ብሮሹሯ!… . አዲስ አበባ… ከ1850 በላይ ተዋንያንን በአስቸኳይ ትፈልጋለች!… (አንተነህ ይግዛው)
አዲስ አበባ…
ከ1850 በላይ ተዋንያንን በአስቸኳይ ትፈልጋለች!… (አንተነህ ይግዛው)
.
.
ዛሬ ማለዳ…
ኦሎምፒያ አካባቢ ታክሲ እጠብቃለሁ (ባቡሩ በዚያ በኩል ስለማያልፍ)…
በመካከል…
አንድ ከሲታ ወጣት፣ መዳፉ ላይ ካለው የብሮሹር ክምር እየቆነጠረ፣ ታክሲ ጥበቃ ለቆመው ህዝብ ያድላል፡፡
እኔ ጋ ሲደርስ…
ቀና ብሎም ሳያየኝ፣ አስራ ምናምን ብሮሹር አስታቅፎኝ፣ ጉዞውን ቀጠለ፡፡
ገረመኝ!…
ጀለሴ ብሮሹሩ አላልቅለት ብሎ ተቸግሯል መሰል!?…
.
ታክሲ ውስጥ ሆኜ…
ወጣቱ ሳልወድ በግድ ካሳታቀፈኝ ደርዘን ብሮሹር አንዷን መዝዤ አየት አደረግኳት…
“ተዋናይ እንፈልጋለን!…” ይላል በጉልህ የተጻፈው ርዕሷ፡፡
ዝቅ ብሎ ደግሞ…
“አስቸኳይ!…” የሚል ማሳሰቢያ አለ፡፡
በማሳሰቢያው መሰረት፣ በአስቸኳይ አነበብኳት…
.
ዘ ይገርም አዲስ አበባ!…
አመንከኝም አላመንከኝም…
አሁን አዲስ አበባ ከ1800 በላይ ተዋንያንን በአስቸኳይ ትፈልጋለች!…
ብሮሹሯ እንደምትለው…
የተለያዩ የፊልምና የቴሌቪዥን ድራማ ፕሮዳክሽን ኩባንያዎች፣ በድምሩ ከ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሃምሳ በላይ ተዋንያንን በአስቸኳይ ይፈልጋሉ፡፡
በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ጀማሪና ነባር ተዋንያን፣ በ4 አዳዲስ ፊልሞችና በመተላለፍ ላይ በሚገኙ 4 የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ይተውኑ ዘንድ ይፈለጋሉ፡፡
.
እነ እንተና በ80 ብር ደመወዝ ብሄራዊ ቲያትር ለመቀጠር፣ ግማሽ ዕድሜያቸውን ያህል የወጡ የወረዱባት አዲስ አበባ፣ ዛሬ ተዋንያንን ፍለጋ መንገድ ለመንገድ መንከራተት ጀምራለች!…
በቴሌቪዥን ድራማ ላይ በተዋናይነት ለመሳተፍ፣ የስድስት አመታትን ደፋ ቀና ይጠይቅ የነበረው ዘመን አልፎ፣ ዛሬ ተዋናይ ለመሆን ስድስት ፎቶ ግራፍ መነሳት ብቻ በቂ ሆኗል!…
.
“እስከ መስከረም 15 ድረስ 4 ጉርድ ፎቶ ግራፍ፣ አንድ አልበም ሳይዝ የቁም ፎቶ እና አንድ አልበም ሳይዝ ከወገብ በላይ የሆነ ፎቶ ይዘው ይምጡ!…” ትላለች ብሮሹሯ፡፡
.
አንዳንዶቹ ፊልሞችና ድራማዎች ይፈልጉታል የተባለው የተዋንያን ብዛት ይገርማል!…
በተለይ የ“ሞጋቾች”…
ሞጋቾች ከ400 በላይ ተዋንያንን እንደሚፈልግ ሳነብ፣ ደራሲውን ሃይሉ ጸጋዬን ጠረጠርኩት፡፡
ሃይሉሻ በቀጣዩ ሲዝን፣ ኢቦላ ከ400 በላይ ሰዎችን ሲረፈርፍ የሚያሳይ ትዕይንት ለመፍጠር አስቧል እንዴ?…
ያ ካልሆነም…
የድራማውን ዘውግ ወደ “ጦርነት” ሊቀይረው ሳያስብ አልቀረም!…
ምን ላድርግ ታዲያ!?…
ሞጋቾች በቀጣዩ ሲዝን እንዲህ ያለ ነገር ካላሰበ፣ ከመሬት ተነስቶ ከ400 በላይ ተዋንያንን ይፈልጋል?…
.
የምር ግን…
የቲቪ ድራማዎቻችንን ቁጥር በዚሁ ከቀጠለ፣ ድራማ እንደ ዜና በየሰዓቱ የሚተላለፍ ቋሚ ነገር የሚሆን አይመስላችሁም?…
እንደኔ እንደኔ…
የቴሌቪዥን ድራማዎቻችን እና የድራማ አፍቃሪው ህዝብ ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ፣ ጥናት ቢደረግበት መልካም ነው፡፡
እንዲህ አይነቱ ጥናት፣ የሚያመለክተው ነገር የሚኖር ይመስለኛል፡፡
.
ለምሳሌ…
ህዝብ በገሃዱ አለም ኑሮው ተስፋ ሲቆርጥ፣ በፈጠራ ድራማ መጽናናት ይጀምራል!…
ኢኮኖሚ በሁለት ዲጂት ሲያድግ፣ የድራማ ፍላጎት በአምስት ዲጂት ያድጋል!…
ህዝብ እንዲፈዝ ከፈለግክ፣ በየሳምንቱ ሳይሆን በየቀኑ በድራማ ጠምደህ ያዘው!…
በልማታዊ አገር ላይ፣ ፊልም የስራ አጡን ቁጥር በመቀነስ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል!…
.
ብሮሹሯን እያፍተለተልኩ…
ለብዙ ጊዜ አልዋጠኝ ብላ የኖረች፣ የአንድ ወዳጄ ድምዳሜ ትዝ አለችኝ…
“ተዋናይነት ጥበብ አይደለም!… ተዋናይና ቴፕ አንድ ናቸው – የሰጧቸውን ይለፈልፋሉ እንጂ፣ ከራሳቸው የሚያፈልቁት የላቸውም!…” ይላል ወዳጄ፡፡
ይሄን የወዳጄን ድምዳሜ ለማመን ስቸገር ኖሬ ነበር…
አሁን ግን ለማመን እየዳዳኝ ነው…
ምክንያቱም…
“ስድስት ፎቶግራፍ ካለህ፣ ተዋናይ ነህ!…” እያለችኝ ነው – ብሮሹሯ!…
.
