ዘመናዊው ሰው ከኢትዮጵያ ቻይና፥ 80 ሺህ ዓመታት

በሣይንሳዊው መላ ምት ዘመናዊው የሰው ልጅ ምድር ላይ ተገኘ የሚባለው ከዛሬ 200,000 ዓመት በፊት ነው። ይኽ በሣይሳዊ አጠራሩ ሆሞ ሳፒያንስ (Homo Sapiens)፥ በላቲን ትርጓሜው ደግሞ «ጥበበኛው ሰው» አለያም «አዋቂው ሰው»፣ «ብልሁ ሰው» የሚል ስያሜ ያገኘው ዘመናዊ ሰው ምንጩ ከአፍሪቃ ብሎም ከኢትዮጵያ እንደሆነ ይነገራል።
ዘመናዊው ሰው ከአፍሪቃ ወደ ሌሎቹ ክፍላተ-ዓለማት መቼ ፈለሰ? በቅርቡ ቻይና ውስጥ የተደረገ የቅሪተ-አካል ምርምር «ጥበበኛው ሰው» ከምሥራቅ አፍሪቃ ፈልሶ አውሮጳ ከመድረሱ አስቀድሞ ቻይና መግባቱን ጠቁሟል። ይህ የሰው ዘር ከአፍሪቃ በቅርቡ የምትገኘው አውሮጳን ትቶ ስለምን ወደ ሩቅ ምሥራቋ ቻይና ተሻገረ? ጥያቄዎቹ በዚህ አያከትሙም።
«ጥበበኛው ሰው» አንዳንዴም «ዘመናዊው ሰው» ይሉታል፤ አሁን በምድር ላይ ከሚገኘው የሰው ልጅ የዘር ሐረግ ጋር ተመሳሳይ የሆነውን የሆሞ ሳፒያንስ ዝርያ። ዘመናዊው ሰው ከአፍሪቃ ተነስቶ እስያ ከመድረሱ በፊት አውሮጳ ሰፍሮ ነበር የሚለውን መላ ምት የሚሽር የሰው ልጅ ቅሪተ-አካል ባለፈው ሣምንት ቻይና ውስጥ ተገኝቷል። የቅሪተ-አካል ተመራማሪዎች 80 ሺህ ዓመታት ያስቆጠሩ ጥርሶችን ካገኙ ወዲህ ዘመናዊው ሰው አውሮጳ ከመድረሱ ከእጥፍ ዓመታት በፊት እስያ ውስጥ መገኘቱን ደርሰንበታል ብለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኘው ክሊቨላንድ የተፈጥሮ ሣይንስ ቤተ-መዘክር፥ በሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ፦ ዘመናዊው ሰው ቻይና ውስጥ መገኘቱ የታወቀው በምንድን ነው? Listen