የመንግስት ሰራተኞች የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ እንዳላስደሰታቸው እየገለፁ ነው
በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚያገለግሉ የመንግስት ሰራተኞች ትላንት ይፋ የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ እንዳላስደሰታቸው አስታወቁ፡፡ ሰራተኞቹ የደሞዝ ጭማሪው ከፍተኛ መጠን ያለው (ከ100-117%) እንደሚሆን በከተማው በሰፊው ሲናፈስ የከረመ በመሆኑ በጉጉት ሲጠብቁት እንደነበር አስረድተው ተደረገ የተባለው ጭማሪ ግን ከተጠበቀው በታች በመሆኑ የስራ ሞራላቸውን እንደጎዳው በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ ሰራተኞቹ ይህን የገለጹት የሲቪል ሰርቪስ ሚንስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ ትላንት ከሰአት በኋላ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ ነው፡፡
ከመግለጫው መረዳት እንደተቻለው የደሞዝ ጭማሪው ከ35-39 በመቶ የሚደርስ ሲሆን ከጥር 1 2003 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡ በዚሁ መሰረት አነስተኛ ደሞዝ ያገኙ ለነበሩ ሰራተኞች 39 በመቶ ጭማሪ ሲደረግ፤ ከፍተኛ የመንግስት ደሞዝተኛ የሆኑ የህዝብ ተመራጮችና የመንግስት ተሹዋሚዎች ደግሞ 35 በመቶ ጭማሪ ያገኛሉ፡፡
አቶ ጁነዲን ይህ እርምጃ የመንግስት ሰራተኞች የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም እንደሚያስችላቸው የገለጹ ቢሆንም በተለይ ዝቅተኛ ተከፋይ የሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ አዲስ አበባ በሚገኝ የመንግስት ት/ቤት ውስጥ በጥበቃ ስራ ላይ የተሰማሩ አንድ ግለሰብ ለኢትዮጵያን ሪቪው ሪፖርተር እንዳስረዱት ሲከፈላቸው በነበረው 320 ብር ደሞዝ ላይ የ100 ብር ጭማሪ እንዳገኙ ገልጸው ይህ ጭማሪ በከፍተኛ ፍጥነት እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም ያስችላል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ አክለውም ከጭማሪው ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለው የዋጋ ንረት እንዳሰጋቸው ተናግረዋል፡፡
መንግስት ከጭማሪው ጋር ተያይዞ በቤት ክራይና በፍጆታ እቃዎች ላይ ጭማሪ የሚያደርጉ ዜጎች ላይ እርምጃ ወስዳለሁ ማለቱ ይታወቃል