ከዲሲ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን የባለ አደራዎች ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

 

ዶክተር ጌታቸው መታፈሪያ በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በምትገኘው ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅርቡ የተከሰተውን ድርጊት መነሻውንና ሁኔታውን አስመልክተው የባለ አደራዎች ቦርድን አቋምና ውሳኔ በዝርዝር አስረደተዋል። በዚህም መሠረት የችግሩን መነሻ በሚከተሉት አራት ነጥቦች አስፍረዋል፤

1) ብዙኅን አባላት ያጸደቁትን የቤተክርስቲያኑን መተዳደሪያ ደንብ አንቀበልም የሚሉ መነሳታቸው፣

2) አንዳንድ ካህናት ከራስ ወዳድነት መንፈስ በመነሳናት አስተዳደሩንም ገንዘቡንም መቆጣጠር አለብን ማለታቸው፣

3) በአሁኑ ተቃውሞ ውስጥ የተሳተፉት አላማቸውና ግባቸው የተለያየ መሆኑና አንዳንዶችም ከንስሐ አባቶቻቸው በተነገራቸው ከእውነት የራቀ ወሬ የተነሳሱ መሆናቸው፣

4) አንዳንድ ግለሰቦች ግራና ቀኙን ሳይመለከቱ ፣ በጥሞና ሳይሰሙና ሳያረጋግጡ በግብታዊነት አጀቡን እያደመቁ መገኘታቸው፣

5) ያሁኑ የባለአደራዎች ቦርድ ዕውነታው እሱጋ እያለ መግለጫ በወቅቱ በማከታታል ባለማውጣቱ ምክንያት አባላት ለአወናባጆች መጋለጣቸው፣

ዶ/ር ጌታቸው የር/አ/ደ/ሰ/ቅ/ማ/ቤ/ክ የባለ አደራዎች ቦርድ ሊቀመንበር ከዚህም በማያያዝ ለአራት ሳምንታት በጸሎትና በማምለኪያ አውደ ምሕረት ላይ በጥቂት ካህናትና ግብረአበሮቻቸው አማካይነት ታይቶ በማያታወቅ መልክ ጸያፍ ስድብ፣ብጥብጥ፣ጫጫታና ግፊያ መታየቱንና መፈንቅለ ቦርድ ሙከራ መደረጉንም ገልጸው ይህም በቤተክርስቲያኗ ላይ ጥቁር ነጥብ መጣሉንም አስታውቀዋል። “ተቆርቋሪ ኮሚቴ” ብሎ እራሱን የሰመው ቡድን የግለሰቦችን ስብዕና በመግደል፣ ስም በማጥፋት በራሪ ወረቀት በስውር ይበትን የነበረው አሁን በይፋ ብቅ ማለቱና ለቤተክርስቲያኗ ሰላም ሲባል ከነሱም ጋር ውይይት ጀምረው እንደነበርና በቡድኑ ሰላም አለመፈልግ ምክንያት ውይይቱ መደናቀፉን ጠቁመው እነዚህ በስውር ወረቀት ይረጩ የነበሩ ግለሰቦች አሁን በደብሯ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው ብጥብጥ መሪዎች መሆናቸውን አጋልጠዋል። ዶ/ር ጌታቸው ከዚህም በተጨማሪ የባለአደራዎች ቦርድ ሁኔታዎችን አገናዝቦ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ለማሳለፍ መገደዱን ገልጸዋል። ውሳኔዎቹም የሚከተሉት ናቸው፤
1) በሰውና ንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመከላከልና የደብሯን ጎረቤቶች ሰላምና ጸጥታ ለማክበር ቤተክርስቲያኗን ለመዝጋት መገደዳቸውን። እንዲሁም ታላቅ ወንጀል በመፈጸም የቤተክርስቲያኗን በር በመስበር ንብረቷን በመድፈርና አባላቱን በመናቅ ህገወጥ ሹም ሽር ያደረጉት ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ መሆናቸውን፣
2) የአባላትን ስብሰባ ለጥቂት ቀናት ለማስተላለፍ መገደዳቸውና የደብሯ ሰላምና ጸጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ መረጋገጥ እንዳለበትና በሰውና በንብረት ላይ አደጋ እንዳይደርስ ተግተው በመስራት ላይ መሆናቸውን፣
3) ቤተክርስቲያኗ ለከፋ አደጋ ያጋለጡ ቀንደና ግለሰቦች ላይ የደብሩ መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረትና የአሜሪካን ህግ በደነገገው መሠረት ህጋዊ እርምጃዎችን እንደሚወሰዱ ገልጸው ይህንን በሚያደርጉበት ጊዜ ደስተኞች ሆነው አንዳልሆነና ተገደው የገቡበት መሆኑንም አልሸሸጉም። ይህም የሚደረገው ለቤተክርስቲያኗ ህልውና ቅድሚያ መስጠት ስለሚገባና የባለአደራዎች ቦርድ ኃላፊነት በመረጠው ህዝብ ተጠያቂነት እንዳለበት አንደሚረዱ አስገንዝበዋል።

ዶ/ር ጌታቸው በቅርቡ የአባላት ስብሰባ ስለተጠራ ቦርዱ ሪፖርት እንደሚያቀርብና ውይይትም ስለወቅታዊው ሁኔታ እንደሚደረግ ገልጸው አባላት መብታቸውን በመጠቀም በስብሰባው ላይ ተገኝተው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ከተቃጣባቸው አደጋ ቤተክርስቲያናቸውን እንዲከላከሉ ጥሪ አድርገዋል። ከባለአደራዎች ቦርድ ውስጥ ሊቀመንበሩ፣ ምክትል ሊቀመንበሩና ጸሐፊዋ የአገልግሎት ዘመናቸውን ጨርሰው በጥቂት ወራት ውስጥ የአመቱን በጀት አጸድቀውና አስመራጭ ኮሚቴ አስመርጠው ከቦርድ ይሰናበታሉ ካሉ በኋላ በሽግግሩም ሂደት ወቅት የቤተክርስቲያናችን ሒሳብ በተመለከተ የውጭ የሒሳብ መርማሪ (ኦዲተር) ሂሳቡን አጣርቶ እንደሚያቀርብ አስታወቀዋል። ይህም በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ዝናን ያተረፈውን ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለውን የሂሳብ አያያዛችን ስራ ላይ ይውላል ብለዋል። በመጨረሻም ዶ/ር ጌታቸው አባላትና ምዕመናን ለቤተክርስቲያናችን፣ ለአገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለአለም በሞላ እንድትጸልዩ አደራ እንላለን በማለት መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።