የኢትዮጵያ የስደት መንግስት፤ ከህሳቤ ወደ ተግባራዊነት

entc and eynm logo
የኢትዮጵያ የስደት መንግስት መመስረት አስፈላጊነት ላለፉት ሁለት አስርት አመታት፣ በተለይ ደግሞ የግንቦት 1997 ዓ.ም. ሃገራዊ ምርጫን የህወሃት/ኢህአዴግ ስርዓት በጠመንጃ አፈሙዝ ከህዝብ መንጠቁን ተከትሎ ውይይትና ክርክር ሲደረግበት ቆይቷል። የተሰረቀውን የህዝብ ድምፅ ለማስመለስ የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የተለያየ የትግል ስልት መከተልን መርጠዋል። አንዳንዶች የትጥቅ ትግል ሲመርጡ፣ ሌሎች የምርጫ ፖለቲካን ገፍተውበታል። የአፖርታይዱ ወያኔን አምባገነን ስርዓት አስወግዶ ሁሉም አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም እስካሁን ያልተሞከረ መንገድ ቢኖር የፓርቲ ፖለቲካን ወደ ጎን በመተው ባለድርሻ አካላትን ሁሉ ያሳተፈ የስደት መንግስት መመስረቱ ነው።

ይህን ሃሳብ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር ሐምሌ 2012 እ.አ.አ. አያሌ ኢትዮጵያውያን በዳላስ ቴክሳስ በመሰባሰብ የኢትዮጵያ የሽግግር ምክር ቤት መስርተዋል። የሽግግር ምክር ቤቱም ላለፉት 3 ዓመታት ሃሳቡን ለማስረፅና ስምምነት ለመድረስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በርካታ ስብሰባዎችና የምክክር ጉባዔዎች አካሂዷል።

ባሳለፍነው ወር ሐምሌ 2015 የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤቱና የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ ከተለያዩ የድርጅቶች ተወካዮችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋር ለሁለት ቀናት በዋሽንግተን ዲሲ ውይይት ካደረጉ በኋላ የኢትዮጵያ የስደት መንግስት አደራጅ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማምተዋል።

በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ የስደት መንግስት አደራጅ ኮሚቴ በመመስረት ላይ ይገኛል። የመጀመሪያ መዋቅሩ ተዘጋጅቷል። የኮሚቴው ተቀዳሚ ስራ የሚሆነው፤ 1) የኢትዮጵያ የስደት መንግስት መመስረት አስፈላጊነትን ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ 2) አስፈላጊ የሆኑ ህዝባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና የፋይናንስ ድጋፎችን ማሰባሰብ፣ 3) የስደት መንግስቱን መሰረት መገንባት።

የስደት መንግስት ምስረታው ብዙ ደረጃዎች ይኖሩታል። የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት በጣም በጥንቃቄ ታቅዶ ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ ኮሚቴው ይረዳል። በተጨማሪም ዘርፈ-ብዙ ስራዎችም እንዳሉት ይገነዘባል። በሚቀጥሉት ቀናትና ሣምንታት አደራጅ ኮሚቴው የነደፋቸውን እቅዶች ለህዝብ ይፋ በማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል።

የኢትዮጵያ የስደት መንግስት የመጨረሻ ግብ የሚሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ፣ ሰላማዊና ወደትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር መኖሩን ማረጋገጥ ነው። ከዚህ በፊት ያልታቀደ የስርዓት ለውጥ የሚያስከትለውን ቀውስ አይተናል። ለዚህ ደግሞ ሃገራችንን መመልከት በቂ ነው። በአሁን ወቅት በሶሪያና ሊቢያ እየሆነ ያለውን መመልከትም እንችላለን። ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጠነም ዘገየም ለውጥ መምጣቱ የማይቀር ነው — ምክንያቱም አምባገነን ስርዓትን ለመታገል ህዝብ በየትኛውም ሀገር ቢሆን ማመጹ ስለማይቀር። በተቻለ መጠን ሌላ ቀይ ሽብር፣ ሌላ አፖርታይድ ስርዓት፣ ሌላ የህዝብ እልቂት በሀገራችን እንዳይከሰት የሚመጣው ለውጥ በሰላማዊ ሂደት እንዲያልቅ እንፈልጋለን።

የታቀደ፣ የተደራጀና ሠላማዊ ለውጥ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመሰረት በሚደረገው ጥረት ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንድትሳተፉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን!

የኢትዮጵያ የሽግግር ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ
ቀን 20/09/2015

ለግንኙነት፤
[email protected] or [email protected]