በደ/ጽጌ ቅ/ዑራኤል: የ6 ሚ. ብር የሕንፃ ገቢ ምዝበራ ጥያቄ ሳይመለስ ሌላ የሕንፃ ዕብነ መሠረት ሊቀመጥ ነው
- የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀ መንበር: “ባልተጣራ ሒሳብ እንዴት ሕንፃ ይሠራል?”
- የግንባታ ጥናቱ ከክፍያ ነፃ እንደተሠራ ቢነገርም የብር 250,000 ክፍያ እያነጋገረ ነው
- ሕግን መጣስ፣ ያለዕቅድ እና ያለጥናት ከፍተኛ ገንዘብ ማባከን የአስተዳደሩ መገለጫ ነው
- በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተካሔደው የምዝበራ እና ብክነት ምርመራ ውጤቱ አልታወቀም
- ነገ ዕብነ መሠረቱን የሚያስቀምጡት ፓትርያርኩ ኹኔታውን እንዲያጤኑት ተጠይቋል

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ነገ ነሐሴ ፳፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው፣ የሕንፃ መሠረት ደንጊያ እንዲያስቀምጡ መርሐ ግብር ተይዞላቸዋል፡፡
በቀድሞው ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የታቀደው ግንባታው÷ የካህናት ማረፊያ፣ የአብነት ት/ቤት እና የሰንበት ት/ቤት አዳራሽ እንደሚያካትት ተገልጧል፡፡
የግንባታው ጥናት፣ የምሕንድስና ሞያ ባላቸው በአንድ የቀድሞው የሰንበት ት/ቤቱ አባል እና በሌላ ምእመን ከክፍያ ነፃ በበጎ አድራጎት መሠራቱ ቢነገርም፣ በስማቸው ቃለ ጉባኤ ተሠርቶ ወጪ ለማድረግ የታቀደው ብር 250,000 የወቅቱን የሰበካ ጉባኤ አባላት እያነጋገረ ነው፡፡
በሌላ በኩል፣ የግንባታ ወጪው በዝርዝር እንዳልተሠራ እና በቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ መሠረት በሀገረ ስብከቱ እና በሊቀ ጳጳሱ መመሪያ እንዳልተሰጠበት የደብሩ ሠራተኞች ጠቁመዋል፡፡ “መነሻ እና መድረሻው በማይታወቅ የገንዘብ ወጭ እንዴት ሕንፃው ይሠራል?” ሲሉ የሚጠየቁት ሠራተኞቹ፣ ግንባታው የሚታወቅ የጸደቀ በጀት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡
የደብሩ ሒሳብ ሹም፣ የ2007 ዓ.ም የበጀት ዓመት ሊዘጋ ሰባት ቀናት ሲቀሩት ወደ ማኅደረ ስብሐት ልደታ ለማርያም ካቴድራል መዘዋወራቸውን በመቃወም፣ ከመጋቢት/2005 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 22/2007 ዓ.ም. ድረስ ለ27 ወራት ከብር 54 ሚሊዮን በላይ ገቢ እና ወጪ የሠሩባቸው የሒሳብ ሰነዶች እና መዛግብት በገለልተኛ እና ሕጋዊ ኦዲተሮች በይፋ እንዲመረመርላቸው ፓትርያርኩን ጠይቀዋል፡፡
በሒሳቡ ሹሟ ጥያቄ መሠረት ሒሳቡ ሳይመረመር እና ሳይጣራ የሌላ ሕንፃ መሠረት መጣሉ አግባብነት እንደሌለው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምእመናን ተችተዋል፡፡ አያይዘውም፣ ለደብሩ ከፍተኛ ገቢ ለሚያስገኘው ሕንፃ ዕድሳት ባለመደረጉ ይዞታው እየተጎዳ ባለበት የሌላ ሕንፃ መሠረት መጣሉ ጥያቄዎችን የሚያስነሣ ነው፤ ብለዋል፡፡
ምእመናኑ እንደሚናገሩት፣ ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ በሥራ ላይ የሚገኘው የወቅቱ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀ መንበር፣ እውነቱ መውጣቱን እንደሚሹ እና ሒሳቡ ተጣርቶ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ወደ ግንባታው መሔዱን ነው የሚመርጡት፡፡
በደብሩ ስለተፈጸመው የገንዘብ ብክነት እና ምዝበራ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እንደሚያውቁ የጠቆሙት ምእመናኑ፣ ከቃለ ዐዋዲው ድንጋጌ ውጭ ስለተፈጸሙ የአስተዳደር እና የፋይናንስ አሠራር ችግሮች በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ ሀገረ ስብከቱ ማጣራት ቢያካሒድም ውጤቱ እንዳልተገለጸላቸው አስታውሰው፣ ቅዱስነታቸው በነገው ዕለት ዕብነ መሠረቱን ከማስቀመጣቸው አስቀድሞ ስለ ግንባታው በተጨባጭ ያሉ እውነታዎችንና አግባቦችን በጥንቃቄ እንዲያጤኑት ጠይቀዋል፡፡
በአስተዳደሩ፣ ያለ ዕቅድ እና ያለጥናት የሚሠሩ ሥራዎች እና የሚፈጸሙ ክፍያዎች፣ የወጣባቸውን ከፍተኛ ገንዘብ ያኽል ጥራት እንደሌላቸው ተነግሯል፡፡ ለካህናት “ጊዜያዊ ቤት” በሚል እስከ ብር 600,000 ወጪ ቢደረግም ያለጥናት በመሠራቱ ክፍቱን መቀመጡ በአብነት ተጠቅሷል፡፡ ለደብሩ ዐይነተኛውን ገቢ ለሚያመነጨው እና በርካታ ሱቆች ላሉት ሕንፃ ጠርዝ የመሠረት ሥራ ከፍተኛ ወጪ ቢወጣም ጥራቱ ደረጃውን የጠበቀ እንዳልኾነ ተገልጧል፡፡
በአንጸሩ ጥቂት የደብሩ የአስተዳደር ሓላፊዎች፣ ውሳኔን በውሳኔ በመሻር ከሕንፃው የኪራይ ገቢ ላይ ከብር 6 ሚሊዮን በላይ ወደ ደብሩ ካዝና አለመግባቱን፤ በውል ላይ ውል በመዋዋል ከአንድ የሕንፃ ኪራይ ብቻ ብር 487,869.32 መመዝበሩን፤ የደብሩን የሕንጻ ኪራይ የአፈጻጸም ችግሮች ያጣራው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አጥኚ ኮሚቴ በሒሳብ ሹሟ አማካይነት ከመዝገብ ቤት በቀረቡለት ሰነዶች ማረጋገጡ ታውቋል፡፡
በኮሚቴው ጥናታዊ ሪፖርት እንደተዘረዘረው፣ በትክል ዘመኑ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቀደምት አብያተ ክርስቲያን አንዱ የኾነው የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን፡-
- ሰፋፊ የንግድ ተቋማት ካሏቸው አጥቢያዎች መካከል በርካታ የንግድ ማእከላትን በማቀፍም ተጠቃሽ ቢኾንም አትራፊዎቹ ግን ግለሰብ ነጋዴዎች እና ከእነርሱ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ጥቂት የአስተዳደሩ እና የሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ናቸው፡፡
- የደብሩ አስተዳደር፣ የንግድ ተቋማቱን የሚያከራየው ከሕጋዊ አሠራር ውጭ ያለጨረታ ነው፡፡ በደብሩ አካባቢ የሚከራዩ የግለሰቦች እና የደብሩ ሱቆች ኪራይ ዋጋ በእጅጉ የሚለያይ በመኾኑ ደብሩ ተጎጂ ኾኗል፡፡
- ያለጨረታ የተከራዩት የንግድ ቤቶች የውል ዘመን ሳይጠናቀቅ ውስጥ ለውስጥ ስለሚሸጡ እና በሰፊው ለሦስተኛ ወገን ስለሚተላለፉ፣ ለደብሩ ገቢ መኾን የሚገባው የስም ማዘዋወርያ ብር 50,000 ገቢ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡ ይህም ግለሰብ ነጋዴዎች እርስ በርስ እንዲጠቃቀሙ በማድረግ ደብሩን ያለአንዳች ጥቅም እያስቀረው ነው፡፡
- ግለሰብ ነጋዴዎች ከደብሩ የተከራዩትን ሱቅ ሸንሽነው ለግሰለቦች በማከራየት ተጠቃሚ ሲኾኑ አስተዳደሩ በዝምታ አልፏል፡፡ ተከራዮቹ የኪራይ ውላቸው እንዲጸና በማድረግ እና ውል በመዋዋል ሱቆቹ በጨረታ ቢከራዩ ኖሮ ደብሩ ሊያገኝ ይችል የነበረውን ከፍተኛ ጥቅም አሳጥተውታል፡፡
- አስተዳደሩ፣ በሕጉ መሠረት በካሬ ሜትር መክፈል የሚገባቸውን ክፍያ በአግባቡ የማይከፍሉትን በመከታተል እና በመቆጣጠር ማስከፈል አልቻለም፡፡ ለምሳሌ፣ የቅዱስ ዑራኤል ፋርማሲ ብር 167,552 ዕዳ እያለባቸው ተገቢው ክትትል ባለመደረጉና ተከራዮቹ ከአንዳንድ የደብሩ ሓላፊዎች ጋር በመመሳጠራቸው የተጠቀሰውን ገንዘብ ሳይከፍሉ ቤቱን ለቀው በመሔድ ደብሩን ተጎጂ አድርጎታል፡፡
- በደብሩ ከሦስት እስከ ስምንት ሱቆች በአንድ ግለሰብ ስም ተከራይተው ይገኛሉ፡፡ ይህ በተናጠል ለተለያዩ ግለሰቦች በጨረታ እንዲከራይ ቢደረግ ኖሮ ደብሩ እጅግ በጣም ተጠቃሚ መኾን ይችል ነበር፡፡ ይህ ቀርቶ ተከራዩ ግለሰብ ለሌሎች በማከራየት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ተደርገዋል፡፡