የኢትዮጵያ የስደት መንግስት ምስረታን በተመለከተ የተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ
የኢትዮጵያ የስደት መንግስት አደራጅ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የስደት መንግስት የምስረታ ሂደትንና እያከናወናቸው የሚገኘውን ሰፊ የስራ እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ፤ ቅዳሜ፣ ሴፕቴምበር 12፣ 2015 የመጀመሪያውን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። ጋዜጣዊ መግለጫውን ብዙ ሚድያዎች፣ ጋዜጠኞችና፣ በአለም ዙሪያ የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተከታትለውታል።
በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ የስደት መንግስት አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ስለሺ ጥላሁንና፤ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሥዩም ወርቅነህ፤ ከተለያዩ ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። የአደራጅ ኮሚቴው አመራሮች በተነሱት ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ከመስጠታቸው በተጨማሪ እንዳስገነዘቡት፤ የኢትዮጵያ የስደት መንግስት መመስረት ወቅታዊና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማብራራት፤ በምስረታው ሂደት ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሳተፍ እንዲችሉ የተመቻቸና ለሁሉም ያለልዩነት ክፍት መሆኑን በማስገንዘብ፤ ይህ ቅዱስ ሃሳብ በአስተማማኝ
መልኩ የተሳካ እንዲሆን፤ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዜጎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና፣ የሲቪክ መሃበራት፣ እንዲሁም በአለም ዙሪያ የሚኖሩ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦችና፣ የእምነት ኣባቶች ርብርብና ቀጥተኛ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በማስረገጥ፤ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሃገርአድን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በእለቱ ከተሳተፉ ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች መካከል፤ የአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ድምፅ ሬድዮ፣ የአዲስ ድምፅ ሬድዮ፣ የኢትዮጵያ ሽግግር ምክር ቤት ሬድዮ፣ የህሊና ሬዲዮ፣ የምንይሻላል ሬድዮ፣ የሰይፈ ነበልባል ሬድዮ፣ የዳላስ ኮሚኒቲ ሬድዮ፣ ቅንጅት ስዊዘርላንድ ፓልቶክ፣ ክርስቲያን ኢንተርናሽናል የቴሌቪዥን ሚዲያ፣ የቀድሞ የአንድነት ፓርቲ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ መስራች፣ የአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ኤዲተር እንዲሁም እንቁና ቁምነገር ጨምሮ በተለያዩ ጋዜጦች ይፅፍ የነበረና በሙያው ጋዜጠኛና መመህር የሆነው አቶ የትነበርክ ታደለ በስደት ከሚገኝበት ከኬንያ፣ እንዲሁም ሌሎች በርካቶች ይገኙበታል።
በዝግጅቱ የተነሱት ጥያቄዎች በአብዛኛው በስደት መንግስት መመስረት አስፈላጊነትና በሂደቱ ዙሪያ የሚያጠነጥኑና የሚያተኩሩ ነበሩ። አደራጅ ኮሚቴው በቀጣይ ቀናት የጋዜጣዊ መግለጫው ሙሉ ዝግጅትን በድምፅ የሚያቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልፃለን።
የኢትዮጵያ የስደት መንግስት አደራጅ ኮሚቴ
ሴፕቴምበር 16፣ 2015