ጋዜጠኛ ደምስ እና ተያያዥ ጉዳዮች
ይህ ጽሁፍ ቀደም ሲል ጋዜጠኛ ደምስ በለጠ ሄኖክ ሰማ እግዚሀር (የቪኦኤ ጋዜጠኛ) መብቱ ነዉ በሚለዉ መጣጥፉና በኤርትራ በኩል ኢትዮጵያን ነጻ ማዉጣት ሊታሰብ የማይቻል ነዉ ተብሎ የሚቀረበዉ ሀሳብ በማይመቻቸዉ ወገኖች ላይ ከሞላ ጎደል የተነጣጠረ ድርሳን ነዉ።
ጋዜጠኛ ደምስ አከታትሎ በኤርትራ በኩል የሚደረገዉ የነጻነት ጉዞ አልጣመኝም በማለት ቀደም ሲል ከጻፈዉ ጽሁፍ በተጨማሪ ሁለተኛዉ መጣጥፉን ይዞ ብቅ አለ ሶስተኛዉንም ደገመ ቃለ መጠይቅም ለቀቀ። ይህ ደግሞ ሊቃረኑት የሚከበድ ትንታኔና የፎቶግራፍ ማስረጃ በማስደገፉ ለተቺዎቹ የሚመች ሁኖ አልተገኘም። ጋዜጠኛ ደምስ እንደሚለዉ ከአርበኛዉ ጋር ኮሾሮ በልቼ ቂጣ አብስዬ የሆድ የሆዴን ተነጋግሬ ማስታወሻ ይዤ ተመልሻለሁ በተደጋጋሚ ወደ ኤርትራ ባቀናም በዛ የሚሰራዉ ስራ ጤናማ አለመሆኑ ስለገባኝ የማስጠንቀቂያ ፊሺካ አሰማለሁ በማለት ወደ ወገን እንደገና ተመልሻለሁ ብሏል። ይህ እንቅስቃሴ የግንቦት 7 ደጋፊዎችን ቢያስቆጣም ጋዜጠኛ ደምስ ደግሞ በምድረ አሜሪካ እስከኖርኩ ድረስ ህገመንግስታዊና ሰብአዊ መብቴ ስለሆነ በተሰጠኝ መብት መሰረት መብቴአነ ተግባራዊ አደርገዋለሁ በማለት በአጽንኦት ድርጊቱን ቀጠለ ።
በተመሳሳይ ሁኔታ ቀደም ባለዉ ጊዜ አቶ አበራ ለማ ሲፈርድበት አቶ አንዳርጋቸዉ በታሰረበት ማግስት ቀኑን በትክክል ሳያሰላ ቀርቶ ስለበአሉ ግርማ በማዉጣቱ የእሩምታ ተኩስ ከየአካባቢዉ ተተኩሶ ጥጉን እንዲይዝ ተደረገ።ወደ አዉሮፓ ግድም የምትኖር አንድ እህትና የሷን ሀሳብ የሚጋሩ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይነት ባለዉ ጽሁፍ አቶ አበራን አወገዙ አቶ አበራም ባልተመጣጠነ ቅጣት በገዛ ወገኖቹ ወደቀ። ተቃራኒዎቹ በሱ ብቻ ሳይወሰኑም ወደ ቤተሰቡም ተሸጋግረዉ ስለ ልጆቹ አላስፈላጊ ትችት ሰጡ። እንደዉም አንድ የግንቦት 7 አቀንቃኝ በድፍረት ስለ አቶ አንዳርጋቸዉ በቅጡ እንዳናዝን ሆን ተብሎ የተሰራ የወያኔ ሴራ ነዉ ብላ በድፍረት ጽሁፏን አወጣች። የሚገርመዉ አቶ አበራ የከሰሳቸዉ ሰዎች በህይወት እያሉ መልስ ለመስጠት ከብቃት በላይ ችሎታ እያላቸዉ የእንቅቡ መንጣጣቱ የሚገርም ነበር።
ይህች እህትና የእሷን ሀሳብ የሚጋሩ ወገኖች ያልተረዱት ነገር ቢኖር ለአቶ አንዳርጋቸዉ የድርጅቱ ሰዎችና በሱ በኩል መሽሎኪያ አናጣም ብለዉ የሚባዝኑ የሻቢያና የዘር አምላኪዎች የሚያብዱለትን ያህል ለሀገሩ ቋሚ ሀዉልት ሰርቶ እንደወጣ የቀረዉ የብእር ሰዉ፤የፖለቲካ ተንታኝ፤ምሁር፤ጋዜጠኛ፤ዲፕሎማት በአሉ ግርማ ነገር ሲያንገበግባቸዉ የሚኖሩ ዜጎች ቀላል እንዳልሆኑ እሷና መሰሎቿ ሊረዱት በተገባቸዉ ነበር። ከመጣዉ ባለጊዜ ጋር ብቻ ከመደነስ ባለፈዉ ለሀገራቸዉ ዉለታ የዋሉትን ማስታወስ ሀገር በቀጣይነት እንዲኖር ከማድረጉም በላይ ዜጎችም ለሀገር ለመዋል የተቻላቸዉን ጥረት ያደርጉ ነበር።
አንድ ታጋይ ወደ ትግል ሲገባ ከዚህ የከፉ ጉዳዮች እንደሚገጥሙት ጠንቅቆ ያዉቃል። አቶ አንዳርጋቸዉም ከድርጅት አባሎቻቸዉ ጋር የቀጥተኛ መስመር ተቋርጦባቸዉ ነዉ እንጂ ስለእኔ አታስቡ ስራችሁን ቀጥሉ ወያኔን፤ ሻቢያን የዘር ድርጅትን አትመኑ (የእኔ ህልም ነዉ ይሄኛዉ) ብለዉ ትእዛዝ የሚሰጡ ይመስለኛል ምንም እንኳን በህወአት ቴሌቨዠን ቀርበዉ የተናገሩት ሌላ ቢሆንም ።
እነዚህ በኢትዮጵያዉያን ተከልለዉ የሚያሳክሩ ጸረ አንድነት ሀይሎች ጠንከር ያለ ኢትዮጵያዊነት ሃሳብ ሊያመጣ ይችላል በሚሉት ዜጋና ጽሁፍ ላይ፤ በፓልቶክ አልፎ አልፎም በኢሳት አማካይነት ሰብአዊነት ባልተላበሰ አነጋገር ግለሰቡን በማሸማቀቅ፤በማዋከብ ከፖለቲካ ጨዋታ ዉጭ ያደርጉታል። ይህንንም ልምድ ከቅንጅት ማግስት አንስቶ ሲጠቀሙበት ተስተዉሏል ጋዜጠኛ ደምስም ጉዳዩን በስሱ ሂዶበታል። በተለይ በዚህ በተቀነባበረ የጥቃት ሰለባ ግምባር ቀደም ከሆኑት ወገኖች መሀል ዶር ታየ ወ/ሰማያት ፤ኢንጂነር ሀይሉ ሻዉል፤ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሀይሌ በተወሰነ መልኩ ኮለኔል ጎሹ እና ሌሎችም ምርጥ ኢትዮጵያዉያን ይገኙበታል። ኢንጂነር ሀይሉ ይህ ገደቡን የጣሰ ስድብ ተመጣጣኝ እንዲሆን በአንድ ቃለ መጠይቅ ከረንት አፌየርስ ለተባለዉ ለፓልቶክ ክፍል ተማጽኖዋቸዉን አቅርበዉ እንደነበር ሁላችንም የምንስታዉሰዉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር።
ቀደም ሲል በታላቅ ኩራት የቀድሞ የፓርላማ ተመራጭ ነኝ ብሎ እራሱን ያስተዋወቀን ክቡር ኑረዲን ነዉ መሰለኝ ስሙ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ በጻፉት የምርምር ጽሁፍ አስተያየት መስጠት ፈልጎ ማጣሪያዉ ቢያጥረዉ የደብተራ ትምህርት ብሎት አጣጥሎት አልፏል። እንግዲህ ይህ ብዙ ያወቀ የመሰለዉ የቀድሞ የፓርላማ ተመራጭ ነኝ ባይ ህወአትና ሻቢያ በተካካዱበት ዉል ምክንያት በተነሳ ጦርነት 70000 የወገን ጦር እንደ ቅጠል ከረገፈ በሗላ ያስመለሱትን መሬት እንኳን ማስከበር ያልቻለ ፤አሰብና ኤርትራ ያለምንም ተቃዋሚ ከእናት አገራቸዉ ተገንጥለዉ ሲሄዱ ተቃዉሞ ያላሰማ ፤ኢትዮጵያ በዘር ተከፋፍላ ብትንትኗ ሲወጣ ደስታዉን በጭብጨባ የገለጸ ካድሬ ዛሬ ከአለም ምሁራን ጎን ተርታ የሚቀመጡትን ምሁር የደብተራ ትምህርት ብሎ ሲያጣጥል ምን ይባላል? ስንት የሚጠቅም ጽሁፍ እየተጣለ እንዲህ አይነት ዝባዝንኬስ ለአንባቢ ማቅረብ ጥቅሙ ምንድነዉ?። መቼም ስለ ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሀይሌ ትልቅነት መናገር ጊዜ ማጥፋት ስለሆነ ማለፉ ይመረጣል። ፕሮፌሰር ጌታቸዉ ሐይሌ ምሁር ብቻ ሳይሆኑ የምሁር ደረጃ መዳቢም ናቸዉ ጀግናም ናቸዉ። ክቡር የህወአት የፓርላማ ተመራጭ ግን ይህንን ሳይመዝን በሚቀጥለዉ ጽሁፉ ደግሞ ነገሩ ሁሉ የተሳከረ የኒዎ ሊበራሊዝም ትንተና ይዞልን ቀረበ መቼም ተዉ አይባል መሀይመነቱ ገዝፎ ጠልፎ እስኪጥለዉ መመልከት ነዉ እንጂ። መለስ ዜናዊስ ፍሬ ከርስኪ 700 ገጽ ያህል ድርሳን ደጉሶ አልነበር ከሱ ጋር አብሮ በነነ እንጂ።
ይህን በዚህ ሁኔታ ካቀረብኩ በሗላ በአንባቢዎቼ እንደ መንደርደሪያ ታይቶልኝ ጋዜጠኛ ደምስ ሔኖክን አስመልክቶ ወደጻፈዉ ስመለስ። ጋዜጠኛ ደምስ ሔኖክ በአቋሙ እንደተጎሳቆለ አድርጎ አቅርቦ ከዛም ገፋ ብሎ ሄኖክ መብቱ ነዉ የሚል አስተያየትም አክሎበታል። እዚህ ላይ ሄኖክ እንደማንኛዉም ነጻ ዜጋ የራሱ የግሉ የሆነ አመለካከት ይኖረዋል ወያኔነቱንም ከመረጠ የሚነካበት የለም ፡ያለበት አገርም ይህንን ሰብአዊ መብቱን ያከብርለታል በዚያ የሚኖሩት ዜጎቹም ይህን መብቱን የማክበር ግዴታቸዉ ነዉ። ጋዜጠኛ ደምስ እራሱ እንደተናገረዉ ወያኔ ዘመም የፖለቲካ እምነቱን ለመጋፋትም ይከብዳል ምናልባትም የተሰራበትም ሊሆን ይችላልና።
ይህ እንዳለ ሁኖ የሄኖክ የግል እምነቱ የግል የማይሆንበት ጊዜም እንዳለ ማሳየት አግባብ ነዉ። ሄኖክ በጣም ጉልበታም በሆነዉ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ተቀጣሪ ሰራተኛ ነዉ። ከዛ የሚያስተላልፈዉ ማንኛዉም መልእክት ሁሉ አንድ ፕሮፌሺናል ጋዜጠኛ የሚያስተላልፈዉን እንጂ የግል እምነቱን ያንጸባረቀ መረጃና ትንታኔ ሊሆን አይገባም። “እናንተ የአለም አይን ናችሁ አለም እዉነታዉን በእናንተ አይን ያያል” ተብሎ ለጋዜጠኞች መመሪያ ቢሰጥም አለም ግን በሄኖክና በአዳነች ፍስሀዬ አይን ያየዉ እዉነታዉን ነባራዊዉን ሳይሆን የነሱን ወያኔያዊ እዉነታ ነዉ። ይህን አስመልክቶ ቀደም ባለዉ ጊዜ ለቪኦኤ ስለነዚህ ሰዎች መላ እንዲፈለግ በስልክ እና በድር ጥንጥን መስመሩን ኢትዮጵያዉያን ቢያጨናንቁትም የሄኖክ ቀጣሪዎች የህዋት ቀጣሪዎች በመሆናቸዉ የህዝቡን ጩኸት ዋጋ ሳይሰጡት ቀርተዋል ሄኖክም ወያኔነቱን ቀጥሎበታል።
የተቆጣ ህዝብ ብዙ ያደርጋል የደፈረ ክራቫት ይስባል፤ ራቅ ካለበትም ጫማ ይወረዉራል፤ ከጠነከረ ደግሞ በነጎድጓድ ድምጹ መብረቅ ጥሎ ይገላግላል። ይህ ሁሉ ሲሆን ያየነዉ ቢሆንም ሄኖክ ላይ ግን ይህ ሁሉ አልተሞከረም። ሄኖክ የሚያየዉን ከወገናዊነት በጸዳ መልኩ እንደ ካሜራዉና ድምጸ መቅረጫዉ ሊያቀርብ ሲገባ እያሸና እያስተካከለ ለህወአት እንዲመች አድርጎ ካቀረበ የጋዜጠኝነት ሺፋን ሊሰጠዉ አይገባም (persona non grata)። በዚህም የተነሳ ድምጹ የታፈነ ህዝብ ሄኖክን ቢቆጣዉ ገሰጸዉ እንጂ አልተበቀለዉም ባይ ነኝ። የጋዜጠኛ ደምስ ሀሳብ ሁሉም ተስማምቶኝ እዚህ ላይ ተለይቻለሁ።
እዚህ ላይ ዉድ አንባቢዎቼ ከዚሁ ከቪኦኤ(VOA) ቤት ሳልወጣ በመለስ ዜናዊ ህወአት ትእዛዝ 280 ህጻናት በጠራራ ጸሀይ ሰላማዊ ሰለፍ ወጣችሁ ተብለዉ ሲታጨዱ አድሃነች ፍስሀዬ የተባለቸዉ የዚሁ የቪኦኤ ተቀጣሪ ምንም ሳይሰቀጥጣት የስርአቱን ደጋፊ እና ተቃዋሚ በወቅቱ ስታወያይ “እነሱም (ሰላማዊ ሰልፈኞቹን ማለት ነዉ) ድንጋይ ይወረዉሩ ነበር” ያለችዉ ቪኦኤ አርካይቭ ዉስጥ ይገኛል:: የህች ሴት በቦታዉ ተገኝታ የሳሞራን ቦታ ብትይዝ ልታደርስ የምትችለዉን ጥፋት አንባቢ በአይነ ህሊናዉ ይቃኘዉ ከማለት በስተቀር ምን ማለት ይቻላል?። ጋዜጠኛ ደምስ ይህችን ሴት መብቷ ነዉ እንደማይለኝ እርግጠኛ ነኝ።
እንግዲህ የቪኦኤ ወያኔዎች ነገር ይህን ይመስላል በታንክ የታጀበ በራይት ጊር(riot gear) የታጠቀ የህወአት መንጋ ድንጋይ ለወረወሩት ህጻናት (መወርወራቸዉም እዉነት ከሆነ) የሞት ቅጣት ይፈርዱባቸዋል አሜሪካ አገር ቁጭ ብለዉ ፕሬዚዳንቱን ተኩሶ ያቆሰለ በማይገደልበት አገር። አድሀነች ፍስሀዬ ይህን ስትናገር ቀጥታ(live) ስለሆነ ተጠንቅቃ ነዉ በቤተሰብ ስብሰባ ግን ምን ልትል እንደምትችል መገመት አስቸጋሪ አይሆንም። በግሏና መሰሎቿን ሰብስባ በዛን ቀን ወያኔ ባደረገዉ ገድል ሻምፓኝ አትከፍትም ይባላል? እንግዲህ ይህን ነገር አንባቢ ይፍረደን። ይህ የእመቤት አድሀነች ፍስሀዬ የጭካኔ ስራ ግር ያለባቸዉ ዜጎች ጊዜዉም ስለራቀ ነገሩም ከአእምሮዋቸዉ ስለደበዘዘ ወደ ቪኦኤ አርካይቭ ጎራ ብለዉ በዚያን ጊዜ የተደረገዉን ቃለ መጠይቅ ጎግሎ መስማት ጠቃሚ ይሆናል እላለሁ። ነገሩን ነገር አነሳዉ እንጂ ትዝታ በላቸዉም በዚህ በተከበረዉ ወንበር ተቀምጣ ተዉ አትቆንጥጠኝ ስትል ተደምጣ ነበር። እንደነዚህ አይነት ሰዎች ሲበዙ መሰለኝ እነ ሰለሞን ክፍሌም ገለል ማለት የጀመሩት።
የፕሮፌሺናሊዝም ኤቲክ( professional ethics) ሄኖክንም ሆነ አድሀነች በደምብ ሊረዱትና በመርህ ደረጃ ሊከተሉት ይገባል። ፕሬዚዳንት ሬጋን በጥይት ተመትተዉ ወደ ሆስፒታል በሄዱበት ጊዜ ቀዶ ጥገና ሊደረግላቸዉ በዝግጂት ላይ እንዳሉ ዞር ብለዉ ለመሆኑ ሪፐብሊካን ናችሁ ብለዉ ሀኪሞቹን ቢጠይቁ የቡድኑ መሪ ፈጠን ብሎ ለዛሬ ሪፐብሊካን እንሆናለን ብሎ መልሶ ነበር። ጠላታችንም ብትሆን ማዳን የሙያ ግዴታችን ነዉ ለማለት ፈልጎ መሰለኝ። ይህ ክስተት በዘር ለተለከፉት ለቪኦኤ ሙያተኞችና ሌሎችም ትምህርት ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ።
የጋዜጠኝነት ሙያ የጠሉትን የሚቀጡበት የሚወዱትን የሚክቡበት ሳይሆን እንደ ሬጋን ሀኪሞች ስራዉን በፕሮፌሺናል ኤቲክስ (professional ethics) የሚወጡበት ሙያ ነዉ። ያ ካልሆነ ዛሬ በትችት የተጀመረዉ የህዝብ ቁጣ ነገ ወደ ሌላ ሊሸጋገር ይችላል። እዚህ ላይ የኢሳት ሰዎችም መልኩን ይለዉጥ እንጂ ከስህተት የጸዱ አይደሉም አለሙ ሁሉ በነሱ ቅኝት ብቻ እንዲደነስ ይፈልጋሉ። ኢሳት በኢትዮጵያዉያን ገንዘብ በእግሩ ቁሞ ኢትዮጵያን በእጅጉ ለሚጠሉ ግለሰቦችና ድርጂቶች ክፍት በር ሁኖ ሲያገለግል ቆይቷል እርምት ካልተደረገበት ችግር ዉስጥ እንደሚገባ ከወዲሁ በድፍረት መናገር ያስችላል።
ነገሬን ሳልጨርስ ጋዜጠኛ ደምስ ስለነ ኮለኔል ታደሰና በዛብህ ጴጥሮስ በማንሳትህ ሊያስመሰግንህ ይገባል ለመሆኑ ወደዛ ስታቀና አንተዉ እራስህ ይህን ነገር ጠይቀህ ነበር? እነዚህን ጀግኖች አስመልክተህ አንዳንድ ዘገባ ታቀርብልን ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። በዛ ያሉ አርበኞችስ ነገ የነኮለኔል ታደሰ ጽዋ እንደማይደርሳቸዉ ምን ማስተማመኛ አግኝተዋል? በዚህና ተመሳሳይ ጉዳዮች ለእኛ የራቁብንን አቀርበህ ታሳየን ይሆናል የሚል እምነት አለን።
ባጠቃለይ ነገሬን ለመዝጋት ሄኖክም ሆነ አድሀነች ሌሎችም ቪኦኤ ዉስጥ በሀወአት ጋሻ ጃግሬነት የመሸጋችሁ ሁኔታዉ እየገፋ ህዝብን መናቃቸሁ ከጨመረ ከቀጣሪዎቻችሁ ጋር በእኩልነት ሊወያዩ የሚችሉ የተከበሩ ተሰብስበዉ የተቀመጡ ወገኖች ስላሉን እነሱ ማስተካከያ እንዲሰጡበት መጠየቃችን ግድ ይላል።
ይህን ጽሁፍ እንደጨረስኩ ታሪኩ አባ ዳማ (ተናግረዉ የሚያናግሩ…. በኢትዮሚዲያ ላይ) ሚዛን በሚዛን የደምስን ጽሁፍ ከመተቸት ይልቅ ከላይ በጠቀስኩት መልኩ በማሸማቀቅ ወያኔያዊ ዜግነት ለደምስ በመስጠት መልእክቱን ዘግቶታል። ታሪኩ አባ ዳማ ምላሽ መስጠት ካለበት አሀዝ እየጠቀሰ ጦራችን ይህንን ወረዳ ተቆጣጥሯል፤ በወገን ጦር ብቻ ታግዘን ከወያኔ ግማሽ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ጎንደርና ወልቃይትን ተረክበን በቦታዉ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ባንድራን አዉለብለበናል፤ የወያኔን የመሳሪያ ዲፖ ጥሰን ምርጥ መሳሪያዎችን ለወገን ጦር አድለናል ፤ያለ አግባብ በወያኔ የታሰሩ ዜጎችን ከወልቃይት፤ከጎንደር፤ከትግራይ ለቀናል፤ በሱዳን የሰፈረዉን ወራሪ ሀይልም ከወገን ጋር በመሆን በመጣበት መልስናል በህዋአት የተቸረዉ የኢትዮጵያ ግዛትም የጥንት ድምበሩን ይዟል፤ለሻቢያ ሰራዊት ዳግም አንታለልመ ተመለስ ብለናል የሚለዉ እዉነት ያዘለ መልእክት እንጂ አስመራ ሄደዉ የሞቱብንን ወገኖች በደምስ በኩል መነገሩ፤ ለጦሩ እየተባለ የሚላከዉ ገንዘብ ለኮለኔል ፍጹም ልዩ ገቢ መሆኑ መገለጹ ሊያሳስብህ አይገባም እላለሁ። ካንተ ከፖለቲካ እምነት ዉጭ መሄዱም ወያኔ የሚያደርገዉ ስላልመሰለኝ ለወያኔነቱ ማረጋገጫም ጊዜ ልንሰጠዉ ይገባል ወይም በመረጃ ብታረጋግጥልን ሚዛን የሚደፋ ይሆናል። ከዚህ በፊት ብዙ አገር ወዳዶችን አስደንብረን ለአንድነቱ ሊጠቅሙ የሚችሉትን ወደ ወያኔ ጎራ ከተናቸዋል። ይህ ወይ ከእኔ ወይ ከእኔ በተጻራሪ ወይም ደግሞ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነዉ የሚለዉ አካሄድ ኢትዮጵያን ከስልሳዎቹ ጀምሮ ሲያጠፋ እንጂ ሲያለማ ስላላየን ቆም ብለን እናስብ እላለሁ። በእርግጥ ኢትዮጵያዊ ከሆንክ ደምስ ወንድምህ እንጂ ባላጋራህ ሊሆን አይችልም ቢያንሰ ከሻቢያ በተሻለ ልታቀርበዉ ይገባ ነበር።
እንደ እዉነቱ ከሆነ እኛም እንደ እናንተ ከኤርትራዉያን ጋር ነዉ የምንኖረዉ በየቦታዉ የምንገናኘዉ ኤርትራዉያን ኢትዮጵያን አስገድዶ አሰብን ከመጠቀም ዉጭ ለኢትዮጵያ ቀና የሚያስቡ አልገጠሙንም። በኢትዮጵያ በኩል ነብሳቸዉን አድነዉ አሜሪካ እና አዉሮፓ ሲደርሱ ሲነገራቸዉ የኖረዉን ከማንጸባረቅ በስተቀር በምድር ላይ ያለዉን አዉነታ ሲቀበሉም አላየንም። ፍቅር እና ክብር ከሁለቱም አቅጣጫ ካልሆነ ሌላዉን ተዋራጂ ያደርገዋል። ስለዚህ እባካችሁ ኢትዮጵያ ነጻ የምተወጣዉ በሻቢያ መልካም ፍቃድ ነዉ የሚለዉን የተንበርካኪነት ሀሳብ ይዛችሁብን አትቅረቡ። ኢትዮጵያ 100 ሚሊዮን ህዝብ ያላት የጀግና አገር ነች ዱሩና ደኑን ህዝብችንን አድርገን ትግሉ ይቀጥል እንደዉነቱ ከሆነ በዛ በኩል የምታጠፉት ገንዘብ እና ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ዉሎ ቢሆን ዛሬ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትገነባ ነበር። አንዴ ከዘር ድርጅት ጋር መክነፍ አንዴ ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ የኢትዮጵያን ህዝብ በእሳት ሲያጋዩ ሲያርዱ ከነበሩ ጋር ማበዱ ዉጤቱ እንዳያችሁት ስለሆነ በተረጋጋ መንፈስ ኢትዮጵያዊ መፍትሄ ቢፈለግ መልካም ነዉ እላለሁ። እዚህ ላይ በአጽንኦት መናገር የሚቻለዉ የተሰራዉ ጥሩዉም ሆነ መጥፎዉ ተመዝግቦ ተቀምጧል ዳግም ስህተት ላለመስራት መጠንቀቅ ተገቢ ነዉ እላለሁ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ሰመረ አለሙ