር ሰብሮ የተቆጣጠረው የነአዲሱ አበበ ቡድን የበላይነትና ተሰሚነት ይዞ ለመቆየት የሚያደርገው እንደሆነና ብዙ ቦታ የወያኔ የሚያደርጋቸውን የማወናበጃ ስልቶች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው የሚሉም አሉ።

የቤተክርስቲያኗ የባለአደራዎች ቦርድ በዚህ ሁኔታ በሚደረገውን ወያኔያዊ የማጭበርበሪያ ዘዴ ይታለላሉ ተብሎ ባይጠበቅም በምዕመናን ላይ የስነ ልቡና ጫና ለማሳደር  ያስችል ይሆናል የሚሉም አልታጡም። በዚህም መሠረት የነዶ/ር አክሊሉ ሐብቴ  ቡድን በእጅ አዙር የወያኔ ምክርን የሚከተሉ ሰዎችን ይዘው ቀጥለዋል እየተባለ በመነገር ላይ ነው። በእርግጥ እነዶ/ር አክሊሉ ሀብቴ የገቡበት የህግ አጣብቂኝ ያልጠበቁት ሁኔታ እንደሆነባቸውና  ጉዳዩም የወንጀል ክስ ስለሆነ በቀላሉ አጣጥለውት ሊያልፉት ያልቻሉ እንደሆነ ተገልጿል። በመምህር ተስፋዬ መቆያ የተደራጁ አንዳንድ ምዕመናን የሚናገሩት አፀያፊ ቃላቶች እጅግ አሳፋሪዎች መሆናቸውንና እነዚህን ተሳዳቢዎች ፍርድ ቤት ድረስ ነጭ አስለብሰው ያሰማሯቸው መሆኑን ተረጋትጧል። ከዚህም በተጨማሪ መፈንቅለ-ቦርድ ያካሄደው ቡድን አዳዲስ ሰዎችን የቤተክርስቲያን አባል ሁኑ በማለት በማስጨነቅ ላይ እንዲሆነና በከፍተኛ ርብርቦሽ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንና ለመመዝገብ ፍቃደኛ ያልሆኑ ምእመናን ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳረፍ ላይ መሆኑን ተገልጾልናል። በዚህች ደብር  ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃዎች እንዳገኘን የምናቀርብ መሆናችንን እንገልጻለን።