እናት ኢትዮጵያ አደይ ኤርትራ
ከአንተነህ መርዕድ (ሚያዝያ 2007)
መሳይ መኮንንና ፋሲል የኔዓለም ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉዞ የብዙ ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም የኤርትራውያን ወንድምና እህቶች ቀልብ መሳቡ እሙን ነው። በተለይም የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቃለ መጠይቅ በብዙ መልኩ አስደምሞናል። እድላችን የተቆራኘነውና መነጋገሩና መብሰልሰሉ የሚገባ በመሆኑ ያለፍንበትን ሁሉ በትዝታ እንድፈትሽና አሁን የደረስንበትን እንዳይ ምክንያት ሆኖኛል። ነገሮችን ውስብስብና አጠቃላይ ከሆነ መልኩ ይልቅ ተጨባጭ ከሆኑ የግል ገጠመኞች ዙርያ ማውጋቱ የበለጠ ጉልህ ያደርገዋልና አንባቢዎቼም የራሳችሁ ገጠመኝ ዙርያ እየተሽከረከራችሁ የእኔን እንድትካፈሉ እጋብዛለሁ። በዚህ መልኩ ከምን ተነስተን የት እንዳለን ይታየናል።