ዶ/ር አክሊሉ ሐብቴ መፈንቅለ ቦርድ አወጁ

ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ውስጥ በምትገኘው በደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣው ቤተክርስቲያኒቷን ከህጋዊው ቦርድ አስተዳደር ነጥቆ ለወያኔው ሹመኛ ለአባ መላኩ (አቡነ ፋኑዔል) የማስረከብ ትንንቅ በዛሬው ዕለት ከፍ ወደአለ ደረጃ መሸጋገሩ ከስፍራው የደረሰን ሪፖርት ያመለክታል። በዚህም መሠረት የዕለተ ሰንበት የቅዳሴ አገልግሎት ተጠናቆ ህዝቡ ከተሰናበተ በኋላ በአቶ አዲሱ አበበ አማካይነት የተደራጁት የቤተክርስቲያኒቷ አባላትና ካህናት እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው ከየት እንደመጡ የማይታወቁና የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ምዕመናን ለመሆናቸው እንኳ ማረጋገጫ ሊቀርብላቸው የማይቻል ሰዎችን አስቀድመው ቦታ አሲዘው በተጠንቀቅ እንዲጠባበቋቸው አደረጉ። ከዛም በዕቅዳቸው መሠረት ዶ/ር አክሊሉ ሐብቴ አብረዋቸው በረብሻው ላይ ተሳትፎ ከሚያደርጉ የውስጥ አርበኛ ካህናት ከሆኑ ከቄስ ኃይሉና ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ በተሰጣቸው የድምፅ ማጉሊያ በመጠቀም ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው “የደብሩ የባለ አደራዎችቦርድ ተሽሯል“ ብለው በሌላቸው ስልጣንና ኃላፊነት አዋጃቸውን አስተጋቡ። ይህ አዋጃቸው የቤተክርስቲያኒቷን የመተዳደሪያ ደንብ የጣሰና ህገወጥ ድርጊት ነው። የር/አ/ደ/ሰ/ቅ/ማ/ቤ/ክ ለ3ኛ ጊዜ ተሻሽሎ እ.አ.አ. ጁን 10, 2012 የጸደቀው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 11 የባለአደራዎች ቦርድ በሚለው ርዕስ በማያሻማ ሁኔታ ከዚህ በታች የተጠቀሰውን በመጻረር ነው ዶ/ር አክሊሉ የጭቃ ጅራፋቸውን ያሽጎደጎዱት። ይኽውም የርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ሥራዎችንን የሚመራ፣በማናቸውም ጉዳይ የቤተ ክርስቲያኑ ተጠሪና ኃላፊ የሚሆን በጠቅላላ ጉባዔ የሚመረጥ አንድ የባለ አደራዎች ቦርድ ይኖራል። የባለ አደራዎች ቦርድ ተጠሪነቱ ለቤተክርስቲያኑ የጠቅላላ አባላት ጉባኤ ይሆናል።
በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት ዶ/ር አክሊሉ አንድ ተራ ምዕመን እንጅ ምንም ዓይነት የባለ አደራዎች ቦርድ ሥልጣንና ኃላፊነት የላቸውም። ዶ/ር አክሊሉ ሐብቴን የመሰሉ በትምህርት፣ በስራ ልምድና በዕድሜ አንጋፋ ከሆኑ አዛውንት አንደበት እንደዚህ ዓይነት መደዴና ህገወጥ ነገር መነገሩ ብዙዎችን በእጅጉ ማሳዘኑና “ኢትዮጵያ ሰው አልወጣላትም” ያሰኘ መሆኑንም ገልጸውልናል። የታወጀው ሹም ሽር ምንም ዓይነት ህጋዊነትና የሌለውና መፈንቅለ ቦርድ መሆኑ ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰው ሪፖርት ያመልክታል።
በዚህ ታላቅ ደብር አስተባባሪነት በዋሽንግተን ሞኑመንት አጠገብ በሊቢያ ለተሰው ሰማዕታት የመታሰቢያ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ለረዥም ዓመታት በደብሩ ውስጥ ሲብላላና ሲንተከተክ የነበረው የጥቂት ካህናትና ምዕመናን ቤተክርስቲያኒቷን ለወያኔ አስላፎ የመስጠት የደፈጣ ትንንቅ አደባባይ በመውጣት አሁን ለተፈጠረው ችግር አቀጣጣይ ነጃጅ እንደሆነ የቤተክርስቲያኗ አንጋፋ አባላት ይናገራሉ። እነዚህ ለህግና ለስርዓት ደንታ የሌላቸው ግለሰቦችበአቶ አዲሱ አበበ በኩል ከወያኔው ተወካይ ከአባ መላኩ ጋር በቀጥታ የሚሰሩና “ከእናት ቤተክርስቲያን ጋር ተራርቀናል እንደገና አንድ መሆን አለብን” በሚል በማር በተለወሰ መርዝ የተወሰነ ቁጥር ያላቸውን ምዕመናን ለማወናበድ እንደቻሉ ይነገራል። አንዳንዶቹም ከፍተኛ የደርግና የኢሰፓ ባለስልጣኖች የነበሩና ወያኔ ኢትዮጵያን ወሮ ከያዘበት ጊዜ አንስቶ አገር ቤት ለመሄድ ፍላጎቱ ቢኖራቸውም ያልቻሉና ሲሞቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የመቀበር ፍቃድ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩም ይገኙባቸዋል ተብሏል። የነዚህ የቀድሞ የደርግ ባለስልጣኖች ፍላጎት ከነአዲሱ አበበ ቤተክርስቲያኗን ለወያኔ በጉቦ መልክ የማቅረብ ተልዕኮ ጋር መስተጋብር እንደፈጠረላቸውና በአቶ አዲሱ አበበ በኩል ቤተክርስቲያኗን በአባ መላኩ ቁጥጥር ስር ካስገቡ አገር ቤት በህይወታቸውም ሆነ በበድናቸው ለመግባት እንደሚፈቀድላቸው ቃል የተገባላቸውም እንደሚገኙ ውስጥ አወቆች ለዝግጅት ክፍላችን ጠቁመውናል።
በምዕመናን የተመረጠውና ከፍተኛ ኃላፊነት ጫንቃው ላይ የተሸከመው የባለ አደራዎች ቦርድ ከዛሬው የዶ/ር አክሊሉ አዋጅ በኋላ ይሉኝታና የዋህነት ከወያኔ ተኩላዎች ጋር በሚደረግ ፍጥጫ ስለማያዋጣ ጠንካራና የማያዳግም እርምጃዎችን በአስቸኳይ በመውሰድ ቤተክርስቲያኒቷን ማዳን እንደሚጠበቅበት በስፋት እየተነገረ ነው። በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያኒቷ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ በመግፋት ላይ ያሉትን ቀንደኝ በጥባጭ ምዕመናንና ካህናት ተጨማሪ ወንጀል እንዳይሰሩ ለማስቆም ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዳይገቡ ከፍርድ ቤት ማዘዣ ማውጣትእንደሚገባቸው በመነገር ላይ መሆኑ ተገልጾልናል። እንዲሁም በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ከባለ አደራዎች ቦርድና ከደብሩ አስተዳዳሪ ውጭ ማንም ሰው እየተነሳ እንዳይዘላብድና እንዳይቀባጥር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም ተጠቁሟል። ሁኔታው እስኪረጋጋና የምዕመናን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እሲኪረጋገጥ ድረስ የፖሊስ ኃይል በቅርብ እንዲገኝ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉም በርካቶች መሆናቸውን የደረሰን ሪፖርት ያመለክታል። ይህንን በመካሄድ ላይ ያለ ቀጣይ ዜና (developing story) እየተከታተልን መረጃ የምናቀብ መሆኑንን እንገልጻን።