የባርነት ዘመን ( አቶ እምላሉ ፍስሃ )

የባርነት ዘመን ;—- ( አቶ እምላሉ ፍስሃ )
ሰው እንዴት በገዛ ሃገሩ እርር እንዳለ ኖሮ እርር እንዳለ ያልፋል? ጣልያን ተመልሶ አልመጣ፣ ለነገሩ የአሜሪካም ሸውራራ አካሄድ ከጣልያን ተምራ እርስ በርስ እንደጅብ የምታባላን አይደለች? 100% የምርጫ ውጤት ዲሞክራሲያዊ ነው ያሉ እለት እኮ ነው አሜሪካ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያላትን ንቀት ያስመስከረችው። እንደው የቅልውጥ እንጀራ ለክፉ ቀን ላይሆን እርስ በርስ እንድንከፋፈል እያደረጉን ገንዘብ እና አስፈላጊ ቁሳቁስ ለተወሰነ ገሩፐ እየሰጡ በለበጣ ሳቅ የ90 ሚሊዮን ህዝብ ላይ ጣሩን ሲያበዙበትአረ ስንቱን ግፍ አየን? የመንደር ጎረምሳ እየሰበሰቡ እያስታጠቁ ሲያስፈጁን ዛሬም ከቅልውጥ እንጀራ ውጭ አማራጭ እንደሌለን ሊያሳዩን የማይሰሩብን የግፍ አይነት የልም። በርቄም የዲሞክራሲ መስራቾች፣ ድንቄም የአልም መሪ፣ ድንቄም የሰላም ተባባሪዎች፣ ድንቄም የመቶ አመት ወዳጅነት፣ የገዛ ጥቅማቸውን ልማስጠበቅ ሲሉ በ90 ሚሊዮን ህዝብ ላይ የሚያላግጡ ጉዶች ሰው በገዛ ሃገሩ ተፈናቅሎ መድረሻ ሲያጣ ከንጉሰ እልፍኝ ገብተው ሻምፓኝ የሚያንሱ ነውረኞች፣ ሀዝብ እንባው ደርቆ ሰውነቱ አልቆ በሃዘን ተኮራምቶ ሲሞት እድገት እያሉ ጡሩምባ የሚነፉ ነውረኞች፣እፍረትን እንደክብር ተጎናጽፈው በገንዘባቸው ተማምነው የሚነውሩ ዘመነኞች፣ አረ ስንቱን ቀን እያዩ ከሞላልት ጋር የሚጎለምቱ ፖለቲከኞች፣ ………………

የባርነት ዘመን 2
አዲስ አበባ እንደዚህ ፍርስርሷ ሲወጣ ከጣሊያን ወረራ በኋላ የመጀመሪያዋ ነው፡፡ ጣሊያንስ በአምስት አመት የአልገዛም ትንቅንቅ ፈርጥጦ ጠፋና ሃገሬው ወደቀዬው እየተመለሰ ኑሮውን ቀጠለ፡፡ የዛሬው የሃገራችን ደፋሮች የአዲስ አበባን ነዋሪ በኑሮው ቁምስቅሉን ማሳየታቸው አነሰና በልማት ስም ከመሃል ከተማ ከመኖሪያው ቀዬ እያራቆቱ በኮንዶሚኒየም ስም ቤት ሰጠንህ ይሉናል ቤቱን ተነጥቆ 250,000 ብር እዳ ቆልለውበት በተገፋ ኑሮው ላይ ቁልቁል የድህነት ማጥ ውስጥ ይዘፍቁታል፡፡ የማያፍሩት ጉዶች ከጭቃ ቤት አውጥተን ጥራቱን የጠበቀ ቤት ሰጠንህ ብለው ሊመጻደቁም ይፈልጋሉ፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ያቺ እንደዛ የሚያናንቁአትን የጭቃ ቤት አፍርሰው ባዶ መሬቱን በሚሊዮን ብር ሻጮች እነርሱ ገዢዎችም እነርሱው ሆነው ያርፉትና (ካሳንችስ እየፈረሰ ያለውን አካባቢ ማን እንደሚሰራበት ልብ በሉ) በባለቤትነት ይኖር የነበረው የአዲስ አበባ ህዝብ ግን እንደ ዲቃላ ከከተማ ዳር እየተጣለ በገዛ ሃገሩ በእንፉቅቅ ኑሮውን ይገፋል፡፡ እውነት ይህ በመንግስት ስም አይን ያወጣ ውንብድና በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ልክ እንደደቡብ አፍሪካ ለተወሰኑ ዜጎች የተከለለ አካባቢ ላይ አለም ዘጠኝ ትሆንና ነባሩ የከተማዋ ነዋሪ ከዳር ቆሞ የበይ ተመልካች ያደርገዋል፡፡ በተለይ ዝቅተኛው የማህበረሰብ ክፍል ዝር የማይልበት የኔ ቢጤ የእግዚትነማርያምን ስም ጠርቶ የማይመጸወትበት ሰፈር ገንብተው ሲጨርሱ ልክ እንደ አፓርታይድ አይነት ስርአት ላይፈጠር የሚችልበት ምንም አይነት መተማመኛ የለንም፡፡ ምን አሁንም እኮ የሚገነቡዋቸው መኖሪያ መንደሮች በእግር ለማቋረጥ እየተከለከለ ዙሪያው ታጥሮና በቀን ጭምር ሲጠበቅ እንኳን የሰው የወፍ ደሃ ዝር እንዳይልባቸው የተከለሉ ነው የሚመስሉት፡፡ ደርግ ከስልጣን ሲወርድ እነለገሰ አስፋው እንደ ማስረጃ ከቀረበባቸው ክስ አንዱ እነርሱ ቪላ ቤት በቦሌ መሃል እየገነቡ የደሃን ልጅ ለጦርነት ይማግዳሉ የሚል ነበር፡፡ እርግጠኛ ዛሬም ሱማሌ እየሄደ የሚያልቀው ከተገቡት አዳዲስ መንደር ውስጥ እየተለቀመ ሊሆን አይችልም፡፡ የከተማው ወጣቶች ሰርቶ ማደግ እና መለወጥ የድካም ውጤት ሰይሆን የእነእከሌ አባልነት እና አጫፋሪነት መሆኑን ስላመኑ ከሰረቅህ አይቀር እንደዚህ አይነት ቤት መስራት ነው የሚል ግልጽ ምኞት ሲለዋወጡ መስማት በከተማችን ብዙ የማያስገርም መሆኑ በግልጽ ይታየል፡፡ ድንገት እንደእንጉዳይ የበቀሉትን የከተማዋን ቱጃሮች ምን እንዳላቸው ማውራት የተከለከለ ባይሆንም እንዴት እንዳመጡት እንኳን በህግ በጨዋታ መሃል መጠየቅ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ ነውር እየሆነ መጥቶአል፡፡ ሞራልና ይሉኝታ የሚያጠቃውን የሃገራችንን ማህበረሰብ የአሜሪካን ዲሞክራሲ ያተረፈለት ነገር ቢኖር መኖሪያ ቤቱን በቁሙ እየተነጠቀ ቀን የፈቀደላቸው ባለጊዜዎች ሰማይ ጠቀስ ህንጻ እየቆለሉ የዜግነት ክብሩን ብቻ ሳይሆን የስብእናውን ልክ ሲፈታተኑት ማየትን ያህል ክፉ ቀን ይኖር ይሆን? በዲያስፖራ ስም ሊሸነግሉን ሲሞክሩ የግድ እንደነለገሰ አስፋው ለእነርሱም እንደ አመጣጣቸው እሚመልሳቸው ተገኝቶ የሚያስገርመን ዘመን ይመጣባቸው ይሆን? እንዴት እና ምን በሚሉት ህግ ይሆን ሰው ከገዛ ቀዬው እየተፈናቀለ የገዛ ቤቱ ያረፈበት ቦታ በሚሊየን ሲሸጥ እርሱ በመቶ ሺዎች እዳ ተመርቆለት ከከተማ የሚባረረው? ጎበዝ እርግጠኛ ነን ጣልያን ባይመጣ እንኳ ሰው አላከብንም? መቼም ወገን በወገኑ ላይ እንዲህ የሚጨክን ልብ ይኖረዋል ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡ ድፍን ሃገር በረሃብና በጠኔ ጠፍንገው እንዳይላወስ መብቱን እንዳይጠይቅ ሲያደርጉት እውነት ግን ህግ አለ በሃገሩ? ሰውየው ትዳር ይዞ የሰርጉ እለት እንደወጉ ብርአንባር ሊሰብር ምሽቱን ሲናፍቅ አድሮ ያሰበው አልሰመረለትምና በሌለነገር መሞኘቱ ቆጭቶት ሁሌም ጀርባውን እያዞረ ይተኛል፡፡ የባሏ ነገር ያስጨነቃት ሚስት ታዲያ እናቷ ዘንድ ሄዳ ስታማክር እናትም ለምን እኛ ቤት ህግ የሚባል ነገር የለም ብለሽ ቁርጡን አትግሪውም አሏት አሉ፡፡ የኛም ሃገር ነገር ቁርጡን አልተነገረንም እንጂ ህግስ እንደሌለ ነገር አለሙ ሁሉ ያስታውቃል፡፡ እንደው እነርሱ እስኪነግሩን እንጠብቅ ካላልን ቀን ሲጥል፣ ሲጎድል እና ሲመሻሽ እንኳን ሃገር መድረሻም እንደሌለን ጠፍቶንስ አልነበረም፡፡
በዚህ ሁሉ መከራና ግፍ ተጨምቆ የሚንጠባጠብ የፎቅ ጋጋታ እየተመለከቱ የሃገራችንን እድገት ሊነግሩን የሚሽቀዳደሙ ምእራባውያንን ምን ያህል በመከራችን እና በግፋችን ላይ እየተሳለቁ እንደሆነ ያልገባው ካለ አልሰሜን ግባ በለው በሉት፡፡ በድህነት እና በባርነት ተጠፍንጎ መንቀሳቀሻ ያጣ ህዝብና ዜጋ አማራጭ ሲያጣ እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ያድራል እንጂ ገና ለገና የአሜሪካን ፍርፋሪ ይቀርብናል ብለን የሃገርን ክብር አናዋርድም፡፡ የአሜሪካኖች የውሸት ተስፋ በተለይ ለወጣቶች እየሸነገሉ የሚያማልሉትና እርቃናቸውን አውላላ ሜዳ ላይ ሲያራግፋአቸው ቅንጣት ታክል ይሉኝታ የማያውቁ ነውረኞች መሆናቸውን እኛው ለልጆቻችን ካላስተማርናቸው በራሳችን ተስፋ ያለን ዜጎች መሆን የማንችልበት ደረጃ ላይ ያደርሱናል፡፡ በዲሞክራሲ ስም እያላገጡ ለጅብ አሳልፈው ሲሰጡን ጠባሳችንን ለልጆቻችን እያሳየን እንዲመራመሩ ማድረግ ካልቻልን የባሪያ መንጋ የምታመርት ሃገር እና ለባርነት የሚሽቀዳደም ማህበረሰብ በሂደት እንዳንፈጥር ያስፈራል፡፡ የዘረኝነት እና የባርነት ልክፍት አንዴ ከተጠናወተ ምን ቢሰለጥኑ አይለቅምና እንጠንቀቅ፡፡ ከጥቅማቸው ውጭ ቅንጣት ታክል ይሎኝታ የማያውቁት አሜሪካኖች ከመቶ አመት በኋላ እናደርግላችኋለን ብለው ሲነግሩን አሜን ይደልዎ ብሎ የሚቀበል ባሪያ እንጂ ለምን እንዴት ብሎ የሚጠይቅ ማህበረሰብ እንዳለን መቀበል አይፈልጉም፡፡ የወሮበላ ስርአት ፈጥረው አስፈላጊውን እርዳታና እውቅና እየሰጡ በተላላኪነቱ ልክ እምነትና እውነታችንን ከቆዳችን ጋር ከላያችን ላይ አስገፍፈው በማጣታችን እና በውርደታችን የሚሳለቁብን በስብእናችን ልክ ሳይሆን በምርጥ አሽከርነታችን እና ወዶገብ ባርነታችን ልክ ቅኝ ገዢዎቻችንን በገዛፈቃዳችን ተቀባዮች አርገውናል፡፡ በአሽቃባጭነታችን ልክ እየተለካ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ዘጠና ሚሊየን ህዝብ ለመከራና ለጠኔ እየዳረግን ኮሮጆ ሰርቀን 100% አሸንፈናል ስንልም በለበጣ ሳቅ የሚሰፈርልን ስልጣን አዘጋጅተውልናል፡፡ ጭብጨባው ግን ስላስራብነው ህዝብ ይሁን ስለጥሩ አሽከርነታችን እራሳችንን መጠየቅ እና መመራመር አላስፈለገንም፡፡ የእሳት ልጅ አመድ እንዲሉ የአባቶቻችንን መክሊት ሰብረን ብኩርናችንን ሸጠን ወገን አስጠቅተን ሃገር እና ሽማግሌ አዋርደን የገዛ ዜጎቻችንን መድረሻ አሳጥተን በበረሃና በውሃ ሳናስበላ አንድ አመት በሰላም ከከረምን ውቃቤያችን የሚጣላን እስኪመስለን ድረስ ያጎፈላናል፡፡ አስመሳይነት እና ቀጣፊነት ብሎም ፍርደገምድልነት በሸንጎው ላይ ከኛ በላይ ላሳር እያሉን እምነት እና እውነት ከቅስማችን ጋር ተሰብረው የክፋ ቀን የምንለው ሰው አሳጥተውናል፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ ሐገርን ያህል ነገር መቅኖ መንሳት ማለት፣ እንግዳ እንኳን ሲመጣብን ከመንግስታችን አጠገብ ሆነው የስብእናቸው ግርማ ሰውሰው የሚሸት አርባ መቁጠር አቅቶን በየፌስቡኩ ላይ ኦባማ ሲመጣ እነእንትና ይገኛሉ ሌላ ማንን እንጨምር ተብለን ስንጠየቅ ዘጠና ሚሊዮን ህዝብ ያውም ሃያአራት አመት ሙሉ ሲያስተዳድር የኖረ መንግስት አርባ የሞራል ልእልናቸው በማህበረሰቡ ዘንድ የጎላ ሰዎችን መጥቀስ ተስኖት በአዋጅ አፋልጉኝ ሲለን እነማን እየመሩን እንደሆነ እርግጠኛ ሆኖ ለመናገር ብዙ አይከብድም፡፡ ህዝብን የናቀ መንግስት በእብሪቱና በመመጻደቁ ልክ ከሌባና ከጥራዝ ነጠቅ ሆዳሞች ውጭ ሰው ማውጣት አቅቶት ህሊናቸውን ሸጠው በህዝባቸው መከራ ላይ የሚመጻደቁ እፋኝቶችን ሰብስቦ መጨረሻው ሰው አፋልጉኝ እንደሚሆን የኢሃዴግ መንግስት በኦባማ የጉብኝት ወቅት አስመስክሮልናል፡፡ መጥኔ!