ግንቦት 7ና አሜሪካ — ከመጋረጃው በስተጀርባ

ኤልሳ ብስራት

ገንዘብ አምጡ ክፈሉ ባዩ ግንቦት 7 ቡድን በዋሺንግተን፤ ሲያትልና ዳላስ ያከሄደውን ዝርፊያ በሎንዶንም በመቺው እሁድ ሊያከናውን ተዘጋጅቷል። የሚሞኝ ዳያስፖራ ሞልቷልና በአስቸኳይ እንብላው ነው ዘመቻው። የጦር ስምሪቱ ወሬ ነፍሶበታልና፤ ውሸት መሆኑን የቡድኑ ደጋፊዎች ራሳቸው እየተረዱት ነውና ቶሎ ቶሎ ዝርፊያው መጧጧፉ ለብርህኑ የሞት ሽረት ጉዳይ ሆኖበታል። በለንደን ያላችሁ ወገኖች እባካችሁ አሳፍሩት ለአንዴም ለሁሌም። አደራ።

ወደ ቁም ነገሬ ስመለስ ባለፈው ሰሞን አሜሪካ ከወያኔ ጋር በይፋ ደንሳለችና፤ በዚያውም ቀበጣጥራለችና በኦባማ አማካይነት ብርሃኑ ከሄደበት እንዳይመለስ ይታገዳል ተብሎ ነበር። የኢዴኃቁ አቶ መርሻ ዮሴፍ እንዳይመለስ ታግዶ እንደነበረው ሁሉ ማለት ነው። ውስጠ አዋቂዎች ግን ብርሃኑ ከአሜሪካ ባለስልጣኖች ጋር ሳይወያይ ነቅነቅ አይልም ያሉትን አቶ ካሳ ከበደም በዳላስ ማረጋገጡ ተነግሯል። ብርሃኑ መመለስ ላይ ምንም እንቅፋት አይመጣም ካሳ ከበደ አለ ነው የተባለው። አሜሪካ ስለብርሃኑ ጉዞ ቀደም ብላ ያወቀችና አሁንም መመለሱ አይቀርምና (ይብላኝ ለጭፍን አምላኪዎቹ) በማይሆን ሁኔታ ፕሮፌሰር ያሰኘችው አሜሪካ በደስታ እንደምትቀበለው ተረጋገጠ። ባለፈው ሳምንት በዋሺንግተን ዲሲ በተደረገው የግንቦት 7 የገንዘብ ማሰባሰቢያ በዓል ላይ የሞሳድም የሲአዬም ሰላይ የሚባለው የደርጉ ካሳ ከበደ በይፋ ለህዝብ እየተነገረ 3 ሺ ዶላር ለግንቦት 7 በራሱ ስም፤ አንድ ሺ ዶላር ደግሞ ያሳደግኩት ልጄ ባለው ነአምን ዘለቀ ስም አበርክቷል። አሜሪካ ግንቦት 7ን ሽብርተኛ ብትልና ይህ ጦር የሚባለውን የኤርትራ ኮሜዲ የምትቃወም ቢሆን ኖሮ አቶ ካሳ እንኳን በይፋ በምስጢርም ሀምሳ ዶላርም አይሰጥም ነበር። ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው እንበል በዚህ ላይ!

የግንቦት 7 የወቅቱ ምልመላና ማሰባሰብ ዘዴ ወደ ጎጥና ጎሳ ማምራቱ ማመዘኑ እየታየ ነው። የስብሰባ አዳራሾችንም የታዘዙ የሻዕቢያ ጀሌዎች በቁጥር ጨማሪነት ይሞሏቸዋል። ብርሃኑ ነጋ ከአሜሪካን ባለስልጣኖች ጋር የነበረውና ያለው ግንኙነት ለተጨፈኑት እንጂ ለሌሎቹ ምስጢር አይደለም። በአዲስ አበባ አስተማሪ ሳለ ከዓለም ባንክ የተለገሰው ብዙ ገንዘብ ቀልድ አልነበረም። የበክኔል ዩኒቨእርስቲ አስተማሪ የተባለው ለሽፋን ነው ። በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ህዝብን ሸጦ ያገኘው ካሳ ከበደስ የቲንክ ታንክ ሰራተኛ ነን ብሎ እንደሚሸፋፍነው። ብርሃኑ ከወያኔ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ሲሰራ
ከጀርባው የነበሩት አሜሪካኖች ዛሬም አልተቁትም። ግንቦት 7ን የመሰረተው — ቅንጅትን ካፈረሰና ወይዘሮ ብርቱካን ሚዲቅሳን ካከሸፈ በኋላ — ቆራጥ ትግልን ለማደናቀፍ መሆኑ ለማንም ንቁ ዜጋ የሚታይ ነው። ወጣቱን አቅጣጫ ለማሳጣት፤ ቁርጠኛ የትጥቅ ትግል እንዳይካሄድ ለማደናቀፍ፤ ተቃዋሚዎችን ለማጋለጥ ወዘተ መሆኑ ተላላ ለሆኑት እንጂ ለሌሎች ከታወቀ የቆየ ነው። አሜሪካ ወዳጇን ወያኔን ትታ ለብርሃኑ ነጋ ድጋፏን ልትሰጥ ዝግጁ ትሆናለች ብሎ መገመት አይቻልም፤ ስህተት ነውና። ታዲያ ይህን የብርሃኑን ቀልድ ማካሄዱ ለምን አስፈለገ ? ትንኮሳ አካሂዶ የሻእቢያውን መሪ ወያኔ እንዲያጠቃውና እንዲያስወግደው ድልዳል መስራት ሊሆንም ይችላል። አሜሪካ ከኢሳያስ ጋር ጠጋ ጠጋ ፈለገች የሚባለው ለመጬ መፈንቅለ ኢስያስ ማዘናጊያ ሊሆንም ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ሻዕቢያ የኢትዮጵያን ትግል ጎዳሁ ብሎ በራሱ ላይ መርዘኛ እባብን ጠመጠመ ያሰኛል። የዚህን ሴራ ዕምብርትና ልክ ሳይውል ሳያድር በቅርብ ጊዜ የምናውቀው ይሆናል።

በዋሺንግተኑ የገንዘብ ዝርፊያ በዓል በSkype ይቀርባል ተብሎ የነበረው ብርሃኑ ነጋ አልቀረበም። የኢርትራ ኔትወርክ ስተማማኝ ባለመሆኑ ሊሆን ይችላል። በምትኩ አጭር ቪዲዮ ታይቷል። ብርሃኑና ነዓምን አንድ 40 የአርበኞች ግንባር ወታደሮችን ሲያነጋግሩ። ቀይ ሽብርተኛው ተመስገንም ነበር። ቀልድ አይታክቴው ብርሃኑ ይህ ትልቅ ሰራዊት ይበልጥ ገዝፎ እንዳያብጥብን መከላከል ያስፈልጋል ብሎ ሲያሾፍ ይደመጣል። ከጓድ ብርሃኑ ጋር ወደፊት የሚልም ጀሌ ተዘጋጅቶ ነበርና ሲጮህም ተደምጧል። ነዓምን በበኩሉ በዲፕሎማሲያዊ መስክ ከውጭ እንረዳችኋለን ብሎ ቢያንስ ለቤተሰቡ መመለሴ አይቀርምን አስተላልፏል። ሁለቱም በረሀ አለመድረሳቸውን መሬት ሊነካ ጉዞ የጀመረው ቦርጫቸው ይመሰክራል። ስለ ህብረት ጠይቅ ተብሎ የታዘዘው ሌላ ጀሌም ይህንኑ ጥያቄ ያነሳና ብርሃኑ በሁለት ሳምንት ውስጥ ውጤት ትሰማላችሁ ብሎ መልሶለታል። ብርሃኑ ከዚህ በፊት የሞከራቸው የህብረት ጥረቶች ሁሉ ከወያኔ እስከ ጄኔራል ከማል ገልቹና ኦነግ ሁሉም ወድቀበታል። ብርሃኑ አሁንም ህብረት ይኖራል ሲል ከኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ሳይሆን ከገንታዮችና በሻዕቢያ ስር ከተኮለኮሉት የድርጅት ፌዞች ጋር ነው። እነማን ጋር ነው ብርሃኑ በመጪው ሳምንት ህብረት አደረግኩ ብሎ ዲያስፖራውን አዋጣ ደግፍ የሚለው?

1. ከፖለቲካው መድረክ ተኖ ጠፍቶ የነበረውን የሻዕቢያ ታዛዥ የበኒ ሻንጉልን እንቅስቃሴ እንደገና ነፍስ ዘርተው ለህብረቱ አባልነት ሊያቀርቡ እየጣሩ ናችው
2. አንድ ወይ ሁለት አባላት ያሉት የሲዳማ አርነት እንቅስቃሴ
3. ሻዕቢያ ካዘዘና ከፈቀደ የትግራይ የሚባለው የኢሳያስ የግል ጦር ዴምህት
4. ሻዕቢያ ከፈቀደ ከኦነግ አንጃዎች አንዱ በጄኔራል የሚመራ ኢምንት ቡድን
5. ጭንቅ ይዞት ርጉዝ ሊያገባ ከተስማማ አንድ የአፋር ቡድን

የሁሉም አንድ መለያ የሻዕቢያ ፍጡራን ወይም ታዛዥ መሆናቸው ነው። በርካታዎቹ የግንጠላም አቀንቃኝ ናቸው። ሲአን የሲዳማ ህዝብ ቅኝ ተገዢ ሆኗል ሲለን እንደነበር አልረሳንም። ሁሉም የኦነግ አንጃዎች ደግሞ ነጻ ኦሮሚያ ከሚለው ቅዠታቸው ገና አልተላቀቁም። ሁሉም ተባበሩ ቢባል የዝምብ ክምችት ከመሆን የሚያልፉ አይደሉም — መሶብ አይከፍቱም። ወያኔን አያሰጉትም። ዲያስፖራውን ለመዝረፍና ቆምጫጫ ትግልን ለማደናቀፍ ግን ለብርሃኑ ያመቻሉ። አሜሪካም ወያኔም ደስ ይላቸዋል። ሌላ ውጤት የለውም። ብርሃኑ የህዝብን ትግል አደናቅፎና ቅንጅትን አፍርሶ የመጣ ነውና ለሀቀኛ የኢትዮጵያውያን ህብረት ዕጩም ፈላጊም አይደለም። ረዳቱ ተመስገን ለጄቦም የቀይ ሽብሩ ወንጀለኛ ለሻዕቢያ ተገዢ ሆኖ ተጋልጧል። ነዓምንም ከመድህን እስከ ህብረትና ግንቦት 7 ያደረገው ጉዞና ሻዕቢያን ደጋፊ መሆኑም ሀገራዊ አቅዋም ጋር መለያያቱን የሚያረጋግጥ ነው። አሜሪካ የሕዝብን ጸረ-ወያኔ ትግል ለማደናቀፍ ስታደርገው የቆየው ጥረት አካል ሆኖ ግንቦት 7 የሚንቀሳቀሰው። የኢሳቱ መሳይ ለምሳሌ በሺ ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ትግልን ሊመራ ጫካ የገባ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነው ብሎ በራዲዮ ተደምጧል። ይህ ለኢሳያስ ሲሽቆጠቆጥ የታየና ያሳፈረን “ቦጤ” የዛሬ ሺ ዓመት ፕሮፌሰር የሚባል ጉድ አለመኖሩን የሚያውቅ አይመስልም። የግርግር የሽፋን ፕሮፌሰርነት ማንንም አያደናግርም። ብርሃኑ ለመሆኑ ረዳት ፕሮፌሰር ሆኖ ስንት ዓመት ቆይቷል? በትምህርቱ መስክ ስንት መጽሃፍት አበርክቷል? ስንት ሰዓታት አስተምሯል — በአውሮጳ መንሸራሸሩ ከእዚህ ካልተቆጠረ? በራሱ በሻዕቢያም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ድርጅቶች ስንት የላቁ ምሁሮች ታግለው መሰዋታቸው ለዚህ ጋዜጠኝነትን አሰዳቢ የማይታወቅ ሆኖበታል። ዋናው ቁም ነገር ግን የግንቦት 7 ፕሮፌሰር ኤርትራ ሄደ እንጂ ትግል ሜዳ ጭራሽም ዝር አለማለቱ ነው — ሀሬና፤ ጉልች፤ ተሰነይ አስመራ የትግል ሜዳ ካልተባሉ በስተቀር።

ኦገስት 23 ብርሃኑ በSkype ከተገኘ ለንደን ነዋሪውን ሊዘርፍ ደፋ ቀና ማለቱ የሚጠበቅ ነው። በዚህ ዘመቻው አዛውንቱ እምሩ ዘለቀና የሲአይኤ (የስታንፎርድ) ምሩቆችና አላርፍ ያሉ ደርጎች ቢያጅቡት የሚገርም አልሆነም። እበላ ባይ ብዙ ነው። የብርሃኑ ፖለቲካ ደግሞ ገንዘብ በመሆኑ ጠጋ ጠጋው ትርፍራፊ ያስገኛል። የፋሺስቱ መንግስቱ የብዕር ቅጥረኞች በሽፋን ስም የብርሃኑ ነጋ የብዕር ማጅራት መቺዎች ቢሆኑ የሚያስገርም አይሆንም። አሜሪካ ወያኔን እየጠቀመች ያለችበት አንዱ መንገድ ብርሃኑ ነጋን በማሰማራት ነው። ፎቶው ተሸጠ የሚባልለት ታጋች አንዳርጋቸው ደግሞ ብርሃኑንን ከነአዛዞቹ ሻዕቢያ የሚያወግዝ መጽሃፉን ጨርሶ ለገበያ ሊያቀርብ ደርሷል። ጉድ ሊፈላ ነው! ተገዶ ጻፈ አያዋጣምና ከአሁኑ መከላከያ ለማዘጋጀት ቢጥሩ ይጠቅማቸዋል። ስየል ለመቀበል፤ ለመሰዋት ያልተዘጋጀ ድንቄም የትግል መሪ!

ዛሬ በብርሃኑ የተደናገሩና ሳይወዱ መሳሪያው የሆኑት ሁሉ ነገ ትግል ሜዳ ያለውን ያውም ኤርትራን ጥሎ ሲመለስና ተሰማራ የተባለውም ጦር (ለመሆኑ አዘዞ ደርሶ ተነነ እንዴ?) ጭራሽ ያልነበረ መሆኑን ሲያውቁ ይብላኝ ያኔ ለብርሃኑ ነጋ። ለማንኛውም ይህ የመጨረሻው የማወናበድና የክህደት ሙከራው ይሆናል። በለንደንና ሌሎች ከተማዎች ነዋሪ የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን በብርሃኑ ነጋና ሻዕቢያ ላይ ማዕቀብ አድርጉ! አትታለሉ፤ አትዘረፉ! በጎጥ መሰባሰብን አውግዙ! ሻዕቢያን አቅፎ ወያኔን ማጥቃት ዘበት ነው! ወያኔ በውሸት ጦር አይሸነፍም!