መልካም አስተዳደርና መንግስት ~ ችግሩም ከሱ? መፍትሄውም ከሱ? (የትነበርክ ታደለ)
የገዢውን ፓርቲ አስረኛ መደበኛ ጉባኤን ተከትሎ ሰሞኑን በተደጋጋሚ እየተነሳ ያለው “የመልካም አስተዳደር እጦት ታይቶብናል” የሚል መንግስት ራሱ የሚያነሳው ጉልህ ችግር ነው። ይህ ችግር ዛሬ በድንገት የተከሰተ ሳይሆን ህብረተሰቡ ለረዥም አመታት ሲያነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች ጥርቅም ነው።
በተለይም ደግሞ በመልካም አስተዳደር ውስጥ ከሚካተቱት ዋነኛ የሆነው “የህግ የበላይነት አለመኖር” ህዝቡም የሚያውቀው መንግስትም ራሱ ያመነው ችግር ነው።
በአንድ ሀገር የህግ የበላይነት የለም ማለት አምባ ገነንነት ነግሷል ማለት ነው። ከህግ ይልቅ ሀይለኞች ፈቃዳቸውን በፈለጉ ጊዜ ሁሉ በህዝቡ ላይ ይጭናሉ ማለት ነው። የህግ የበላይነት አልተከበረም ማለት አቅመ ቢሶች የሚጨቆኑበት፣ ድሆች የማይሰሙበትና ሀይለኞች የሚፈነጭጩበት ሀገር ተፈጥሯል ማለት ነው።
ሌላው የመልካም አስተዳደር እጦት መገለጫ ደግሞ ሙሰኝነት (የባለስልጣናት ሌብነት) ተንሰራፍቷል ማለት ነው። በሙስና መሀል የተቀመጡ ሰዎች ካሉ ደግሞ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያለችና ብዙ ስራዎቿን በብድርና በእርዳታ የምትሰራ ሀገር ብዙ የተበለሻሸ ነገር ተፈጥሯል ማለት ነው። መንግስታዊ ሌብነት ካለ የሀገር እድገት ወይም ልማት ልክ ጪንጫ ላይ እንደተዘራ ፍሬ ነው። ቶሎ ይበቅላል ቶሎ ይደርቃል። መሰረት የለውም።
ህዝብ ከመንግስት ከመልካም አስተዳደር የበለጠ ምን ሊጠብቅ ይችላል? ፍትሀዊነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ከሌለ ህዝብ ተስፋው ምንድነው?
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን እጅግ የሚያሳስበው በሀገራችን የታዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተከታትሎ ለህዝብ ይፋ የሚያደርግና መፍትሄ የሚያፈላልግ ነጻ ተቋም አለመኖሩ ነው።
ዲሞክራሲያዊ በሆኑ ሀገራት የመንግስትን የቀን ተቀን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ ወደ ህዝብም ወደ ፍትህም የሚያመጡ ብዙ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አሉ። በሀገራችን መንግስትን መገዳደር የሚችል እንዲህ አይነት ተቋም ወዴት አለ? በተራ የፌስ ቡክ ጽሁፍ ሆድ የሚብሰው መንግስታችንስ እንዲህ አይነት ተቋማት ኖረው ቢገዳደሩት ይፈቅዳል ወይ?
መንግስት ራሱ ጥሎ ራሱ እያነሳ መልሶ ራሱ እየነገረን ይሄድ ዘንድ እንዴት ይቻላል? የመልካም አስተዳደር ጭግርኮ ስልጣን ለመልቀቅም ስልጣን ለማስለቀቅም የሚያስችል ዋነኛ ጉዳያችን ነው!
እንግዲህ ጥልቅ የሆኑ የሀገራችንን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከስር ለመቅረፍ መንግስት ችግሮቹን ማመኑ ብቻ ፋይዳ የለውም! ቲዮሪዎችን ለህዝብ መጋትም ምንም ቁም ነገር አይደለም! ፋይዳው ነጻና ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱና መንግስትን መቆጣጠር የሚችሉ ተቋማት መፍጠር መቻል ነው! እላለሁ!