ኑ! እንወቃቀስ! (ጌታቸው ሺፈራው)
‹‹በትጥቅ ትግል የሚያምኑ ሰዎች ስኬት የራቃቸው በሰላማዊ ትግል ምክንያት አድርገው ካሰቡ ስህተት ነው፡፡ በሰላማዊ ትግል የምናምን ሰዎችም በትጥቅ ትግል ምክንያት ሊሳካልን እንዳልቻለ ካሰብን ስህተት ነው፡፡›› አንዱዓለም አራጌ (የሀገር ፍቅር ዕዳ)
ይችን ርዕስ በአንድ ወቅት እጅግ የማከብረው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ተጠቅሞባት ነበር፡፡ እኔም ዛሬ መዋቀስ ስላማረኝ ተውሸዋለሁ፡፡ በመሰረቱ ይህን ስርዓት ከሚቃወሙ አካላት ጋር ከመነታረክና ከመናቆር ይልቅ መነጋገር፣ መመካከር አንዳንዴ አለፍ ሲልም መወቃቀስ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ እንኳ ካልሆነ ድንበር አለመጋፋት አንድ አማራጭ ነው፡፡ በተለይ በተለይ ስርዓቱን ትተው በረባ ባልረባው ወደ ጎንዮሽ የሚላፉትን ተቃዋሚዎች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መውቀስ ለትግሉ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን የምለው ዛሬ ጠዋት የግንቦት 7 ወጣቶች በቅርቡ ይወጣል የተባለ ሰላማዊ ትግሉን የሚያንቋሽሽ፣ እዚህ አራት ኪሎ ያለውን ስርዓት ፊት ለፊት እየተጋፈጡ ያሉትን ወጣቶች ክብር የሚነፍግን ሙዚቃ ሲስተዋውቁ ስላየሁ ነው፡፡ ወጣቶቹ ቀንጨብ አድርገው ያስተዋወቁት የዘፈኑ ግጥም እንዲህ ይላል፡-
‹‹ቆርጠህ ተዋጋ ሁሌ አትንከርፈፍ፣
ለውጥ አላመጣም ሰላማዊ ሰልፍ፡፡››
በእርግጥ ይህ ሙዚቃ የግንቦት 7 መዝሙር አይደለም፡፡ ድርጅቱ እንደ ድርጅት ተወያይቶበት የተዘፈነም ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰላማዊ ትግሉን አንቋሽሾ ትጥቅ ትግሉን ለማግነን የተዘፈነ ዘፈን ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የግንቦት 7 ወጣቶች ሲያስተዋቅቁትም የድርጅቱ ሰዎች በአንድም ይሁን በሌላ በኩል ቅርበት እንዳላቸው እንደሚያውቁትም ያሳያል፡፡ ይህ እንኳን ባይሆን ሰላማዊ ታጋዩን ‹‹ከርፋፋ›› እያለ የሚሰድብን ሙዚቃ ማስተዋወቃቸው እነሱም ተመችቷቸዋል ማለት ነው፡፡
እንደኔ ጥፍር የሚነቅልን፣ ኢትዮጵያውያንን ከገዛ ሀገራቸው ዘርፎ የሚያፈናቅልል፣ የሚገድልን፣ የሚመዘብርን ስርዓት ሰላማዊ ትግል አያስፈልገውም፣ ትጥቅ ትግል አያስፈልገውም እያሉ ለእሱ የትግል ስልት መመጠን በእጅጉ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡ በደልም ነው! ይህ ሁሉ በደል እየተፈፀመ የፈለገው ያዋጣኛል ባለው ስልት ቢገጥመው ተቃዋሚ ነኝ ለሚለው ሊያስጨንቅ ይገባል ብዬ አላምንም፡፡ ሌላው ሌላው ቀርቶ የራሱ የስርዓቱ ካድሬዎች የሚያደርጉትን የውስጥ ትግልም መደገፍ ብልጥነት ነው፡፡ የራሱ ካድሬዎች በየ ስብሰባው የሚያሰሙትን ቅሬታ እያጋነን እንዴት ነው ግንባራቸውን ለጥይት የሰጡትን ልጆች ‹‹ከርፋፋ›› እያልን የምንሰድበው?
እኔ እስከገባኝ ድረስ ማንቃት፣ ራስን ማስተዋወቅ፣ ህዝቡንም ማደፋፈር ለትግሉ ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰላማዊ ሰልፍ፣ ስብሰባ….. ሌሎችም ሌሎችም አጋጣሚዎች እጅጉን አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ‹‹እኔ የግንቦት 7 ወታደር ነኝ›› እያሉ በድፍረት የሚናገሩት እነ ብርሃኑ፣ ፍቅረማሪያምና እየሩስ ተስፋውኮ ከምንም የመጡ አይደለም፡፡ የ‹‹የትጥቅ ትግሉን›› ሲገፉ ይምረጡት እንጅ በሰላማዊ ትግሉ ነቅተው፣ ተሞርደው የወጡ ሰዎች ናቸው፡፡ ‹‹ከርፋፋ›› የሚለው ሙዚቃ ግን የሚሳደበው እነዚህን ወጣቶች ጭምር ነው፡፡ ምክንያቱም በርካታ ሰልፎችን ተሳትፈዋልና፡፡ በአሁኑ ወቅት በስብሰባ ወይንም በሰላማዊ ሰልፍ መንግስት ይገለበጣል ብሎ የሚያስብ ያለ አይመስለኝም፡፡ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ የሚጨበጥና የሚታይ ለውጥ ባያመጡ እንኳ ተደማምሮ ግን ለትግሉ ትልቅ ግብዓት ይኖራቸዋል፡፡ ነገሮች ሲመቻቹ ደግሞ ራሱ ሰልፍና ስብሰባም ቀላል የማይባል ሚና እንዳለው በተለያዩ ሀገራት የታየ ሀቅ ነው፡፡
ግንቦት 7 ‹‹ሁለገብ ትግል›› እንደሚከተል በተለያዩ ጊዜያት ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ ሁለገብ ትግል ደግሞ ሰላማዊ ሰልፍን፣ ስብሰባን፣ የስራ ማቆም አድማን…..እና ሌሎች የሰላማዊ ትግል ስልቶችን ያጠቃልላል፡፡ ከወራት በፊት ንቅናቄው ከሰጠው መግለጫ መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
‹‹…ከዛሬ ጀምሮ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደዝንባለውና አቅሙ በሚመቸው የትግል ዘርፍ ይሳተፍ። …..ድርጅታችንን እያጠናከርን ወያኔን ከሁሉም አቅጣጫ እንሸርሽረው፣ እንገዝግዘው። በዚህ መንገድ በሚደረግ ሕዝባዊ ትግል የሚገኝ ድል ፈጣን ከመሆኑን በላይ የድሉ ሕዝባዊነት ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ይሆናል።››
ይህ እንግዲህ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ወይንም በየ ክፍለ ሀገሩ የስርዓቱን ወታደር፣ ፖሊስና ደህንነት ሳይፈራ፣ ሌሎቹንም ወገኖቹን ለማነቃቃት ሰልፍ የሚወጣውን ያጠቃልላል፡፡ ነገር ግን አዲስ በሚወጣውና በቀዳሚነት የግንቦት 7 ወጣቶች እያስተዋወቁት ያለው ሙዚቃ ‹‹ከርፋፋ›› ይለዋል፡፡ በእርግጠኝነት ከዚህ ሙዚቃ የገንዘብ ትርፍ ሊገኝበት ሳይሆን ሆን ተብሎ የትጥቅ ትግሉን ለማገዝ የወጣ ነው፡፡ ያ ሲሆን ግን ‹‹ሁለገብ›› ለተባለው ትግል አንድ አካል የሆነውን ሰላማዊ ትግል ‹‹ከርፋፋ፣ ለውጥ ያላመጣ›› እያለ ዘልፎታል፡፡
ከዚህ ባሻገር ግንቦት 7 በተደጋጋሚ ‹‹ትጥቅ ትግሉ ተገደን የገባነበት ነው›› ብሏል፡፡ እሱም ብቻ ሳይሆን ሀገር ውስጥ ያለው ህዝብ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችልና ዋነኛውም ሀይል ያለው ሀገር ውስጥ መሆኑን እንደሚያምን መግለጫዎቹን መመልከት ይቻላል፡፡ ይህ በሆነበት ግን እሱ ያራምደዋል የሚባለውን ‹‹ትጥቅ ትግል›› ለማበረታታት በቅርቡ ይወጣል የተባለው ሙዚቃ ሀገር ውስጥ ያለውን ትግል (ሰልፍ) ከርፋፋ ሲል እየዘለፈ ነው፡፡ አባላቱም ይህን ሙዚቃ እያስተዋወቁ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ሀገር ውስጥ የሚደረገውን ትግል መተቸት አንድ ነገር ነው፡፡ በተለይ ሰላማዊ ሰልፎቹ በሚገባ የተቀናጁ እንዳልሆኑና ሌሎቹንም ነገሮች ነቅሶ ማውጣት ለትግሉም የሚጠቅም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሰልፍ የሚወጣውን ሁሉ ‹‹ቀርፋፋ›› ማለት፣ ሰላማዊ ሰልፍ አያወጣም ብሎ መደምደም የሚያስተዛዝብ ይሆናል፡፡ ይበልጡን የሚያስተዛዝበው ደግሞ ግንቦት 7ን የሚደግፉ፣ ወይንም ስርዓቱን የሚቃወሙ ሰልፎች አሁንም በየ ኤምባሲው በር እየተደረጉ መሆኑ ነው፡፡ ስብሰባዎችም በየ ቦታው ይደረጋሉ፡፡
ነው ከአሁን በኋላ በአሜሪካና በአውሮፓ ሰልፎች አይደረጉም? የተሳኩትን የሰማያዊ፣ የአንድነት፣ የመድረክ ሰልፍና ስብሰባዎች አላደነቅንም? አልደገፍንም? ባህርዳርና በደቡብ ክልል ከተማዎች ህዝብ ሰልፍ ሲወጣ መግለጫ አልወጣም? አላበረታታንም? የሙስሊም ወጣቶች ያደረጓቸውን ሰልፎች አልደገፍንም? ለውጥስ አላመጡም? አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም የተጠራው ሰልፍ ላይ ወጣቶች ስርዓቱን ሲቃወሙ አላንቆለጳጰስናቸውም? የትኛው ሰልፍን ነው ቀርፋፋ የምንለው? በስርዓቱ አፈና ያልተሳኩትን? እናቶች የተደበደቡበትን? ሰልፈኛና ሰልፎቹን ከመተቸት ሰልፍ እንዳይደረግ ያገደውን፣ ሰልፈኛውን የሚደበድበውን ስርዓት ላይ ብናተኩር አይሻልም?
ከላይ እንደጠቀስኩት ግንቦት 7 ሰብሰባን፣ ሰልፍን…. በሚያጠቃልለው ሰላማዊ ሰልፍንም ጭምር ያምናል፡፡ ሆኖም ግን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እሱ ይመራበታል ያለውን ትግል ለመደገፍ በአባላቱ እየተዋወቀ ያለው ሙዚቃ ግን ‹‹ሁለገብ ትግል›› አያዋጣም የሚል ነው፡፡ ይህ በመርህ ለሚያምን ድርጅት የመርህ ጥሰትም ጭምር ነው፡፡
በጣም የሚገርመው ደግሞ ህወሓት/ኢህአዴግ ኤርትራ ውስጥ ከነበረው ታጣቂ ቡድን ጋር ለአንድ አመት ያህል በሰራሁት ስራ፣ ብርሃኑ ነጋን አስገድጄ ወደ ኤርትራ አስመጥቼ…….. እያለ እዛው ትጥቅ ትግሉ ውስጥ ከነበረው ሰው ጋር በሚያብርበት በአሁኑ ወቅት ይህን ስርዓት የሚታገሉትን የሚያሸማቅቅ ዘመቻ መጀመሩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ሰላማዊ ትግል ላይ ያሉት (የፓርቲ አመራሮችም ጭምር) የአቶ ሞላን መክዳት ተከትሎ ‹‹ግንቦት 7›› እንባላለን ብለው ሳይፈሩ፣ በሁለቱም ትግሎች መካከል ድንበር ሳይለዩ ክስተቱን ክህደት ብለው ተናግረዋል፡፡ ስርዓቱ የሚያደርገውን ፕሮፖጋንዳም አምርረው ተችተዋል፡፡ ለእነሱ ግን ሰላማዊ ሰልፍ አንዱ የግትል ስልታቸው ነውና ‹‹ቀርፋፎች›› የሚል ዘፈን ሊደለቅላቸው ነው፡፡
እነዚህ ወጣቶች የሚያዘጋጁትን ሰልፍ ለውጥ አያመጣም፣ እነሱንም ‹‹ከርፋፋ›› ማለት ግን ስርዓቱን ከመደገፍ ለይቼ አላየውም፡፡ ምክንያቱም ህወሓት/ኢህአዴግም መስቀል አደባባይን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹን አካባቢዎች ለሰልፍ የማይፈቅደው፣ የተቃዋሚዎችን ሰልፍ በአንድም ሆነ በሌላ ነገር ህገ ወጥ ለማድረግ የሚጥረው፣ የሚደበድበውና የሚያስረው ሰልፍም ለውጥ ስለሚያመጣ ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ሰልፍ ባይደረግ፣ የባህርዳር ህዝብ ሰልፍ ባይወጣ ለማን ነው የሚጠቅመው? ስርዓቱን የምንቃወመው ምን እንጎዳለን? በምን መመዘኛ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ሊዘመት ይችላል?
ይህ አሁን ‹‹ከርፋፋ›› በሚል የተጀመረው ዘለፋ እያደር ወደ ሌላ ነገር እንዳይሄድ እፈራለሁ፡፡ በተለይ ከድርጅቱ መርህም ጭምር እያፈነገጠ፣ እያፈነገጠ ከስርዓቱ ጋር ያለውን ትቶ ከተቃዋሚዎች ጋር ያለው ግንኙነት መንገዱን እንዳይስት ትልቅ ስጋት አለኝ፡፡ ወደድንም ጠላንም በ‹‹ትጥቅ ትግል›› ብቻ ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ይመጣል ብንል እንኳ ብናስብ ሀገር ውስጥ ሰልፍም እያደረጉ፣ ሰብሰባም እየጠሩ ያሉት ጋር አብሮ መስራት ካልተቻለ መሰረታዊ ለውጥ አይመጣም፡፡ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ደግሞ ለቃል ከመጠንቀቅ፣ ለሌላው ታጋይ እውቅና ከመስጠት ይጀምራል፡፡
