ዛሬም ወደ ውስጥ የመመልከትን ‹‹ግርዶሽ ›› ካልገፈፍን– በተናጠል ፉከራ የትም አንደርስ ::Girma Bekele

ከሰሞነኛ የፌስቡክ ጉዳዮች የህወኃትና የአጃቢ ፓርቲዎቹ ጉባኤ በአዘናጊ መልኩ ሰፊ ቦታና ጊዜ እየወሰዱ ሲያነጋግሩ እየታዘብን ነው፡፡ ልክ የማናውቀው ህወኃት በጉባኤ ‹‹እሞትለታለሁ›› ከሚለው የህልውናው መሰረት የሆነውን ‹‹የከፋፍለህ ግዛ›› እና የ‹‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ›› ፖሊሲውን፣ የሴራ ፖለቲካውን ይለውጥ ይመስል፣ ወይም አጃቢዎቹ ከህወኃት ፈቃድ ውጪ በራሳቸው ይወስኑ ይመስል፤ ተከፋፈሉ፣ ተባሉ ወዘተ እየተባለ የሚባክነውን ጊዜ፣ገንዘብና ጉልበት በመገንዘብ ‹‹ ከፕሮፓጋንዳ ጡዘት እንላቀቅ::ስለ ሕወሓት መተካካት እና ስለ ብአዴን መሰነባበት ከምንደሰኩር ትግላችንን አጠናክረን በጋራ በአንድነት ሆነን ለሚፈናቀለው ለሚታሰረው እና ለሚገደለው ሕዝባችን እንድረስለት፡፡››የሚል ምክር የሚወረውሩ አድማጭ አላገኙም፡፡ ጡዘቱ ቀጥሏል ብቻ ሳይሆን ይቀጥላል ማለት ያስችላልና እኛ የእነሱን ለእነሱ ትተን ወደ ራሳችን ጉዳይ እንድንመለስ ያስፈልጋልና ይህችን ‹‹ ዛሬም ወደ ውስጥ የመመልከትን ‹‹ግርዶሽ ›› ካልገፈፍን– በተናጠል ፉከራ የትም አንደርስ//›› በሚል ርዕስ እየጻፍኩ ካለሁት ከዚህ በፊት ስለ መድረክና ሰማያዊ ጉባኤዎች ያቀረብኩት ትዝብትና ስጋት ቀጣይ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ጽሁፍ ወደ ቦታችን እንድንመለስና በጉዳያችን ላይ እንድናተኩር ለማሳሰብ ይህቺን ቀንጭቤ አቅርቤኣለሁና እንነጋገርበት፡፡ ሙሉውን ጽሁፍ ከሰሞኑ ይዤ እመለሳለሁ፡፡
‹‹ ……ዛሬም ታዛቢ፣ ጠያቂ የለም፤ ህዝብ እንደትናንቱ ‹‹የተቃውሞ ጎራውን›› በሰሞናዊ ሆይ-ሆይታ ይደግፋል፣ እስከ መጪው ምርጫ የደረሰበትን ሞትና ስቃይ ይረሳልና እንደተለመደው ለቀጣዩ ምርጫ አጃቢያችን ይሆናል፤…. በሚል ታሳቢ ከሆነ አያስኬድም፡፡ ህዝብ ውጤት የማያመጣ አላስፈላጊ መስዋዕትነት የሚከፈልበት ‹‹ምርጫ›› ላይ ተስፋ ቆርጧል፤ህዝብ ቀርቶ ከፓርቲ ቢሮ የወጡትን የፖለቲካ አመራሮች ‹‹ሞት/ስቃይ ካልቀረ የተለመደው የጦር ሜዳ የጀግና ሞት/ስቃይ ይሻላል›› የሚለውን መምረጣቸውን– እነ ብርሃኑን ከወህኒ፣ እነ ተስፋሁንን ከግንባር ለማስረጃ መጥቀስ በቂ ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡….. ጊዜው ለገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ለተቃዋሚውም ራሱን እንዲለውጥ ከሚያስገድድበት 11ኛው የለውጥ ሰዓት ደርሷል፤ ደወሉ ተደውሏል፤ …….ያለተጠያቂነት ሲጓዙ በተደጋጋሚ የከሸፉና ዛሬም በዚያው መንገድ ለሚጓዙና ለመጓዝ ለሚያስቡ፣ በህዝብ መስዋዕትነት የራሳቸውን ስምና ዝና ለመገንባት ለሚታትሩ ‹‹አይነኬ አመራሮች ›› ጀንበር ጠልቃለች፤ ተቃዋሚን መተቸት፣ መንቀፍ ‹‹ዋናውን ዓላማ›› መጉዳት ነው የሚለውም ሆነ የሚቃወሙትና የሚተቹት ላይ ታርጋ በመለጠፍ ህዝብን ማሳሳት ረፍዶበታል ሳይሆን መሽቶበታል፤ ጨዋታው በመረጃና ማስረጃ እየተደገፉ ህዝብን ከአላስፈላጊ መስዋዕትነት መታደግ ደረጃ ላይ ስለደረሰ ለውጥ የማያመጣና ተቃዋሚዎችን በተስማሙበት በአንድ የማያቆም የምንሳሳለትና ዋጋ የምንከፍልለት ‹‹ ዋና ዓላማ›› ብሎ ነገር የለም// ….›› ስለሆነም ትኩረታችን ሁላችን ስለምናተርፍበት በብሄራዊ መግባባትና እርቅ አልፎ ስለምንመሰርተው የሽግግር መንግስት እንዴትነት ላይ ቢሆን ‹‹ልፋ ያለው ገበሬ መንገድ ያርሳል›› ከሚለው የአበው አባባል ያተርፈናል፡፡ በቸር ያገናኘን፡፡