ገብሩ አስራት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያወጣው መግለጫ ገለልተኛ አይደለም አሉ

የወያኔ አገዛዝ ያቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ትላንት ባወጣው መግለጫ ሂውማን ራይትስ ዎች የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች የተቃወመ ሲሆን ኢትዮጵያ ከለጋሽ ሀገራት ዕርዳታ እንዳታገኝ በማሰብ የተደረገ እንደሆነም አስታውቋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የወቅቱ የመድረክ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መበት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ እንደማይስማሙ ገልጸዋል፡፡ አቶ ገብሩ ተቋሙ ከዚህ በፊትም በተለያዩ ሁኔታዎች ተፈትኖ ገለልተኛ አለመሆኑ የተረጋገጠ በመሆኑ መግለጫው እንዳላስገረማቸው አስረድተዋል፡፡ የመድረኩ ሊቀመንበር የተቋሙን ነጻ አለመሆን ለማሳየት በማስረጃነት ያስቀመጡት ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት የአረና ፓርቲ አባል ግድያን በተመለከተ ጉዳዩን አጣርቼ አቀረብኩ ያለበትን ለመንግስት የሚወግን ሪፖርት ነው፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎች በበኩሉ በዚህ ሳምንት ይፋ ባደረገው ባለ 668 ገጽ ሪፖርት ባለፈው አመት በኢትዮጵያ የነበሩ ክስተቶችን ሲዘረዝር መንግስት መራጮች ገዢውን ፓርቲ እንዲቀላቀሉ ወይም እንዲደግፉ የተለያዩ ጫናዎችን ያደርግ እንደነበር፣በተጠቀሰው አመት ብቻ 15 ያህል ጋዜጠኞች ሀገር ጥለው መሰደዳቸውንና ዛሬም በርካቶች ያለ አግባብ በእስር ላይ እንደሚገኙ መግለጹ ይታወቃል፡፡