ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ማክሰኞ መስከረም ፳፭ ቀን ፪ሺህ፰ ዓ.ም. ቅፅ ፬ ፣ ቁጥር ፪ ግልጽ ደብዳቤ

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ማክሰኞ መስከረም ፳፭ ቀን ፪ሺህ፰ ዓ.ም. ቅፅ ፬ ፣ ቁጥር ፪

ግልጽ ደብዳቤ
ለምንድን ነው «እንኳን በሰላም ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ» የምንባባለው? በሰላም ኖረን፣ሰላምን አጣጥመናት እናውቃለን ወይ?
• ለኢትዮጵያውያን ልዩ ልዩ የኃይማኖት ተቋሞች፣
• በኢትዮጵያ ስም ለተደራጁ የፖለቲካ እና የሲቪክ ድርጅቶች፣
• ለወገናችን የኢትዮጵያ ሕዝብ፤
በያላችሁበት፦
እንደ ባህል ሆኖ በዘመን መለወጫ ዋዜማ እና ማግስት፤ መንግሥታት፣ የመንግሥታት ልዩ ልዩ ተቋሞች፣ የኃይማኖት ድርጅቶች፣ የፖለቲካ እና የሲቪክ ማኅበሮች፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ተቋሞች፣ ቡድኖች እና ግለሰቦች የመልካም ምኞት መግለጫዎች ይለዋወጣሉ። ይህ መልካም መመኘት እና አዲስ ተስፋ ሰንቆ መጭውን ዘመን በሥራ የደስታ ምንጭ ለማድረግ መሻቱ በራሱ መልካም ነገር ነው። የሰው ልጅ ሕይዎት በተስፋ የተመላ ነውና ተስፋ መስጠቱ ተገቢ ነው።
ተስፋ ሲሰጥ ግን፣ ባለፈው አሮጌ ዘመን ያጋጠሙ እና ለተከታዩ አዲስ ዘመን ደንቀራ የሆኑ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሮአዊ የሆኑ ችግሮችን እንደሌሉ በመቁጠር መሆን ያለበት አይመስለንም። ተስፋው ባለፉት ዘመኖች የገጠሙ ችግሮችን አውስቶ፣ እነዚህን ችግሮች እንዴት መቋቋም እንዳለብን ሁነኛ የመፍትሔ አቅጣጫ ጠቁሞ፣ ለሚቀጥለው አዲስ ዓመት ልንጨብጣቸው ያቀድናቸውን መልካም ተግባሮች አመላክቶ፣ ለእነዚህ ስኬታማ መሆን ሕዝቡ ተስፋውን አደንድኖ ለተግባራዊነታቸው በቆራጥነት እና በአንድነት እንዲቀሳቀስ ከፊቱ ብሩሕ ተስፋን ማመላከት ተገቢ እና መደረግ ያለበት፣ ተበረታትቶም መቀጠል ያለበት መልካም ባህል እንደሆነ እናምናለን።
ሆኖም በዘንድሮው ዓመት መግቢያ ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ (ከ፪ሺህ፯ ወደ ፪ሺህ፰ ዓ.ም.) በተደረገው ሽግግር የተላለፉ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች፣ እንዳለፉት የዘመን መለወጫ የመልካም ምኞት መግለጫዎች ሁሉ፣ ዕውነታውን ያመላከቱ ሆነው አላገኘናቸውም። የመልካም ምኞት መግለጫዎቹ የተላለፉት በተለምዶ እንደ ባህል ሆኖ፦ «እንኳን በሰላም ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ! እንኳን ከዘመነ ሉቃስ ወደ ዘመነ ዮሐንስ በሰላም አሸጋገራችሁ!» የሚሉ ሆነው እናገኛቸዋለን። የመልዕክቱ ችግር የሚመነጨው መልካም ከመመኘቱ ላይ ሳይሆን፤ «ሰላም» ከሚለው ቃል ላይ ያረፈ ነው። ምክንያቱም ባለፈው አሮጌ ዓመት ቀርቶ ባለፉት ፳፭(ሃያ አምሥት) ዓመታት በትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ምክንያት፣ ኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ለደቂቃም ቢሆን ሰላምን አገኝተው አያውቁም። ሕዝቡ የማኅበራዊ ደኅንነት ርሃብ እና ችግር አለበት፤ የብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት መጠበቅ ችግር እና ርሃብ አለበት፤ የዳር ድንበር እና የወደብ ችግር አለበት፤ የአንድነት እና የአብሮነት ጥማት አለበት፤ የመኖር እና በሰላም ወጥቶ የመግባት ከፍተኛ ችግር እና ርሃብ አለበት፤ የጤና ማጣት ችግር አለበት፤ የትምህርት ማጣት ችግር አለበት፤ በመሪዎቹ የመታመን እና መሪዎቹን የማመን ችግር እና ርሃብ አለበት፤ የኃይማኖት ነፃነት ችግር አለበት፤ የመደራጀት፣ ኃሣቡን በነፃነት የመግለጽ፣ በፈለገው የሥራ መሥክ የመሠማራት፣ በመረጠው አካባቢ የመኖር፣ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የመመካት እና የመኩራት ጥማት እና ርሃብ አለበት፤ በአገሩ የመኖር እና የመሥራት ችግር አለበት፤ ከሁሉም በላይ የሰላም ማጣት ርሃብ አለበት። እነዚህ እና መሠል ችግሮች ትናንት አሮጌ ብለን በሸኘነው ዘመን ብቻ ተገድበው የቀሩ ሳይሆን፣ ዛሬ አዲስ ብለን በተቀበልነው ዘመን በከፋ መልኩ የተሸጋገሩ ችግሮች ናቸው። እነዚህን ችግሮች ሳናነሣ፣ መወገጃ ስልቱንም ሳናመላክት፣ በድፍኑ እንኳን «በሰላም» አሸጋገራችሁ ማለት ሰላምን ይፈጥራል ወይ? መጭው ዘመንስ እንደተመኘነው የሰላም ይሆናል ወይ?
ከሁሉም በላይ ሌሎቹን ዓመታት ትተን፣ ያለፈውን ፪ሺህ፯ ዓ.ም. እንኳን ብንወስድ ዘመኑ ለኢትዮጵያውን የመከራ እና የችግር ዘመን እንደነበር እንረዳለን። ወገኖቻችን በአገራቸው ሠርተው የመኖር መብታቸው ባለመከበሩ ምክንያት ለመኖር ሲሉ በሚያደርጉት መሰደድ አያሌዎች የበረሃ አውሬዎች እና የውቅያኖስ ዓሣ ነባሪዎች ቀለብ የሆኑትን ትተን፤ በሣውዲ ዓረቢያ፣ በሊቢያ እና በደቡብ አፍሪቃ ይኖሩ በነበሩ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመው ግድያ እና ድብደባ ዓለምን ያስለቀሰ፣ ኢትዮጵያውያንን ያሣዘነ፣ የኢትዮጵያዊነት ውርደትን ያመላከተ እንደነበር ማንም ይዘነጋዋል አይባልም። አገራችን ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ስደተኞች ተቀብላ ያስተናገደች፣ ለኃይማኖቱ መቀጠል መሠረት የሆነች፣ በዚህም ነቢዩ መሐመድ ራሳቸው «ኢትዮጵያውያንን አትንኩ» ያሉትን ኃይማኖታዊ ቃል ሽረው፣ የሊቢያ የአክራሪ እስልምና ተከታዮች በወገኖቻችን ላይ የፈጸሙት ግፍ የተሞላበት ግድያ አገራችን የገባችበትን የውርደት አዘቅት ጥልቀት የሚያመላክት ነው። ኢትዮጵያውያን በዓለም አደባባዮች ደረታቸውን ነፍተው፣ አንገታቸውን አቅንተው እንዳልተራመዱ ሁሉ፣ ዛሬ በትግሬ-ወያኔ ዘመን በየሄዱበት የዓለም ክፍል ሁሉ ተዋራጆች፣ ተሰዳቢዎች እና የተናቁ እንደሆኑ በየቦታው የሚደርስባቸው በደል በግልጽ ይናገራል።
ለዓለም ጥቁር ሕዝብ የነፃነት ምሣሌ፣ የኃይማኖት መምህር፣ የጀግንነት አርማ እንዳልነበርን፣ ዛሬ በዚህ ዘረኛ አገዛዝ ሁሉም ነገር ተረት ተረት የሆነ ይመስላል። የአሁኑ ዘመን ኢትዮጵያውያን የዘመናዊ ባርነት ተሸካሚዎች፣ ኃይማኖት የለሾች እና ፈሪዎች ሆነን እንድንቆጠር ሆነናል። ስደት፣ ርሃብ፣ ጦርነት፣ በሽታ፣ ሞት እና ውርደት መለያችን ሆኗል። ይህን ሁሉ መከራ ተሸክመን እንዴት «በሰላም ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ» ማለት ይቻለናል?
የትግሬ-ወያኔ ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖትን ለማጥፋት ባለው ሠፊ ዕቅድ መሠረት፣«ፓትርያርክ በሕይዎት እያለ ሌላ ፓትርያርክ አይሾምም» የሚለውን የኃይኖቱን ቀኖና ሽሮ፣ በዘር ላይ በተመሠረተ ምርጫ ሌላ ፓትርያርክ በመሾም፣ የኃይማኖቱ ተከታዮች ከሁለት እንዲከፈሉ አድርጓል። የሾማቸው አባ ጳውሎስ በአምላክ ፈቃድ ሲነሱ፣ ስሕተቱን በማረም ፈንታ በማን አለብኝነት አሁንም ሌላ ትግሬ ፓትርያርክ ሾመ። አዲሱ ተሿሚ አባ ማትያስ፣ በአቡነ ተክለኃይማኖት ለጵጵስና የበቁ ነበሩ። ሆኖም በፈጸሙት የዝሙት ተግባር በሾሟቸው ፓትርያርክ በአቡነ ተክለኃይማኖት ተወግዘው የጵጵስና ማዕረጋቸውን የተገፈፉ መሆናቸውን ይታወቃል። ውግዘቱን ንሥሐ ገብተው ሣያስነሱ እና ጵጵስናቸው ሳይባረክ፣ አሁንም ባላቸው የዘር ትሥሥር ምክንያት ፓትርያርክ እንዲሆኑ በማድረግ ቤተክርስቲያኗ የነበራትን ክብር እና ዝና ጠብቃ እንዳትዘልቅ አድርጓል፤ ኃይማኖቱን አዳክሟል፤ ለብጥብጥ እና ለመናቆር ሠፊ በር በመክፈት አማኙን ሆድ እና ጀርባ እንዲሆን አድርጓል። ይህ ኃይማኖታዊ ሰላምን ከመንሣቱም በላይ በአብሮነትን እና በኢትዮጵያዊነት ላይ መለያየትን እና መነጣጠልን አስፍቷል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ነባሩን የእስልምና ኃይማኖት ሥርዓት በኃይል ለማፍረስ ከኃይማኖቱ ሥርዓት ውጭ መሪዎቹን ራሱ በመምረጥ የ«መንግሥት» ተቀጥላ አድርጓል። የኃይማኖቱ ተከታዮች «ኃይማኖታዊ ሥርዓታችን ይጠበቅ» ብለው ላቀረቡት ሰላማዊ አቤቱታ ሕጋዊና ተገቢ የሆነ መልስ በመስጠት ፈንታ፣ የሰጠው መልስ አፈና እና እሥራት ነው። የኃይማኖቱ ተከታዮች ጉዳያቸውን እንዲያስፈጽሙ እና ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝ የወከሏቸውን «የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ» አባሎችን ለረጅም ወራት አስሮ የቁም ስቅል ካደረሰባቸው በኋላ፣ ከ፯(ሰባት) እስክ ፳፪(ሃያ ሁለት) ዓመት በሚደርስ የእሥር ዘመን ፈርዶባቸዋል። ይህም የነባሩን የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ከማሣዘን አልፎ ያስመረረ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ እንዴት ተብሎ «በሰላም» አደረሳችሁ ያስብላል?
በከተሞች ያለው ሕዝብ የዕለት ምግቡን የሚመገበው በወረፋ ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል። የተወሰኑት የቤተሰብ አባሎች ምሳ ከበሉ ራት አይደግሙም፤ ቁርስ የሚታሰብ አይደለም። ይህ እንግዲህ ገቢ አላቸው የሚባሉት ናቸው። አብዛኛው ሥራ-አጥ ሠራዊት አፉን የሚያሟሸው «ሣላይሽ» በምትባል በጨለቆት በምትጎረስ አንዲት ጉርሻ ነው። የዚህች የሣላይሽ አንዲት ጉርሻ መገኛዋም ከታላላቅ ሆቴሎች፣ ከቤተክርስቲያኖች ዘኬ፣ ከልዩ ልዩ ድግሶች ወደ ቆሻሻ ገንዳዎች ከሚጣለው ትርፍራፊ ምግብ የተሰበሰበው መሆኑን ስንገነዘብ ደግሞ ሕዝባችን የገባበትን የረሃብ መጠን እና ስፋት የቱን ያህል ከባድ እንደሆነ መረዳት አይገድም። እህል ከሰማይ ርቆ፣ ሆድ እህል እየሻተ፣ ዓይን እህል እየናፈቀው፣ መሶቡ እንጀራ፣ ሙሐቻው ሊጥ አልባ ሆነው ድር አድርቶባቸው፣ እንግዳ ተቀባይ የነበረው ሕዝብ በማጣቱ ምክንያት እንግዳ ሆኖ፣ «ግቡ ቡና ጠጡ ለምን ትላላችሁ፣ ግቡ ቁርስ ብሉ ለምን ትላላችሁ፣ እህል ክንፍ አውጥቶ ሲበር እያያችሁ፤» የሚለው ዜማ ከሁሉም ሰዎች አንደበት በሚደመጥበት ዘመን ላይ ቆመን፤ «እንኳን በሰላምና በጤና ከዘመን ዘመን አሸጋገረህ» ማለት ይቻላል ወይ? ርሃብ ሰላም ከማሣጣት አልፎ ሕይዎት የሚቀጥፍ አይደለም ወይ? እየተራቡ ሰላም አለ ማለት ይቻላል ይሆን?
ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ዳብሮ መቀጠል፤ ኃይማኖትን ከባህል፣ ቋንቋን ከጽሕፈት፣ አገዛዝን ከሕግ፣ ነፃነትን ከመስዋዕትነት፣ ፍቅር እና አብሮነትን ከትሕትና እና ከይሉኝታ ጋር ለንቅጦ እና አዋህዶ የሰጠን ታላቁን የዐማራ ነገድ፤ በኢትዮጵያ ተፈጠሩ ለሚባሉ ያለፉ ዘመናት ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ በማድረግ፣ ከምድረ-ገጽ እንዲጠፋ በተከፈተበት የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ወንጀል ባለፉት ፳፭(ሃያ አምሥት) ዓመታት ከ፭(አምሥት) ሚሊዮን ያላነሰ ጠፍቶ፣ ተገድሎ፣ ተሰድዶ እና ታስሮ በምን ታምር የዚህ ነገድ ተወላጆችን በ«ሰላም» አሸጋገራችሁ ለማለት ይቻላል? ከዚህም በተጨማሪ በ፪ሺህ፯ ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ ወያኔ መቶ በመቶ የማሸነፍ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ በከፈተው ዘመቻ አያሌ ሰዎችን ገድሏል፤ አስሯል፤ አንገላትቷል። በዚህም መሠረት በመተከል ዞን፣ በቡለን እና በወምበራ ወረዳዎች ይኖሩ ከነበሩ ዐማሮች መካከል 180 እንዲገደሉ፣ 224 ቀያቸውን ለቀው እንዲባረሩ ተደርጓል። በጣም የሚዘገንነው ደግሞ የተገደሉት 180 ዐማሮች ከመሰለባቸው በተጨማሪ ሥጋቸው ተጠብሶ እንዲበላ ተደርጓል። ከመበላት የተረፈው ቅሬተ-አካላቸው ካለመቀበሩም በላይ፣ የአካላቸው ልዩ ልዩ ክፍሎች ለከበሮ መምቻ እንዲውሉ ተደርጓል። ይህን ድርጊት ያዩ፣ ሥቃዩን የተቀበሉና የሰሙ ሰዎች በውስጣቸው ምን ዓይነት ሰላም እና ጤና ይኖራቸዋል ተብሎ ታስቦ «እንኳን በሰላም ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ» ይባላል? የችግሩ ሰለባ ለሆኑ እና እውነተኛ ሰብአዊነት ለሚሰማቸው ሰዎች ይህ ከመልካም ምኞቱነቱ ይልቅ ምፀትነቱ ያደፋል።
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት በኢትዮጵያዊነት ስም ለተደራጁ የኃይማኖት ተቋሞች፣ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ለወገናችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን ግልጽ ደብዳቤ የሚጽፈው፣ ሁሉም ማለት በሚቻልበት ደረጃ፣ ባለፉት ዘመናት በሕዝቡ ላይ፣ በተለይም በዐማራው ነገድ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጽዳት ዘመቻ «ለምን? እንዴት?» ብሎ በመጠየቅ ሁኔታውን ለማስቆም ከመጣር ይልቅ፣ የድርጊቱ ተባባሪ በሚያስመስል መልኩ፣ ሁሉም ምንም ነገር እንዳልተደረገ በመቁጠር የዝምታቸው መድምም ከመክበዱ በላይ፣ «እንኳን በሰላም አደረሳችሁ» የሚለው ስላቅ በዐማራው ቁስል ላይ ጨው የተነሰነሰበት ያህል ሆኖ ስለተሰማን ይህን ቅሬታችን ለመግለጥ ነው።
መንግሥት የሚኖረው ሕዝብ ሲኖር ነው። ኃይማኖቶች የሚኖሩትም የእምነቱ ተከታይ ሕዝብ ሲኖር ነው። የፖለቲካ እና የሲቪክ ድርጅቶችም የሚኖሩት እንወክለዋለን የሚሉት የማኅበረሰብ ክፍል ሲኖር ነው። በጥቅሉ ሕዝብ ከሌለ መንግሥት የለም፤ ኃይማኖት አይኖርም፤ የፖለቲካም ሆነ የሲቪክ ድርጅቶች ካለ ሕዝብ መኖር የሚታሰቡ አይደሉም። ስለሆነም ለሕዝብ ሕልውና እና ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀስ የሁሉም ተግባር ሊሆን ይገባል ብለን እናምናለን።
መንግሥት ካለታክስና ግብር መኖር ፈጽሞ አይችልም። የታክስ እና ግብር ምንጩ ደግሞ ሕዝብ ነው። የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ በሕዝባችን ላይ የሚያደርሰው በደል የሚቆመው፣ «ዐወቅን፤ ተደራጀን» ያሉ ወገኖች ሕዝቡ መብት እና ግዴታውን አውቆ ለመብቱ መከበር በአንድነት እንዲቆም ማስተባበር እና ማደራጀት ሲችሉ ነው። የኃይማኖት መሪዎችም ከሕዝብ ጎን በመቆም የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ የሕዝብ መብት እና ጥቅምን እንዲያከብር መንፈሣዊ ተጽዕኖአቸውን ማሣደር ሲችሉ ነው። ሕዝቡ መብት እና ክብሩ ከተነካ የአገዛዙ ኅልውና መሠረት የሆነውን ግብር እና ታክስ «አንከፍልም» የሚል የእንቢተኝነት ኃይሉ የሚጠነክርበትን መንገድ ማስተማርና ማሳወቅ ሲችሉ ነው። ለሕዝቡ ሰላም፣ አንድነት እና አብሮነት መጠንከር እና መደርጀት ራሳቸው ከሕዝቡ ጋር ሰምና ፈትል መሆን ሲችሉ ነው። ይህን ሣያደርጉ ከቀሩ ለሕዝቡ ቆመናል የሚሉት በተግባር የማይገለጽ ቃል ብቻ ከመሆን አያልፍም። አንድ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም እና መብት የሚቆመውም፣ ሕዝቡ ከያዘው ኃላፊነት የሚያወርደው መሆኑን ሲያውቅ እና ሲረዳ ነው፤ ሕዝብ የሥልጣን ምንጭ መሆኑን ገዥዎች ሲያውቁ ነው። ይህን የማሳወቅ ኃላፊነት ያለባቸው ደግሞ፣ በስሙ የተደራጁ የፖለቲካ እና የሲቪክ ድርጅቶች፣ የኃይማኖት ተቋሞች ናቸው። መንግሥታዊ አካሎችም ሆኑ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ እንዲሁም የሲቪክ ማኅበራት የአዲስ ዘመንን ብሥራት ሲያውጁ መነሻ ማድረግ ያለባቸው ባለፈው አሮጌ ዘመን የገጠሙ ችግሮችን አውስቶ፣ በመጭው አዲስ ዘመን እነዚህ ችግሮች እንዲወገዱ፣ የሕዝቡ ሰላም እና ጤንነት በአዲሱ ዘመን በተሻለ መንገድ የሚጠበቅ መሆኑን የሚያሳይ ተስፋ ማሰነቅ እንጂ፣ ያለፈውን መከራ እና ስቃይ መነሻ ምንጩን፣ መወገጃ ስልቱን ሳያመላክቱ፣ የነበረውን ችግር እንደምንም ባለመቁጠር «እንኳን በሰላም አደረሳችሁ» ማለት በሕዝብ ብሶትና ችግር ላይ መሳለቅ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ይህ ችግርን ሣያወሱ መልካም ነገር መመኘት እንደጥሩ ባህል ተቀብለነው ከሆነም መታረም ያለበት አጉል ልማድ እንደሆነ ይሰማናል።
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ብዙዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ አስበውበትም ይሆን፣ ባለማሰብ የሚገፉትን ሃቅ በታሪካዊነቱ እና በዕውነትነቱ ከተደበቀበት ለማውጣት፣ የተጣለበትን አራሙቻ ለማንሳት፣ የተቀባውን ጥላሸት በመግፈፍ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪካዊ ሚናዋን በተሻለ እና በዳበረ መልኩ መወጣት የምትችልበትን መንገድ፣ የኃይማኖቱ መሪዎች እና የእምነቱ ተከታዮች ማድረግ ያለባቸውን በጋራ እንያደርጉ ድምፁን ያሰማል። በግልጽ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ኃይማኖት፣ ባህል፣ ሥነ-ጽሑፍ፣ ቋንቋ፣ የመንግሥት እና የሕዝብ አስተዳደር ውስጥ ሠፊ ሚና የነበራት መሆኑ ይታወቃል። ቤተክርስቲያኗ ቅብዓ-ቅዱስ ቀብታ ያላነገሠችው ንጉሥ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም ነበር። ቤተክርስቲያኗ ባላት ሕዝባዊ ድጋፍ እና ተቀባይነት፣ የኃይማኖቱ መሪዎች ያላመኑበትን መሪዎቹ ተግባራዊ ማድረግ ፈጽሞ አይችሉም ነበር። የኃይማኖቱ መሪዎች ሕዝብ ሲበደል፣ ፍትሕ ሲጓደል «ለምን? እንዴት?» በማለት ንጉሦችን አስጨንቀው በመያዝ ገዥዎች የሕዝቡን እና የኃይማኖቱን ፍላጎቶች ለማክበር ይገደዱ እንደነበር ታሪካችን ያወሳል። ቤተክርስቲያኗ ከሕግ እና ከሥርዓት ውጭ የሆኑ ንጉሦችን በማውገዝ ከኃላፊነታቸው ጭምር ታስወግድ እንደነበረ በዐፄ ሱስንዮስ ላይ የወሰደችው አቋም ሕያው ማስረጃ ነው። ዐፄ ዮሐንስ ፬ኛ ደርቡሾችን እዋጋለሁ ብለው፣ ነገር ግን እርሣቸው በጎጃም ሕዝብ ላይ ባወረዱት መዓት የተገረሙት የወቅቱ ግብፃዊ ጳጳስ አቡነ ሉቃስ «ደርቡሽን አጠፋለሁ ብለህ መጥተህ፣ አንተ በጎጃም ሕዝብ ላይ ደርቡሽ ሆንክበት» ብለው በመገሰጽ ዘግይተውም ቢሆን ከመጥፎ ተግባራቸው እንዲታቀቡ አድርገዋል። የዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ሕጋዊ ወራሽን ልጅ ኢያሱ ሚካኤልን ከሥልጣን ሽሮ በምትኩ ዘውዲቱ ምኒልክን ንግሥተ ነገሥታት፣ ራስ ተፈሪን ንጉሥ ብሎ ባሉ ሙሉ ሥልጣን እንደራሴ ያደረገው የ1909 ዓ.ም. የቤተመንግሥት መፈንቅለ መንግሥት፣ ያለ አቡነ ማቴዎስ እና እጨጌ ገድለጊዮርጊስ ተሳትፎ የሚታሰብ አልነበረም። ግዝቱን እነርሱ ባይፈቱ፣ ሕዝቡም ለአዲሶቹ ተሿሚዎች እንዲገዛ ቡራኬ ባይሰጡ፣ ለውጡ በቀላሉ ሊከናወን የሚችል አልነበረም። ይህ ሁሉ የሚያመለክተን ቤተክርስቲያኗ በሕዝቡ ውስጥ የነበራት ተቀባይነት እና ሚና የጎላ እንደነበረ ነው።
በዚያን ወቅት ቤተክርስቲያኗ በሕዝብ እና በባለሥልጣኖች ተደማጭ እና ተፈሪ የነበረችው የሚከተሉት ምክንያቶች ተሟልተው በመገኘታቸው ነው፦ መሪዎቿ መንፈሣዊነት ያልተለያቸው ስለነበሩ የሚናገሩት እና የሚሠሩት በሕዝቡ ዘንድ ያለአንዳች መጠራጠር ተቀባይነት ነበራቸው። መንፈሣዊ አባቶቹ የሚጨነቁት ለሰማያዊው ዓለም እንጂ፣ ለሥጋዊ ዓለም አልነበረም። ለምድራዊ እና ሥጋዊ ኑሮ ቦታ የሰጡ አልነበሩም። ሥጋዊ የሆነ የምግብ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት ፍራፍሬን ለቅመው፣ ሥራ-ሥርን ምሰው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ሰሌን እና ጥላ ሠርተው በመሸጥ ገቢ ያገኙ ነበር። ብራና ፍቀው እና አለስልሰው ለገበያ በማቅረብ ገቢ ያገኙ ነበር። መጽሐፍትን ጽፈው በመደጎስ፣ ከቅጠላቅጠል እና ሥራሥር ቀለማትን ቀምመው የሚያመርቱ፣ የነቢያትን እና የሰማዕታትን ሥዕሎች በመሣል ገቢ የሚያገኙ ስለነበር የመንግሥትም ሆነ የሕዝብ ቀጥተኛ ጥገኞች አልነበሩም። ከዚህ ሌላ እያንዳንዱ ገዳም፣ ደብር እና የአጥቢያ ቤተክርስቲያን እንደ ትልቅነቱ መጠን የሚተዳደርበት የራሱ ርስት እና የስሞን መሬት ነበረው። ይህም የኃይማኖቱ አባቶች ኃይማኖታቸው ለሚያዘው ዶግማ እና ቀኖና በጽናት እንዲቆሙ የውስጣዊ ኃይል ምንጫቸው እንዲሆን ማድረጉን መገንዘብ ይቻላል። በሌላ በኩል በጽድቅ እና ኩነኔ መኖር ከልብ የሚያምኑ በመሆኑ፣ «የኃይማኖቱን ቀኖና እና እና ዶግማ መሻር ወይም መቃወም ማለት ለገሃነመ እሣት ራስን ማጋለጥ ነው» ብለው ከምር ስለሚያምኑ፣ ለምድራዊ ኃይል ተንበርካኪዎች አልነበሩም። ይህ ግን ኢትዮጵያ ወደ ዘመናዊ አስተዳደር እና የተማከለ አገዛዝን መከተል ስትጀምር በነበረበት መልኩ መቀጠል አልቻለም።
የዚህም ምክንያቱ እንደ ኢትዮጵያ ያለ የረዘመ የኃይማኖት እና የመንግሥት ቁርኝት አንድነት የሌላቸው የምዕራብ አገሮች የበለጸገው ኢንዱስትሪያቸው ለሚሻው ሠፊ ገበያ የኃይማኖት እና መንግሥት ጥምረት እንቅፋት ሆኖ መገኘት፣ ይህን ቁርኝት ካልበጠሱ የእነርሱ ፍላጎት ዕውን ሊሆን እንደማይችል በመረዳት፣ በሥርዓተ ትምህርታቸው፣ በፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎቻቸው፤ በዲፕሎማሲ ሥራዎቻቸው ወዘተርፈ የመንግሥትን እና የኃይማኖትን መለያየት፣ የኃይማኖትን ዕኩልነት እና የማምለክ ነፃነትን መከበር እና መረጋገጥ እንዳለበት ሰበኩ። ዛሬ በምሥራቁ ዓለም በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ ከምዕራባውያን ጋር ለገጠመው ጦርነት መሠረታዊ መነሻው «የእስልምና ኃይማኖት ከመንግሥት ጋር ያለው ቁርኝት እና ዝምድና ይቋረጥ» በሚሉት ምዕራባውያን እና «መቋረጥ የለበትም» በሚሉት የእስልምና ኃይማኖት አባቶች መካከል ያለ ጦርነት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።
ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከቱርክ፣ የቱርክ ሳተላይት ከነበረችው ግብፅ የመሥፋፋት ዓላማ፣ ከፖርቹጊሶች ወረራ፣ ከጣሊያን ቅኝ ግዛት ራሷን ተከላክላ ማንነቷን አስጠብቃ የቆየችው፣ የመንግሥት እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖት ጥምረት የፈጠረው አንድነት የወለደው ጀግንነት መሆኑን የኢትዮጵያን የነፃነት ታሪክ በቅጡ የመረመሩ የሚስማሙበት ነው። ይህን ደግሞ ምዕራባውያን በሚገባ ከማወቃቸውም በላይ በ1888 ዓ.ም. ዐድዋ ላይ በተግባር አይተውታል። በ16ኛው መቶ ክፍለዘመን አባ እንድርያስ የተሰኙ መነኩሴ የቱርክ ተቀጥላ በመሆን የኃይማኖት ጦርነት ይመራ የነበረውን ማሕፉዝን አንገቱን በመቅላት ያሳዩት ጀግንነት ለትውልድ የሚረሳ ካለመሆኑም በላይ፣ የአገር ነፃነት ሲደፈር የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አባቶች እንደተራ ወታደር ለአገር ዘብ የሚቆሙ መሆኑን ያሳያል። ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. በቆየው የአምሥት ዓመት የአርበኝነት ዘመን አቡነ ጴጥሮስ እና አቡነ ሚካኤል ያሳዩት የጀግንነት ተጋድሎ የዚሁ ተከታታይነት መጠበቁን አመልካች ነው። ይህም የመንግሥት እና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥምረት፣ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትም ሆነ በእጅ-አዙር ቅኝ ግዛት ለመግዛት ለሚሹ ምዕራባውያን ኃይሎች የማይጨበጥ የጋለ አሎሎ ብረት እንደሆነባቸው ተረዱ። በመሆኑም የነዚህ ጥምረት ሳይፈታ፣ ኢትዮጵያን በፈለጓት መልክ እጅ ማድረግ እንደማይችሉ የተረዱት ምዕራባውያን በተለያዩ መንገዶች እንደ ኢትዮጵያ በመንግሥት እና በኃይማኖት መካከል የጠነከረ እና ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት የሌላቸውን አገሮች በምሣሌነት በማቅረብ፣ በሁለቱ ተቋሞች መካከል የነበረው የሰመረ ሰም እና ፈትል፣ ማግ እና ድር የነበረው አንድነት እና ግንኙነት ደረጃ በደረጃ እንዲላላ አስደረጉ። ለዚህም ፈር ቀዳጅ የሆኑት ዳግማዊ ምኒልክ ሆኑ።
ማንም ሊገነዘበው እንደሚችለው፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሰላምን ለማስፈን ሲሉ «ሁሉም ያባት ያባቱን ይያዝ፣ የአባቱን ኃይማኖት ይከተል» በማለት የኃይማኖቶች ዕኩልነት እንዲሰፍን አድርገዋል። ይህ ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በመንግሥታዊ አስተዳደር ላይ፣ ከሁሉም በላይ በነጋሢዎች ላይ ታሣርፍ የነበረውን መልካም ተፅዕኖዋ እንዲላላ መንገድ ጠርጓል። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም (ቀኃሥ) በበኩላቸው «ኃይማኖት የግል ነው፣ አገር የጋራ ነው!» በሚል መርሕ፣ ምኒልክ ኃይማኖቶችን እና ባህልን በተመለከተ የጣሉትን መሠረት ወርድ እና ቁመት እንዲጨምር አድርጓል። ተከታዮቹ መንግሥታት ደግሞ «ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል» እንዲሉ ሆኖ፣ መንግሥት እና ሃይማኖትን ከመለያየት አልፈው፤ ኃይማኖት እንዲጠፋ ዘመቻ ከፈቱ።
ዳግማዊ ምኒልክ እና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ መንግሥት እና ኃይማኖትን ለመለያየት የገፋፉዋቸው ዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ ሁኔታዎች ነበሩ። እነዚህ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የኢንዱስትሪ አብዮት ውጤቶች የሆኑት የሠፊ ገበያ እና ጥሬ ሀብት ፍለጋ ነበሩ። በግልጽ እንደሚታወቀው «የአውሮፓ መንግሥታት በመካከላቸው በኃይማኖቶች ሰበብ በሚነሱ ጦርነቶች በርካታ እና ተከታታይ ጦርነቶች ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህም ጦርነት የምርት ኃይሎችን፣ ሥልጣኔ እና ዕድገትን ከማውደም አልፎ፣ የሰውን ልጅ የሚያጠፋ በመሆኑ ለዕድገት ከፍተኛ ገቺ ኃይል መሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም ሥልጣኔን ለመቀዳጀት የእርሱ ጠንቅ የሆነው ጦርነት መወደግ ነበረበት። ይህንም ለማድረግ አውሮፓውያን በመካከላቸው የነበራቸውን ጦርነት በማስወገድ ለነፃ የሸቀጦች ዝውውር ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር እንዳለባቸው አመኑ። ለዚሁ ሥራ መቃናትም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተቀናቃኝ ሆኖ በአዲስ መልክ የተፈጠረው የፕሮቴስታንት ኃይማኖት በዓለም ላይ መስፋፋት ባስከተለው ተፅዕኖ ሳቢያ፣ በመንግሥት እና በኃይማኖት መካከል የነበረውን ግንኙነት በመሻር፣ ሁለቱ አካሎች እንዲለያዩ ማድረግ የተሻለ እንደሚሆን ታመነ። ይህ ለሸቀጦች ማራገፊያ ሠፊ ገበያ፣ ምርጥ እና ውድ ማዕድኖች እንዲሁም ርካሽ የሰው ጉልበት ለማግኘት ለሚሹ ምዕራባውያን የመንግሥት እና የኃይማኖት መለያየት ለሚያደርጉት ኃይማኖትን ሽፋን ላደረገ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ላልሆነ ወረራ ምቹ መደላድል ሆኖ እንዳገለገለ መገንዘብ ይቻላል።
በአገራችን በኢትዮጵያ ይህ በታሪካችን ረጅም ዘመን የዘለቀ የመንግሥት እና የኃይማኖት ቁርኝት በምን መልክ መቀጠል ወይም መቋረጥ እንዳለበት ከታሪክ፣ ከባህል፣ ከአንድነት፣ ከቋንቋ፣ ከአገር ሉዐላዊነት እና ነፃነት ጋር የነበረው እና ሊኖረው የሚገባ ግንኙነት በአግባቡ ሳይፈተሽ፣ ምርቱ ከግርዱ ሳይለይ፣ በተማሪዎች ጫጫታ እና ኹከት፣ ቀደም ብሎም ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር በወንጌላዊነት በመላ አገሪቱ በተሰራጩ ሰላይ ሰባኪያን በነሰነሱት ምክር ጭምር፣ ነባር ቁርኝቱ ደረጃ በደረጃ እንዲቋረጥ ሆነ። ይህም የኃይማኖቱ አባቶች ከዕውነተኛ መንፈሣዊ ሕይዎት ወጥተው የምድራዊ ዓለም ገዥዎች ፍላጎት አስፈጻሚዎች እንዲሆኑ አስገዳጅ ሁኔታ ፈጠረባቸው። ኑሯቸውንም ከላይ ጥንታውያኑ በሚገፉበት መልኩ ሳይሆን፣ ከመንግሥት በሚሰጣቸው በጄት የሚመራ ሆነ። ተግባራቸውም ለነፍስ፣ ለጽድቅ ሳይሆን፣ ለሥጋ አደላ። በመሆኑም የገዥዎች ቀኝ እጅ ሆኑ። ይህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕዝብ ሲበደል፣ ፍርድ ሲጓደል፣ የነበራት ሚዛን የመጠበቂያ እና የመቆጣጠሪያ ሥልጣን (check and balance) አሳጣት። ቤተክርስቲያኗን ገዥዎች ከሕግ እና ከሥርዓት ውጭ ሲሆኑ፣ በማውገዝ የተጓደለው እንዲሟላ፣ የተጣመመው እንዲስተካከል፣ የተበደለው እንዲካስ፣ በዳይ እንዲክስ የማድረግ አቅሟን አሳጣት። ይህም የኃይማኖት እና የመንግሥት ቁርኝት መለያየት ቤተክርስቲያኗ ይህን ሥልጣኗን እና ኃይሏን እንድታጣ አደረጋት።
በመርኅ ደረጃ «መንግሥት እና ኃይማኖት መለያየታቸው ትክክል እና ተገቢ ነው» ቢባልም፤ ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት እና ትውፊት ጋር አገናዝቦ ላየው እና ይህ ልዩነት በአገሪቱ፣ በሕዝቡ እና በኃይማኖቱ ላይ ካሳደረው አፍራሽ ተጽዕኖ አንፃር ሲመዘን፣ በሁለቱ መካከል የተደረገው ልዩነት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ መሆኑን ነባራዊ ሁኔታው ያሳያል። ትናንትም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ የክርስቲያን አገር ናት። ይህ ሲባል ግን «በአገሪቱ ውስጥ የሌሎች ኃይማኖቶች ተከታዮች የሉም» ማለት አይደለም። የተለያዩ ኃይማኖቶች ተከታዮች ጥንትም ነበሩ፤ ዛሬም አሉ። አገሪቱ ለሦስቱ ታላላቅ የዓለም ኃይማኖቶች መፍለቅያ ለሆነው የመካከለኛው ምሥራቅ አጎራባች በመሆኗ የተነሳ፥ የክርስትና፣ የእስልምናና የአይሁድ ኃይማኖቶች ተከታዮች ጎን ለጎን ለዘመናት የኖሩባት አገር ናት። ይህ ነባራዊ እና ታሪካዊ ዕውነት ነው። «ኢትዮጵያ የክርስቲያን አገር ናት፤ የክርስቲያን ደሴት ናት፤» ሲባል የሚሰጠው ተዳሳሽ ዕውነት «ከነዋሪው ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው ክርስቲያኑ ነው» ማለት መሆኑን መገንዘብ ያሻል። በሌላ በኩል «የክርስቲያን ደሴት ናት» የሚባለው አገሪቱን የሚያዋስኗት አገሮች፣ ማለትም፦ ሱዳን፣ ሱማሊያ፣ ጅቡቲ አልፎም ከቀይ ባሕር ማዶ ያሉት ሕዝቦች ኃይማኖታቸው በአመዛኙ እስልምና ወይም ሌሎች ኃይማኖቶች በመሆናቸው የተነሳ የሚነገር ሃቅ ነው። ለምሣሌ የ1987 ዓ.ም.ን የቤቶችና ሕዝብ ቆጠራ ውጤትን ብንመለከት የሚሰጠን ቀጥተኛ ትርጉም ከላይ የተባለውን ሃቅ ነው። የሚከተለውን ሠንጠረዥ ልብ ይሏል።
ተራ
ቁጥር የኃይማኖት ዓይነት የእምነቱ ተከታይ ብዛት ከአጠቃላዩ ሕዝብ ብዛት (በመቶኛ)
1 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን 26,877,657 50.59
2 እስልምና 17,412,431 32.77
3 የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን 5,405,106 10.17
4 የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን 459,000 0.86
5 ባሕላዊ እምነቶች 2,455,053 4.62
6 ሌሎች ኃይማኖቶች (ልዩ ልዩ) 520,981 0.98
ድምር 53,130,228 99.99
ምንጭ፦ ኢትኦጵ ቅፅ 2፣ ቁጥር 09፣ ታኅሣሥ 1993 ዓ.ም.
ከሠንጠረዡ መረዳት እንደሚቻለው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖት ተከታዩ ብቻ ከሕዝቡ ከግማሽ በላይ የሆነውን ይዟል። ሌሎች የክርስትና ኃይማኖቶች ተከታዮች ሲጨመሩ ከሕዝቡ ቁጥር ፷፪(ስድሳ ሁለት) በመቶው ክርስቲያን መሆኑን ያሳያል። ይህ የሕዝብ ቁጥር ደግሞ ረጅም እና በድል የደመቀ ታሪኩን፣ አኩሪ ባህሉን እና ነባር ኃይማኖቱን ምርኩዝ አድርጎ በአንድነት ቢነሳ፣ የነበረ መልካም አንድነት እና አብሮነቱን ብቻ ሳይሆን፣ በምሥራቅ አፍሪካ ልዕለ-ኃያል አገር ሆኖ ለመውጣት የሚገድበው አንዳችም ምድራዊ ኃይል ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶች እና ምዕመናን በእምነትም ሆነ፣ ወይም በዘመኑ የዕውነት መለኪያ ነው በሚባለው የሕዝብ ድምፅ መሥፈርት ብዙኃኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ኃይማኖት ተከታይ ስለሆነ፣ በነዚህ መሥፈርቶች ተጠቅሞ ኃይማኖቱን ከጥፋት፣ ሕዝቡን ከሥቃይ ለመታደግ ወደነበረው የመንግሥት እና የኃይማኖት ጥምረት እንመለስ እንኳን ማለት ባያስፈልግም፣ «ኃሣባችን ገዥ መሆን አለበት» የሚለውን አጠንክረው ሊይዙት እና ሊገፉበት ይገባል። ኃይማኖቱ በመናቁ እና በመዋረዱ አገሪቱ እና ሕዝቡ ተንቀዋል፤ ተዋርደዋል። ይህን ወደ ነበረበት ለመመለስ «እንኳን በሰላም ወደ አዲሱ ዘመን አሸጋገራችሁ» ማለት በቂ አይደለም። የተሻለ ራዕይ እና ተልዕኮ ቤተክርስቲያኗ እና ምዕመናኑ ሊይዙ ይገባል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የትግሬ-ወያኔ የአገዛዝ መዋቅር ውስጥ ላላችሁ የልዩ ልዩ ኃይማኖት መሪዎች ኢትዮጵያውያን ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያዊነት ስም የተደራጃችሁ የፖለቲካ እና የሲቪክ ድርጅቶች፤ በምትከተሉት ኃይማኖትም ሆነ በምታራምዱት ፖለቲካ የተለያያችሁ እንደሆነ እናምናለን። የኃይማኖት እና የፖለቲካ ልዩነት ግን አገርን ወደሚያጠፋ፣ ማንነትን ወደሚያስክድ የከፋ ጉዞ ይወስዳል ብለን አናምንም። አገዛዞች ይመጣሉ ይሄዳሉ። እንደአገዛዞች የተፋጠኑ አይሁኑ እንጂ፣ የሰው ልጆች ኃይማኖታቸውን እና የፖለቲካ አቋማቸውን ይለውጣሉ። የማይለወጠው የበቀሉበት አገራዊ ማንነት ብቻ ነው። በዚህ በማይለወጠው ማንነታችሁ አያያዥነትና ሁላችሁም ከቆማችሁበት አቋም አንፃር ለምትመኙት የአገር አንድነት፣ ዕድገት እና ብልጽግና ዕውን መሆን ብቸኛው መድኅን ከሕዝቡ ፍላጎት ጎን መቆም ነው።
ስለሆነም፣ በዚህ ዓመት የዘመን መለወጫውን ዕለት መነሻ በማድረግ የተመኛችሁት «የሰላም» ሽግግር ምኞቱ ዕውን የሚሆነው፣ ያሉብንን ችግሮች፣ የገጠሙንን መሰናክሎች፣ መነሻ ምንጫቸውን ሕዝቡ ዐውቆ እንዲታገላቸው የየበኩላችሁን የኅሊና እና የቁሣቁስ ስንቅ ስትሆኑት ነው። በሕዝባችን ላይ የተጋረጠው የመነጣጠል አደጋ፣ በአገራችን ላይ የተፈጸመው የብሔራዊ ጥቅም ክህደት፣ የዳር ድንበራችን መሸራረፍ፣ የድንግል መሬታችን ለዓለም ቱጃሮች በርካሽ ዋጋ መቸብቸብ እና አርሶ አደሩ ለችጋር መዳረግ ባለፉት ፳፭(ሃያ አምሥት) ዓመታት የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ የጣለብን ከፍተኛ ዕዳዎች እና ችግሮች ናቸው። ከሁሉም በላይ አገሪቱ ከሰሃራ በታች ካሉት የአፍሪቃ አገሮች ከፍተኛ የሆነ የውጭ ዕርዳታ እና ብድር ተቀባይ ሆና ሳለ፣ ሕዝቡ በምግብ እህል ራሱን ባለመቻሉ፣ ይኸውና ከ፰(ስምንት) ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝባችን ለምግብ ችግር (ርሃብ) ተዳርጓል። እነዚህን ችግሮች በአናታችን ላይ ተሸክመን፣ «እንኳን በሰላም ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ» ልንል የምንችልበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። ማድረግ እና ማለት ያለብን፦ «ያለፈው ዘመን ችግር እና መከራ የበዛበት ነበር። የዚህም ችግር እና መከራ መነሻ ቋቱ የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ የዘረጋው የዘር ፖለቲካ እና የሚከተለው ፖሊስ ነው። ይህን ሁኔታ ለመለወጥ ቀበቷችንን ጠበቅ፣ ኅሊናችንን ቆጣ፣ ኃሞታችንን ኮስተር፣ አንድነታችንን ጠበቅ አድርገን የመከራ እና የችግር ቋት የሆነውን አገዛዝ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አሽንቀንጥረን ለመጣል እንነሣ!» ብሎ ሕዝቡ በቁርጠኝነት እንዲነሳ ማነቃቃት፣ መቀስቀስ፣ ማደራጀት እና መምራት ይገባል።

ለሰላም ያለን ምኞት እንዲሣካ፣ ፀሎታችንም፣ ተግባራችንም በዚህ አቅጣጫ እንዲሆን እንትጋ!
ኢትዮጵያ በቆራጥ እና ታማኝ ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘለዓለም ፀንታ ትኖራለች!!