ኢ.ቢ.ኤስ: ሃይማኖታዊ የቲቪ ፕሮግራሞች የታደሰ ፈቃድ እንዲያስገቡ አስቸኳይ ትእዛዝ ሰጠ
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ 16 ቁጥር 821፤ ቅዳሜ መስከረም 29 ቀን 2008 ዓ.ም.)
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ(ኢቢኤስ)፤ በሳምንት አንድ ቀን በጣቢያው መንፈሳዊ ዝግጅት የሚያስተላልፉ ሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች፣ የታደሰ የፈቃድ ማስረጃዎቻቸውን እንዲያስገቡ አስቸኳይ ትእዛዝ ሰጠ፡፡
የቴሌቪዥኑ ፕሮግራሚንግ ኮሚቴ መስከረም 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ለአራት የሃይማኖታዊ ፕሮግራም ክፍሎች በጻፈው ደብዳቤ፤ ከጣቢያው ጋር በገቡት ውል መሠረት ለሚወክሉት የሃይማኖት ተቋም ወይም የሃይማኖት ትምህርት ለመስበክ ያስፈቀዱበትን ወይም እያደረጉ የሚገኙትን አገልግሎት የሚደግፍ የታደሰ ፈቃድ ወይም ደብዳቤ በአስቸኳይ እንዲያቀርቡለት ጠይቋል፡፡
የታደሰ ፈቃድ ወይም ደብዳቤ እንዲያስገቡ የታዘዙት÷ ታዖሎጎስ፣ ቃለ ዐዋዲ፣ ማኅበረ ቅዱሳን እና ኤንሼንት ዊዝደም የተባሉ አራት ፕሮግራሞች ሲኾኑ ተቋሞቻቸው ከሚመለከተው የመንግሥት ይኹን የሃይማኖት አካል ለአገልግሎታቸው ይኹንታ ያገኙበትን የታደሰ ፈቃድ ወይም ደብዳቤ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት እትማችን፣ “በታዖሎጎስ እና ቃለ ዐዋዲ የኢ.ቢ.ኤስ ፕሮግራሞች ላይ ተቃውሞ ተነሣ” በሚል ርእስ፣ ፕሮግራሞቹ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ እና ክብር የሚጋፉ በመኾናቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም እንዳጠቀሙ የሚቀሰቅስ የሕዝባዊ ተቃውሞ ድጋፍ ፊርማ በመሰብሰብ ላይ መኾኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል በስም ተጠቃሾቹ የሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች አዘጋጆች፣ በወጣው ዘገባ ላይ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡