የፌዴራል ጉዳዮች የመልካም አስተዳደር ውይይት: ዓላማውንና ሒደቱን በሚቃረኑ ዝብረቃዎች ተጠቃለለ፤ አማሳኞች የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ አጠልሽተውበታል
- የቡድኖች ማጠቃለያዎች፣ ውይይቱን የማያንጸባርቁ እና የጋራ አቋሞችን የማይወክሉ ነበሩ
- አክራሪነት እና ጽንፈኝነት፣ በሚኒስቴሩ ከተሰጣቸው ትርጉም እና ማብራሪያ ውጭ ውለዋል
- ለመልካም አስተዳደር የተሰጠው መድረክ በቀማኞች የስመ አሸባሪ ዝባዝንኬዎች ተጠልፏል
- የሰንበት ት/ቤቶች እና መንፈሳውያን ማኅበራት በአክራሪነት እና በጽንፈኛነት ተፈርጅዋል
* * *
- ጥሪው በአማሳኞቹ በመጠለፉ ከ169 አጥቢያዎች 20 የሰንበት ት/ቤት አባላት ብቻ ተገኝተዋል
- ሕጋዊው የሰሚት መድኃኔዓለም ሰ/ት/ቤት ልኡክ፣ በየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እየተገፈተረ ተባሯል
- የቡድን ማጠቃለያዎቹ እንደማይወክላቸው ለሚኒስትሩ የተናገሩ ሲኾን ሌላ መድረክም ይዘጋጃል
- አማሳኞች በሕግ እንዲጠየቁ ለተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል
* * *
- ዐሥሩንም ቡድኖች ያወያዩት የሚኒስቴሩ ባልደረቦች ቢኾኑም፤ የማጠቃለያ ሪፖርቶቹ በዘባራቂው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በተመረጡ እና ‘ረዳት’ በተባሉ አማሳኞች ተዛብተው መቅረባቸው፣ የጋራ መድረኩ በንቃት እና በባለቤትነት እንዳልተመራ አሳይቷል፡፡
- በውይይቱ መክፈቻ፣ በቤተ ክርስቲያናችን ከአክራሪነት ይልቅ ያለው ዋነኛ ችግር የመልካም አስተዳደር ነው ያሉት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው፣ የግልን ችግር ለመሸፈን ሲባል ‘ጽንፈኛ’ እያሉ ማኅበራት ላይ እየጮኹ ማስቀየስ ተገቢ እንዳልኾነ ተናግረው ነበር፡፡
- የአመራሩ ተሰሚነት እና ተደራሽነት የሌለበት፤ የካህኑና የምእመኑ መብት ያልተለየበት፤ የአሠራር ሒደቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያልተረጋገጠበት ተቋማዊ ችግር በአስቸኳይ ካልተስተካከለ ችግር ፈጣሪውም ተጎጂ እንደሚኾን ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
- በቡድን ውይይቱ፣ ማኅበራትንና ሰንበት ት/ቤቶችን በጽንፈኝነትና በአክራሪነት የወነጀሉት አማሳኞቹ፣ በሚኒስቴሩ የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር፤ እርማት እና ተግሣጽ ተሰጥቷቸዋል – “ጽንፈኝነት እና አክራሪነት ምን እንደኾነ ካልገባችሁ አትናገሩ! ዝም በሉ!”
አንዱ የቡድኑ አባል፣ ማኀበሩ ጽንፈኛ ነው፤ ሰንበት ተማሪውን ዩኒፎርም አስለብሶ ያሰልፋል እያለ ያወራ ነበር፤ በአጋጣሚ ሐጂ የሚሏቸው የሃይማኖት እና እምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬቱ መጥተው ቆሙ፤ ቆይ እስኪ ያቁሙ አሉት፤ ጽንፈኛ ምንድን ነው ትርጉሙ? አክራሪነት ምን ማለት እንደኾነ ታውቁታላችኹ? ብለው ጠየቁ፡፡
እነዚህ ዩኒፎርም ለብሰው ሰልፍ ወጡ የምትሏቸው፣ ጠይቀዋችሁ ሳትመልሱ ስትቀሩና ሲቃወሟችሁ ጽንፈኞች ናቸው፤ አክራሪዎች ናቸው ማለት አትችሉም፤ ወጣት እውነትን ይፈልጋል፤ አሳትፉኝ ይላል፤ ይጠይቃል፤ የሕዝብን ሀብት አላግባብ ስታውሉት ማን ዝም ይላችኋል! ጽንፈኝነት እና አክራሪነት ምን ማለት እንደኾነ ካልገባችሁ አትናገሩ! ዝም በሉ! ማኅበሩ፣ ማኅበሩ የምትሉት ማኅበሩን እኛ ነን እንዴ ዕውቅና የሰጠነው? የቤተ ክርስቲያን አባቶች ናቸውኮ ዕውቅና የሰጧቸው፤ ስለዚህ ማኅበሩ አልተማረም ስትሉ አባቶች አልተማሩም እያላችሁ ነው፤ ምንድን ነው እንደዚህ የምትነጋገሩት፤ አትደባበቁ !!!
* * *
- ንጹሕ መስለው ለመታየት የሞከሩት እነኃይሌ ኣብርሃ፣ ዘካርያስ ሐዲስ እና የተወሰኑ ጸሐፊዎች÷ ምዝበራቸው ፊት ለፊት እየተጋለጠ፣ የመከላከል ዐቅም አጥተው ራሳቸውን እያከኩ እና ወለሉን በእግራቸው እየተመተሙ ቁም ስቅላቸውን አይተዋል፤ የሚኒስቴሩ የቡድን አወያዮች ግን ስለ እነርሱ ይሸማቀቁ ነበር፡፡
- “ኃይሌ÷ ማኅበሩ እና ሰንበቴዎች በጠበጡን፤ ይላል፤ እኛም መቶ ሚሊዮን ብር የሚዘርፍ አለቃ እኮ ነው ያለው እንላለን፤ በአንዳንድ አጥቢያዎች ዐውደ ምሕረቱን የያዙ የያዙ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንን እንቃወማለን፤ አወያዮቹም፤ እነዚህ ናቸው ወይ ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩት ይላሉ፡፡”
- በበርካታ ሱሶች ቀልቡን ያጣውና በቢሮ ውስጥ ሳይቀር አጸያፊ ተግባር የሚፈጽመው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ሕጋዊውን የሰሚት መድኃኔዓለም የሰንበት ት/ቤት ልኡክ፣ “የሰንበት ት/ቤቱ ተበትኖ የለም እንዴ? በየምናኑም ተሰብሰብ፤ አያገባኝም፤ ቤተ ክርስቲያኗ ግን አታውቅህም” ብሎ ከአዳራሹ እየገፈተረ አባሮታል፡፡
- በቤተ ክርስቲያኒቱ ይኹን በማኅበራት አክራሪነት እንደሌለና ለመልካም አስተዳደር ትኩረት በተሰጠበት ኹኔታ የሊቅነትን ካባ ለራሱ የደረበው ዘብራቂው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ “አሸባሪው ዒላማ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ፓትርያርኩን፣ ሰንበት ተማሪውንና ስብከተ ወንጌሉን ነው፤ ማን እንደሚያስተምራቸው፣ ገንዘባቸው አይታወቅም፤ ይህን ለሚጠይቅም ስም ይሰጣሉ” ሲል በፈጠራ ዘባርቋል፡፡
- በርካታ ሰበካ ጉባኤያት በአማሳኝ አለቆች እየታገዱ አድባራቱ ያለከልካይ ለምዝበራ ሲጋለጡ ምላሽ የማይሰጠው የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ከምክትል ሊቃነ መናብርቱ ጀምሮ የሰበካ ጉባኤ አባላቱን፣ “በማኅበር ተደራጅተው ይመጣሉ፤ የራሳቸውን አስተሳሰብ በሰው ላይ እየጫኑ ያስፋፋሉ” እያለ በአክራሪነት ለመፈረጅ ይዘባርቃል፡፡
- እውነታው ግን፣ ዋና ጸሐፊነትን ደርቦ በያዘበት አራዳ መናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር፣ ነበር – የሰበካ ጉባኤ – የቁጥጥር – የልማት ኮሚቴ እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት፣ በዲዛይን ክለሳ ስም ያለጨረታ አማካሪ መሐንዲስ በመቅጠር ከብር 100 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ለምዝበራ እና ብክነት ማጋለጡ ነው፡፡ በትላንቱ ዝብረቃው ታዲያ፣ ይኸው ዘረፋው በማስረጃ የተረጋገጠበትን ጥናታዊ ሪፖርት ነው በፓትርያርኩ ፊት ለማጠልሸት ሲዘባረቅ የነበረው፡፡
