በሚኒስቴሩ የምክክር መድረክ: በመልካም አስተዳደር ላይ የተያዙት የጋራ አቋሞች በአቀራረብ ጫና እንደተደረገባቸው ተገለጸ

  • ተሸራርፈው እና ተገልብጠው ጎልተው እንዳይወጡ መደረጋቸውን ዳይሬክቶሬቱ ገምግሟል
  • “የመልካም አስተዳደር ድምፃችን አልተሰማም፤ ውክልናችንም አንሷል” (ሰንበት ት/ቤቶች)
  • ምክክሩ፣ በሀገረ ስብከቱ የሰባቱ ክፍላተ ከተማ እና በሌሎችም አህጉረ ስብከት ይቀጥላል

(ሰንደቅ፤ ፲፩ኛ ዓመት ፭፻፳፪፤ ረቡዕ፣ ጳጉሜን ፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

Ethiopian Ministry of Federal Affairs

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት 170 አድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች በተገኙበት የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ለኹለት ቀናት የምክክር መድረክ አካሒዷል፡፡ ተጨማሪ የውይይት መድረኮችም፤ በአዲስ አበባ ሰባት የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት እና በአህጉረ ስብከት ለማድረግ ማቀዱንም ገልጿል፡፡

ነሐሴ ፳፱ እና ፴ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ አዳራሽ በተካሔደው የምክክር መድረክ ላይ፤ በሰላም አብሮ መኖርና ዕሴቱን ለትውልድ ከማስተለለፍ አኳያ ቤተ ክርስቲያን በዕቅድ እየተመራች ስለ መኾንዋ፣ ስለ አክራሪነትና ጽንፈተኝነት ጉዳይ እንዲኹም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስላለው ጤናማ ተቋማዊ ግንኙነት በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ተሳታፊ ልኡካን የቡድንና የጋራ ውይይት አድርገዋል፡፡

በመጀመሪያው ነጥብ ላይ፣ ቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተልእኮዋ ስለኾነው ሰላም እና አብሮ የመኖር ወርቃማ ዕሴቶቻችን አዘውትራ ብታስተምርም ሥራዎች በዕቅድ ተይዘው መከናወን እንደሚገባቸውአክራሪነትንና ጽንፈኝነትን በተመለከተ በ“ዘመናዊ ኪራይ ሰብሳቢነት እና ሙስና” መልኩ ተጋላጭነቱ እንዳለ ድምዳሜ ላይ መደረሱን አቶ ትእዛዙ ደለለኝ፣ በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል፣ የሰላም እና መከባበር መስፈን ዳይሬክሬቶሬት ዳይሬክተር ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡

ሦስተኛውን ነጥብ ማለትም፤ በቤተ ክርስቲያንዋ ጤናማ ያልኾነ ውስጣዊ ግንኙነት መስፈኑን በተመለከተ፣ በቡድን ውይይት ወቅት ከፍተኛ ክርክር እና የሐሳብ ልውውጥ መንጸባረቁን አቶ ትእዛዙ አረጋግጠዋል፡፡ ከአሳታፊ እና ዘመናዊ አሠራር አኳያበውሳኔ አሰጣጥ ካህናትንና ምእመናንን በማዳመጥ እና በማሳተፍ፤ በቅጥር፣ ዕድገት እና ዝውውር ወቅት ሰዎችን በብቃት በመመዘንና ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛ ቦታ በመመደብ ረገድ ከፍተኛ ጉድለቶች እንዳሉ መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮች “ድምፃችን አልተሰማም፤ ውክልናችንም አንሷል” የሚሉ አቤቱታዎችን ለፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አቅርበዋል፡፡ በጋራ መድረኩ ውይይት ወቅት ከመልካም አስተዳደር አንጻር ያቀረቧቸው ሐሳቦች በቡድን ሪፖርቱ እንዳልተካተቱ ያጋለጡት ተወካዮቹ፣ የተሳትፎ ቁጥራቸውም ጥሪ ከተደረገላቸው 170 አድባራት ውስጥ ከኻያ ያልበለጠ መኾኑን በመጥቀስ ውክልናው በቂ እና ትክክል አለመኾኑን በመጥቀስ አመልክተዋል፡፡

አቶ ትእዛዙ እንደገለጹት፣ ለመሰል ውይይት ካለው የልምድ ማነስ አኳያ የምክክር መድረኩ ጅምር በመኾኑ ችግሮቹ እንደሚገባው ነጥረው ሊወጡ እንዳልቻሉ፣ ክንውኑን በገመገመው የሚኒስቴሩ የሃይማኖት እና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በኩል ታይቷል፡፡ ይህም በአንዳንድ ቡድኖች አቀራረብ ላይ፣ የጋራ አቋሞች በአብዛኛው ተሸራርፈው እና ተገልብጠው ጎልተው እንዳይወጡ በማድረጉ ጫና የደረሰ የሚመስልበት ኹኔታ መታየቱን በሚኒስቴሩ በኩል ግንዛቤ መያዙን አቶ ትእዛዙ አመልክተዋል፡፡

ተጨማሪ የምክክር መድረኮች፣ በሀገረ ስብከቱ ሰባቱም የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት እና በሌሎችም አህጉረ ስብከት ከሚመለከታቸው ሓላፊዎች ጋር በመነጋገር እንደሚዘጋጁ አቶ ትእዛዙ አስታውቀው፤ ከዚኽ በኋላ በሚኖሩ ተመሳሳይ መድረኰች መሻሻሎች ይኖራሉ ብለን እንጠብቃለን ብለዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንዋ በውስጥዋ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በራስዋ እንድትፈታ ፍላጎቱ መኾኑንና ለዚኽም ውጤታማነት አብሮ እንደሚሠራ ሚኒስቴሩ አረጋግጧል፡፡ የሚኒስቴሩ ቅድሚያ ትኩረት ማስተማር መኾኑንና ወንጀል ከተሠራ ግን የሕግን የበላይነት ለማስከበር የሚያግደው በር እና አጥር የለም፤ ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
His Holiness at Civil service college
በምክክር መድረኩ መዝጊያ ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ÷ የውስጣዊ ሰላም ጠንቆች፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለው አሠራር፣ ሕግንና ሥርዐትን ማእከል ያላደገረ የሥራ አፈጻጸም፣ የቤተ ክርስቲያንን ሳይኾን የራስን ጥቅም ማስቀደም እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡

የእኒኽ ውስጣዊ ጠንቆች መፍትሔዎችም፤ የኅሊና መሥዋዕትነትን በመፈጸም መልካም አስተዳደርን ማስፈን፤ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፤ የቤተ ክርስቲያንንና የሕዝብን ሉዐላዊነት ማስቀደም፤ ብክነትንና ዝርክርክነትን መጠየፍ እንደኾኑና ሓላፊዎች፣ ሠራተኞችና አገልጋዮች በግንባር ቀደምነት ሊተግብሯቸው እንደሚገባ ቅዱስነታቸው በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡