የእናት አንጀት …. ዘመድኩን በቀለ

'እናቴ እግዚአብሔር ያጽናዎት ። ነፍስ ይማር ።'Zemedkun Bekele's photo.
 

የእናት አንጀት ….

ዛሬ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ያገኘሁት የእኚህ እናት ምስል ክፉኛ አስተክዞኛል ። እኝህ እናት ቢያንስ አዘቅዝቀው ያደረጉት ነጠላ እዚሁ ኢትዮጵያችን ውስጥ መሆናቸውን ይናገራል ። ለቀብር እየሄዱ መሆናቸውንም የያዙት አስከሬን ይናገራል ። ቦታው የት እንደሆነ ግን ፎቶውን ያነሳው ግለሰብም አልተናገረም ። አልገለጸልንም ።

እኚህ እናት ለቀብርስ እሺ ይሂዱ ። አስከሬኑን ያጠቡት ፣ ደግሞም የገነዙትስ እሳቸው ይሆኑ ? እሺ አስከሬን የሚሸከምላቸው ሰው እንዴት ጠፋ ? መቃብሩንስ ማን ቆፈረላቸው? ከቀበሩስ በኋላ በዚህ በያዙት ህፃን አስከሬን ላይ አፈሩን የሚመልሰው ማነው ? መቼም ይህ አስከሬን ከማህጸናቸው የወጣ ፍሬ ከሆነ በጣም ያሳዝናል ። እጅግ በጣም ያሳዝናል ። ተደራራቢና መቼም ከህሊና የማይጠፋ ሐዘን ነው።

እድር የሌለውን ሰው ፣ በአካል አይቶት የማያውቀውን እንግዳ እያለቀሰ ደረቱንም እየደቃ የሚቀብር ማኅበረሰብ ባለበት ሀገር ይህ እንዴት ሊከሰት ቻለ?

ከ90 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባላት ሀገር ላይ ምንድነው እንዲህ ያጨካከነን ። ይህን ምስል ያነሳው ሰው ፎቶ ከማንሳት ብትቀበላቸወ ምን አለበት? ብቻ ፎቶው ብዙ ነገር ይናገራል ።

ሰው የለም እንዳንል እግሩ ብቻ የሚታይ ትልቅ ሰው ፣ ከሩቅ የሚያዩ ሰዎች ፣ ቆሞ ፎቶ የሚያነሳ ሰው ይታያል ። የገጠር ከተማ በመሆኑም ብዙ ቤቶችም ይታያሉ ። እና የምን ጉድ ነው የምንስ መዓት መጣብን ? እንዴት ነው እስከዚህስ ድረስ እንዲህ ያጨካከነን ምን ይሆን ።

በእኔ በኩል በእኚህ እናት ላይ የደረሰ ሐዘን በማንም ላይ አይድረስ ። የፍቅር አምላክ ይታረቀን ።

ፎቶው ለምንም ይሁን በማን ዛሬ በፌስ ቡክ ላይ ተለጥፏል ። አነጋጋሪነቱም እንዲሁ ይቀጥላል ።

ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ነሐሴ 5/12/2007 ዓም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ