እስከመቼ ስደት …እስከመቼ በባዕድ ሀገር ሞት
ከኤልያስ ገብሩ
አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌን በአካል አላውቀውም፤ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሕይወት ግን ስማቸው ገንኖ ከወጡ ሰዎች መካከል በቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፍ መሆኑን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ የሞቱን መርዶ፣ አርአያ ተስፋማርያም በፌስ ቡክ ገጹ ጽፎት ካረዳን ጀምሮ፣ በምናቤ ሙሉጌታን ማሳላሰሌ አልቀረም፡፡ ድንገተኛ ሞቱ ልብ ይነካል፤ ከውድ ሀገር ርቆ መሞት ደግሞ ልብ ይሰብራል!!! ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ ስለሙሉጌታ የተለየ የአጻጻፍ ዘዬውን ትናንት ጽፎት ያስነበበንን ሀሳብ በተመስጦ ነበር አንብቤ የጨረስኩት፡፡ አንጋፋውን ጋዜጠኛ በአካል የሚያውቁት፣ በየራሳቸው መንገድ የገለጹትን አንብቤ ለመረዳት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በተከታታይ በተሰበረ የሀዘን ስሜት፣ ስለሙሉጌታ የጻፈቻቸውን ሀሳቦች ሳነብ፣ በአዕምሮዬ ወዲያው የመጣው ባለቤቷ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ነበር፡፡ እስክንድር፣ ከቃሊቲ እስር ቤት ሆኖ የሙያ አጋሩን ሞት ሲሰማ ምን እንደተሰማው ማወቅ መሻቴ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል? እስኬውን መጠየቅ አይቻልም፤ እስክንድር ስለሙሉጌታ የሚያስበውን ሀሳብ መረዳት አልቻልንም! ዕድሜ ለዚህ ክፉ አገዛዝ!!!

…ዛሬም ከግማሽ ሰዓት በፊት፣ የቀድሞ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ፣ የአሁኑ የኢሳት ዘጋቢ ጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማ፣ በፌስ ቡክ ገጹ የአንጋፋውን ጋዜጠኛ የመጨረሻ የአስከሬን ስንብት ፎቶግራፍ አንስቶ አሳየን፡፡ ይህንን ስመለከት፣ ከምር ልቤን አንዳች የሀዘን ስሜት ዳግም ወረራት፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት አንዱ እጣ-ፈንታ ይህ መሆኑ በግልጽ በገሃድ ታየኝ፡፡ አዘንኩ! በስደት ሀገር ኬንያ ታሞ የሞተውን፣ አስከሬኑ የተንገላታውን ወዳጃችን ጋዜጠኛ ሚሊዮን ሹሩቤንም አሰብኩት፤ ይህም ሌላ ሀዘን ነበር፡፡
…እስከመቼ ስደት …እስከመቼ በባዕድ ሀገር ሞት … እስከመቼ መንገላታት …እስከመቼ ሀዘን …ዛሬ መመለስ ያልቻልኩት ነገር ግን፣ አንድ ቀን በትክክል የምንመለሰውን ጥያቄ ለራሴ ጠየኩ፡፡
ጋሽ ሙሉጌታ፣ ፈጣሪ ነፍስህን በገነት ያኑረው!!!