የቡሄ ባዕላችን

ደረጀ ሀብተወልድ – ሆላንድ

ቀኑ ዐይን ያዝ ማድረግ ሲጀምር የቡሄ ጭፈራችንን በኮሎኔል አሰፋ ቤት ለማሟሸት ወስነን ወደዚያው አመራን።ጡረተኛው ኮሎኔል እንደወትሮው ከረዥሙ ጢማቸው ጋር የሚመሳሰለውን ነጭ ጭራቸውን እያወዛወዙ ግቢያቸው ውስጥ ቁጭ ብለው ቪኖ ይጎነጫሉ። አሹ ማወራረዱን ጀመረ፦

“ቡሄ ና ቡሄ በሉ…” እኛም በስሜት ውስጥ ሆነን ተሰጥኦውን እየመለስን ነው -“ሆ!” በማለት።

አሹ ቀጠለ፦

እዛ ማዶ – ሆ! ነጭ ኬሻ ሆ!
እዚህ ማዶ – ሆ! ነጭ ኬሻ ሆ!
የኔማ ኮሎኔል – ሆ! ሻምበል ባሻ ሆ!”

ምን ልበላችሁ? ኮሎኔል አሰፋ እሳት ለብሰውና እሳት ጎርሰው በመነሳት ወደ ቤታቸው በፍጥነት ከገቡ በሁዋላ ከዘራ ይዘው በመውጣት፦”ቀጥል! ጥፋ! ወሮበላ ዱርዬ ሁሉ! ሀይለስላሴ የሰጡኝን ማዕረግ እንኩዋን እናንተ ደርግም አልገፈፈኝ? ቀጥል!“ እያሉ አንከሳከሱን። በወቅቱ ስህተታችን ባይገባንም፤ ውሎ አድሮ ግን ሳንረዳነው አልቀረንም። ለዚያ ስህተት የተዳረግነው “የሻምበል ባሻነት ማእረግ – ከኮሎኔልነት እንደሚበልጥ አስበን “የሙገሳ ስንኝ በማዘጋጀታችን ነው። ለካ አሞገስን ብለን ብዙ ደረጃ ዝቅ አድረገናቸው ኖሯል። ሆኖም ልጅነት ነውና ባለማወቅ እንጂ ሆነ ብሎ የተደረገ አልነበረም።

ነሀሴ በባተ በ13ኛው ቀን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ “ደብረ-ታቦር” ተብሎ ይከበራል- የታቦር ተራራ ማለት ነው።ይህ ተራራ ጌታ ኢየሱስ በምድር ላይ በተመላለሰበት ወቅት ድንቅ ተአምራት ከገለፀባቸው ስፍራዎች አንዱ ነው።

“…ከስድስት ቀናትም በሁዋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያ ዕቆብን ወንድሙንም ዮሀንስን ይዞ ወደ ረ ዥም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው።በፊታቸውም ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሀይ በራ፤ ልብሱም እንደ ብርሀን ነጭ ሆነ።እነሆ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፦”ጌታ ሆይ! በዚህ መሆን ለኛ መልካም ነው፤ብትወድስ በዚህ ሶስት ዳስ፤ አንዱን ለአንተ፣ አንዱንም ለሙሴ፣ አንዱንም ለኤልያስ እንስራ” አለ። እርሱም ገና ሲናገር እነሆ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ እነሆም ከደመናው፦” በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ።” — ማቴ 17፤ 1-5

አባቶቻችን እንዳስተማሩን ባህላዊው የቡሄ በአላችን መነሻ መሰረቱ ይህ በደብረ-ታቦር የሆነው ድንቅ ነገር ነው።

ጎንጉነን የምናጮኸው ጅራፍ የነጎድጉዋዱ ድምፅ ምሳሌ ሲሆን፤የምንቀልሳቸው የቡሄ ዳሶች ደግሞ የጴጥሮስን ንግግር የሚያስታውሱን ናቸው-“ጌታ ሆይ! በዚህ መሆን ለኛ መልካም ነው፤ አንድ ላንተ፤ አንድ ለሙሴ፤አንድ ለኤልያስ ዳስ እንስራ” ማለቱን።(እዚህ ላይ ጴጥሮስ ለኔ ወይም ለኛ እንስራ አለማለቱ፤በክርስትና “ እኔነት “ ስፍራ እንደሌለው አመላካች ይሆን?)

ይሁን እንጅ በአሉ ከጥንት ጀምሮ ከሀማኖታዊነቱ ይልቅ ባህላዊ መልኩ የጎላ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። ስለዚህም በክርስቲያኖችም ሆነ በሙስሊሞችም ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት አግኝቶ ሁሉንም ለረዥም ዘመናት አፋቅሮና አስተሳስሮ ያሳደገና ያኖረ ልዩ በአል ነው – ቡሄ።

ቡሄ መጣ
ያ መላጣ
ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ።
የቡሄ ‘ለት
አለው ለከት
እንደ ጋሻ የሚመከት

እያለ በቡሄ ሙልሙል ያላደገ ማነው?

አዎ! ባንድ ዳስ ተሰባስበን በፍቅር በልተናል፤ጠጥተናል፤ተቃቅፈን እና ተቀባብለን ጨፍረናል። በሚጣፍጠው የልጅነት አንደበት “የእማምዬን ቤት-ወርቅ ይፍሰስበት! “እያልን መባረክን፤ መመረቅን ተለማምደንበታል።ከሁሉም በላይ የአገራዊ ፍቅር መሰረቱን አግኝተንበታል። ኢትዮጵያዊነት እንደ ነፋስ የሚጋባ የአውሊያ መንፈስ አይደለም፤ ምንጮች አሉት። ብዙዎቻችን ከነዛ ምንጮች ስለጠጣን ነው በመፈቃቀድ ገመድ በአንድነት ተሳስረን የምንገኘው።እነዛም ምንጮች፦ የሰርግ ድንኩዋኖቻችን፣የሀዘን ዳሶቻችን፣የቡሄ ቤቶቻችን ወዘተ ናቸው።

ከመለኮታዊ ጥበቃ ባሻገር ለተሳሰርንበት የፍቅር እትብት ዘላቂነት ዋስትና የሆኑትን እነዚህን እሴቶች ታዲያ ልንጠብቃቸውና ልንንከባከባቸው ይገባል።

ይህን ያልኩት አሁን አሁን ባህሉም እየደበዘዘ፤ ጭፈራውም መልኩን እየቀየረ የመጣ ስለመሰለኝ ነው።

ለምሳሌ እኔ፦

የዋንዛው ቲማቲም
ሊሰጠኝ ነው ሳንቲም

እያልኩ ስጨፍር የማደጌን ያህል፤ የሁለት ጊዜ ታናሽ ወንድሜ ደግሞ ሰሞኑን የቡሄ ጭፈራውን እንደሚከተለው በኢሜል አድርሶኛል ፦

እዛ ማዶ ቀይ ዶሮ
እዚህ ማዶ ቀይ ዶሮ
የኔማ ደረጀ – ሊልክ ልኝ ነው – መቶ ዩሮ