አቤል አፍሬም ማን ነው? በእነ ብርሃኑ ላይ ለምን መሰከረ?
አቤል አፍሬም ይባላል፡፡ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ነው፡፡ አቤል ሰማያዊ ፓርቲን ከተቀላቀለ ጀምሮ በገዥው ፓርቲ ደህንነቶችና ፖሊሶች ከፍተኛ ድብደባና ጫና እንደ ማንኛውም የፓርቲው አባላት ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ አቤል ሰማያዊ በሚያዘጋጃቸው ሰልፎች ላይ ሁሌም ከፊት መቆም የሚወድ እና ገፈቱን ለመጎንጨት የማያመነታ ቆራጥ ልጅ ነው፡፡ የዚህን እውነተኛነት ለማረጋገጥ የሰልፎቹን ቪዲዮዎች መለስ ብሎ ማየት ይቻላል፡፡
ነሃሴ 25 ቀን 2005 ዓ.ም ለሰልፍ በምንሰናዳበት ምሽት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፖሊሶች ቢሯችን ሰብረው ገብተው ወደ ጃንሜዳ ፖሊስ ጣቢያ በመጫን እስከ ጉልበታችን ድረስ የሚውጥ ጭቃ ውስጥ አስገብተው ሲደበድቡን እንደ አቤል ከፍተኛ ድብደባ የደረሰበት ሰው አልነበረም፡፡ እርግጥ ነው ትዕቢተኛ ነህ በሚል ዮናታን ተስፋዬም እንዲሁ ከሌሎች በተለዬ መልኩ ወደ ኋላ እንዲቀር ተደርጎ ከፍተኛ ድብደባ ደርሶበት ነበር፡፡ አስታውሳለሁ በማግስቱ ቢሮ ስንገናኝ አቤል ማታ ለብሶት የነበረውን በጭቃ የተለወሰ ልብሱን አድርጎ ነበር የመጣው፡፡
ሌላው ሰማያዊ ፓርቲ ህዳር 27 እና 28 ቀን 2007 ዓ.ም ጠርቶት የነበረውን የአዳር ሰልፍ ተከትሎ አቤል በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ራሱን ስቶ ረጅም ሰዓት በመቆዬቱ ‹‹ሞተ›› ተብሎ ተወርቶ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሞቶ የተነሳውን አቤልን የቅርብ ጓደኞቹ ‹‹አላዛር›› ብለን እንጠራውም ነበር፡፡ አቤል ማለት ይሄ ነው፡፡ ማንም ቢሆን አቤልን ከፊት ለፊቱ ካደረገ የሚተማመንበት ውድ ልጅ፡፡ ከኋላህም ቢሆን አቤልን ለማድረግ የማታመነታበት ቆራጥ ታጋይ፡፡
ብርሃኑ ተክለያሬድ፤ ፍቅረማርያም አስማማው፤ አቤል ኤፍሬም እና እየሩሳሌም ተስፋው በሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ጉልህ የሆነ አስተዋጽኦ የነበራቸው ወጣቶች ነበሩ፡፡ የኋላ ኋላ ግን የትግል ስልታቸውን በመቀየር ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀሉ ሲሄዱ አቤል ባህርዳር ላይ ተመለሰ፡፡ የተመለሰበትን ጉዳይ ለራሱ እንተውለትና ስለሆነው ነገር እንነጋገር፡፡
አቤል ከባህርዳር እንደተመለሰ እነ ብርሃኑም ተይዘው ማዕከላዊ መሆናቸው ተሰማ፡፡ ከፍተኛ የፍርሃትና የመደንገጥ ድባብበ አረፈብን፡፡ ‹‹ጸበል እና ሱባኤ ነው የሄድነው›› ያሉት ጓደኞቻችን ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል ሲሉ ተይዘው መጡ ተባለ፡፡ነገርየው ዱብ እዳ ሆነ፡፡ የመያዛቸው ወሬም አየሩን ሞላው፡፡ እነ ብርሃኑ ፍርድቤት ቀርበው ክሳቸውን እስኪያኑ ድረስ ውስጥ ውስጡን በሹክሹክታ ወሬው ደራ፡፡ በኋላ ግን እነ ብርሃኑ የተከሰሱበትን ‹‹ግንቦት ሰባትን ሊቀላቀሉ ሲሉ ተያዙ›› የሚለውን ክስ አምነው ነገር ግን ‹‹ግንቦት ሰባት ነጻ አውጭ እንጅ አሸባሪ ድርጅት አለመሆኑን›› ጠቅሰው ተከራከሩ፡፡ በዚህም የተነሳ ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል እንደሄዱ በራሳቸው ላይ መሰከሩ፡፡ ይህንን አቋማቸውን ፍርድቤት ከመናገራቸውም አልፈው ለሚዲያ በጻፉት ደብዳቤ ግልጽ አድርገው ነበር፡፡
አቤል እነ ብርሃኑ ማዕከላዊ በነበሩበት ወቅት በተደጋጋሚ እየተጠራ ሌሊቱን ሙሉ ይገረፍ ነበር፡፡ ከዚህ አልፎ አንድ ቀን በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ የቀኝ ኩላሊቱ ደም በመፍሰሱ ደብዳቢዎቹ ምኒልክ ሆስፒታል ጥለውት ሄዱ፡፡ይሁን እንጅ ለህክምናው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ባለማግኘቱ ወደ ቤቱ ከመሄድ ውጭ አማራጭ አልነበረውም፡፡ አቤል እስካሁንም ቢሆን ኩላሊቱ ኦፕራሲዮን እደሚያስፈልገው የተነገረው ቢሆንም በገንዘብ እጥረት ህክምናውን ማግኘት አልቻለም፡፡ ከሚሰራበት መስሪያ ቤት የተባረረው አቤል ለህክምና የሚሆን ገንዘብ ባለማግኘቱ ብቻ የኩላሊት ህመሙን ተሸክሞ ከእናቱ ቤት ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን አቤልን በስልክ ያጽናናው፤ በአካል አግኝቶ አይዞህ ያለው ማንም የለም፡፡ ስማቸውን መጥቀስ ባያስፈልገኝም ከሁለት የማይበልጡ ልጆች ብቻ አበረታተውታል፡፡ ይሄ ሁሉ ከሆነ በኋላ ነው አቤል ለምስክርነት ወደ ፍርድቤት የተጠራው፡፡ በነገራችን ላይ አቤል ከመመስከሩ በፊት ቅሊንጦ ሄዶ ፍቅረማርያምን አግኝቶት ‹‹ምን ብሎ መመስከር እንዳለበት›› ሁሉ ተነጋግረዋል፡፡ አለፍ ሲልም አቤል ለፍርድቤቱ ያስረዳው ነገር በሙሉ ተከሳሾቹ ያመኑበት ነገር ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን መመለስ የሚገባቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ አቤል ባህርዳር ላይ ለምን ተመለሰ? ብርሃኑ ስለ አቤል ምን አለ? ፍቅረማርያም በአቤል ጉዳይ የሰጠው አስተያየት ምን ነበር? እየሩስስ ስለ አቤል ምን ትላለች? አቤል ላይ ከመፍረዳችን በፊት መልስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡
እነዚህን ጥያቄዎች በአዕምሯችን ይዘን አቤል ከደረሰበት ጉዳትና ወደፊትም ሊደርስበት ከሚችለው ጉዳት ጋር ተደማምሮ ተከሳሾቹ ‹‹ክሱን አንቃወምም›› ባሉበት ሁኔታ አቃቢ ህግ ለምን አቤልን ማስመስከር አስፈለገው? ይሄኛውም መልስ አልባ ጥያቄ ነው፡፡ ነገሩን ግልጽ አድርጋችሁ ማየት የሚገባችሁ ግን ተከሳሾቹ ያመኑበትን ነገር ነው አቤል ፍርድቤት ቀርቦ የመሰከረው የሚለውን ነው፡፡
በመጨረሻ ግን አቤልን ‹‹የአድዋ ትግሬ ስለሆነ ነው የመሰከረባቸው›› የምትለው መከራከሪያ ከዘር ጥላቻ የምትመነጭ ተራ የመንገደኛ መከራከሪያ መሆኗን ጠቁሜ ማለፍ እወዳለሁ፡፡ የአድዋውን ጌታቸው ረዳን ብታውቁት ኖሮ እንዲህ ባላላችሁ ነበር፡፡ አቤልን እንደ ቃዬል የምትመለከቱትም ብትሆኑ እነ ብርሃኑ ኤርትራ ድረስ ለመዝለቅ የበለጠ ያመኑት አቤልን በመሆኑ መከራከሪያችሁ አይደለም ውሃ በረዶም አይቋጥርምና ተውት፡፡ ዛሬ ቀን ጣለው ብላችሁ ጀግናውን አንበሳ እናንተ ዝንቦቹ መጫዎቻ ልታደርጉት አትኳትኑ፡፡ እንደ መውጫም አቤል ላይ ከመፍረዳችን በፊት ለጥቂት ደቂቃ ራሳችንን እሱ የቆመበት ጫማ ላይ አድርገን አንመልከት እላለሁ፡፡
ሻሎም!!!! Gashaw Mersha Z Gondar