“አዲሱ ዓመት…የብልግና ይሁንልዎ!” የሚል የባለስልጣን ምኞት ካነበብክ፥ አትደንግጥ ! ያለኸው ኢትዮጵያ ነውና
“አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የዕድገትና የብልግና ይሁንልዎ!” (የብልግና ላይ አስምረን አልፈናል)
የሚል የከፍተኛ ባለስልጣን ምኞት ካነበብክ፥ አትደንግጥ።
ያለኸው ኢትዮጵያ ነውና፣ ይከሰታል። ልታነብ ትችላለህ።
Yohanes Molla

የወዳጆች ማኅበር ስብሰባ ፍቃድ እንኳን ስንት እክል ሊገጥመው በሚችልበት አገር ውስጥ፥ “በመዲናው የሚገኙ የሌላ አገር ስደተኞች (ያቺ አገር በፊት አብራ የነበረችና የተ(ስ)ገነጠለች። ባለው ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ሁለቱ አገራት ባላንጦች መስለው የሚታዩበት) የትጥቅ ትግል የጀመሩበትን 54ኛ ዓመት አከበሩ” የሚል ዜና ከሰማህም ብዙ አትገረም። ወላ “ታጥቀው ታግለው ላለቀ ነገር፣ ጅማሮውን ከማክበር ይልቅ ምናለ የድሉን እለት…ቢባል” ብለህ እንኳን አትብሰልሰል።
ያለኸው ኢትዮጵያ ነውና ጊዜ ከሰጠህ ሌላም ትሰማለህ። (ደግሞ መብሰልሰሉም አደጋ አያጣውም።) ሰው የልቡን እያስታጠቀህ፣ ለተቀበልከው አስተያየት የራስህን አስተያየት ስታክልና ያንተን ሀሳብ በቅንነት ለማብራራት ስትሞክር…“አንተ እኮ አስተያየት አትቀበልም። ችኮ መንቻኮ። ተከራካሪ ነህ።” ቢሉህም ብዙ አትደነቅ። ያለኸው ኢትዮጵያ ነውና ይገጥምሃል። በኃይል ያከበርከው ሰው ራሱን ቁልቁል ፈጥፍጦ ከከበሬታህ ላይ ራሱን የማጥፋት (suicide የመፈፀም) ጥረት ሊያደርግ ሲሞክር ካየህ አትዘን።
“ወዳጄ” ስትለው ከጀርባህ የምላስ ጎራዴውን ጨብጦ፣ ስጋህን ለመዘልዘል መድከሙን ብታውቅም ልብህ አይሰበር። ያለኸው ኢትዮጵያ ነው፤ ብዙው ካኖሩት አይገኝም። ሌላ ሌላም ብዙ ነውር ታያለህ። – ከኗሪውም፣ ከገዢውም! ኢትዮጵያ ውስጥ ነህና፥ ቢከብድህም ትችለዋለህ! በዚያ ላይ “ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ” እንለው ተረትም አለና፥ ቡሄ ካለፈ የምትሰማው ጉድ ቢበረታብህ ግር አትሰኝ። ያለኸው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው! ቻለው ወዳጄ!