የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ሊቀመንበር ኮ/ል ታደሰ ሙሉነህ መሰወር
(ከይታያል የሩቅሰው)
መነሻዬ ሰመረ ዓለሙ የተባሉ ሰው ካቀረቡት ጽሁፍ መካከል አንዱን በማንበቤ ስለተጠቃሹ ከማውቀው እውነት ጥቂት ቆንጥሪ በሚከተሉት አርእዕስቶች በመክፈል፡ የነጠረውን ሀቅ እያነሳሁ አንድ ሁለት ለማለት ነው። ስለዚህ
1/ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ፡ ምን ሰርቶ ነበር?
2/የመሰወሩ ምክናያቶችስ ምንና እነማን ናቸው?
3/እኛስ ስለ እሱ ምን ብለናል?
4/ወደፊትስ ምን ማለት አለብን?
የሚሉ ሃሳብና ጥያቄዎችን እያነሳሁ ባጭሩ ለመዳስ ልሞክር።
ኮሎኔል ታደሰ ምን ሰርቶ ነበር
ገና በለጋ እድሜው ዝነኛውን የኢትዮጵያ አየር ሃይል የተቀላቀለው ታደሰ ሙሉነህ በኮሌጁ የሚሰጠውን ትምህርት አጠናቅቆ በምክትል መቶ አለቅነት ማህረግ እንደተመረቀ ነበር በሲያ ድባሪ የሚመራው የሶማሌ ተስፋፊ ጦር ኢትዮጵያን የወረረው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው፡ ወቅቱ የሃይለስላሴ መንግስት ወድቆ ደርግ ስልጣን የያዘበት ስለነበር ሀገራችን ለመከላከል የምታደርገውን እንቅስቃሴ የሚደግፍላት ባልነበረበት ሁኔታ ላይ ስትሆን፡ ባንጻሩ ሶማልያ የረጅም ጊዜ የወረራ ዝግጅት ከማድረጓም በላይ ሶቭየት ህብረትና ሳውድ አራቢያ እስካፍንጫዋ ያስታጠቀቻት በመሆኑ በሁሉም ዘርፍ የእኛና የጠላት ሐይል አሰላልፍ የተራራቀ ነበር።
ደርግ በአንድ በኩል ከምዕራባውያን መንግስታት መሳሪያ ለማግኘት፣ በሌላ በኩል ወታደር መልምሎ በማሰልጠን ለውጊያ ዝግጁ ለማድረግ በሚሯሯጥበት ወቅት የሶማሌ ታንክና ልዩ ልዩ ከባድ መሳሪያዎችን የጫኑ በሺ የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች ባይድዋ መድረሳቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ይደርሰዋል። ይህ ሃይል ወንዙን ከተሻገረ ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ከመግባት የሚያግደው ነገር እንደማይኖር ሰለሚገመት ምንም እነኳን በተጠናከረ የአየር መቃወሚያና እጅግ ዘመናዊ ተዋጊ አውሮፕላኖች የሚጠበቅ ቢሆንም የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ ያ እንደጉንዳን የሚርመሰመስ ታንክና ከባድ መሳሪያ የጫነ ወታደራዊ ኮንቮይ ሳይሻገር ድልድዩ መፍረስና ተመልሶ እስኪሰራ ጥቂትም ቢሆን የዝግጅት ጊዜ መገኘት እንዳለበት በባለስልጣናቱ ስለታመነ ለአየር ሃይላችን የውጊያ ትህዛዝ በመሰጠቱ ለግዳጁ ለም/ መቶ አለቃ ታደሰ ሙሉነህና ለበዛብህ ጴጥሮስ ወደ ቦታው ይበራሉ። በተጠንቀቅ ይጠባበቅ የነበረው የሶማሌ ወራሪም ገና በርቀት አየር መቃዎሚያውን ቢያስወነጭፍም 2ቱ ጀግኖችና እውነተኛ የ ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በድፍረት ገስግሰው ተፈላጊውን ኢላማ መትተው ድልድዩን በማፍረስ ፊታቸውን ወደሃገራቸው ሲያዞሩ የታደሰ ሙሉነህ ተዋጊ አውሮፕላን በሶማሌ አየር መቃወሚያ በመመታቱ መንደድ ሲጀምር ወጣቱ ፓይለት በፓራሹት በመውረድ፣ በጉዞው ላይም ብዙ አስደናቂ ጀብዱዎችን እያከናወነ ኦጋዴን የሚገኝውን የወገን ጦር ተቀላቀለ። ታደሰ ሙሉነህ ለከፈለው ከባድ መስዋዕትነትና ለፈጸመው ጀብዱ የኢትዮጵያ ጀግና መዳሊያ የተሸለመ ከመሆኑም በላይ ከም/ መቶ አለቅነት አንድ ደረጃ በመዝለል የሻበልነት ማህረግ ተሰጠው።
ታደሰ ሙሉነህ ከዚያም በኋላ በርካታ ሃገራዊ ግዳጆችን የተወጣና ብዙ ቁም ነገሮችን ለሃገሩ ያከናወነ፣ በትምህርት ዝግጅቱም የ2ኛ ዲግሪውን በማዕረግ ያጠናቀቀ ፍጹም ሐገር ወዳድ፣ ቅንና እሩህሩህ፣ አርቆ አስተዋይ፣ ስብናን የተጎናጸፈ ግለሰብ ሲሆን ወያኔ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር የጠላትን ፊት ላለማየት ከድሬድዋ አውሮፕላን አስነስተው ኬንያ ከገቡት የአየር ሃይል አብራሪዎቻችን አንዱ ነበር።
ከዚያም የሀገሩ ውድቀት የእግር እሳት የሆነበት ታደሰ ሙሉነህ ኬንያ እየኖረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማካሄድ ሲጀምር ሁኔታዎች ለህይወቱ አድገኛ ሆነው ስላገኛቸው የተሻለ ከለላ ለማግኘት ባደረገው ጥረት የዑጋንዳ ባለስልጣናትን አነጋግሮ ወደዚያው ሄዶ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንዳለ የወያኔና የሻብያ ግንኙነት በመበላሽት ላይ እንደሆነና ሻብያ ወያኔን በጦር ሃይል ለማበርከክ ሚስጥራዊ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ በአንድ የድሮ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ባልደረባና ኤርትራ ከተገነጠለች በኋላ የኤርትራ ባለስልጣን በሆነ ግለሰብ ይነገረውና ኢትዮጵያን ከወያኔ ነጻ የማውጣት እቅዱን በኤርትራ በኩል ቢያደርግ እንደሚሻል ያግባባዋል።
ኮሎኔል ታደሰም የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው፣ ወይንም ጅብን ለመውጋት አህያን መጠጋት እንዲሉ፣ ከስልት አንጻር ከዚህ የተሻለ ቦታ የለም በማለት ጥያቄውን ተቀብሎ ወደኤርትራ በማምራት የሃገሪቱን መሪ በአካል አግኝቶ ሲያነጋግር ሁኔታዎች እስኪመቻቹ ድረስ የኤርትራ ተዋጊ ጀት አብራሪዎችን ሲያሰለጥን እንዲቆይ ትብብር ስለተጠየቀ እሽ ብሎ እያሰለጠነ ለሁለት አመት ያህል ቆየ። ወያኔ ሳያስበው፣ ሻብያ ግን ከ3አመት ባለነሰ ዝግጅት ጦርነቱ በሻብያ ተንኳሽነት ይፈነዳል።
ይህነን ተከትሎ ደግሞ በኬንያም፣ በሱዳንም፣ በሃገር ቤትም፡ ይንቀሳቀሱ የነበሩ፡ የወያኔ ተቃዋሚዎች ኤርትራ ገብተው ከእዚያ እየተንደረደሩ ወያኔን መውጋት ይችሉ ዘንድ ለኤርትራ መንግስት ጠያቄ አቅርበው ስለተፈቀደላቸው ጠቅልለው እንደገቡ ከኦነግና ከኦብነግ በቀር ሌሎቹ ግንባር ፈጥረው በአንድ ድርጅት ጥላ ስር በመሰባሰብ ለውጊያ እንዲዘጋጁ በሻብያ መመሪያ ስለተሰጣቸው፣
1ኛ/ በአቶ ዮሴፍ ሁነኛው ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ህዝቦች ዲሞክራ ግንባር
2ኛ/ በአቶ ተስፋዬ ጌታቸው ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ንቅናቄ
3ኛ/ በአቶ ቱሗት ፖል ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ አንድነት አርበኞች ግንባር
4ኛ/ በአቶ ጁማ ሩፋኤል ይመራ የነበረው የቤንሻንጉል ንቅናቄ በጋራ ባደረጉት የውህደት ጉባኤ ላይ ኮሉኔል ታደሰ ሙሉነህም ተካፋይ እንዲሆን ተደርጎ ስለነበር ተዋህደው አዲሱን ድርጅት የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር የሚል ስያሜ በመስጠት የመጀመሪያ ጉባያቸውን ሲያጠናቅቁ፣
1ኛ/ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ፣ የግንባሩ ሊቀመንበር
2ኛ/ አቶ ቱሗት ፖል፣ የግንባሩ ም/ሊቀመንበረ
3ኛ/ አቶ ጁማ ሩፋኤል፣ የግንባሩ ጽሃፊ
4ኛ/ አቶ ዮሴፍ ሁነኛው፣ የግንባሩ ድርጅት ጉዳይ
5ኛ/ አቶ ተሰፋዬ ጌታቸው፣ የግንባሩ የእርዕዮታለም ጉዳይና
ሌሎች 2 ሰወችን በማከል 7 ያመራር አካላትን መርጠው ነበር።
ኮሎኔል ታደሰ ያካበተውን የጠለቀ እውቀትና ሰፊ የስራ ልምድ ሳይሰስት ተግባር ላይ ስላዋለው አርበኛ ግንባር ባጭር ጊዜ በብዛትም ሆነ በጥራት ጠላቱን ወያኔን ብቻ ሳይሆን አስተናጋጁን ሻብያን ከማስፈራት ደረጃ ላይ ከመድረሱም በላይ በዲፕሎማሲውም ዘርፍ ኮሎነል ታደሰ ወደ አውሮፓና አሜሪካን በመጓዝ ኢትዮጵያውያንንና የውጭ ሀገር መንግስታትን አነጋግሮ በማሳመን ሰፊ ድጋፍን ያስገኘ ሰው ነው።
እ.አ.አ. በ2001 ዓ/ም ኮሎኔል ታደሰ ወደ አሜሪካን ባቀናበት ወቅት ሻብያን በጥርጣሬ አይን የሚያዩ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው በሻብያ ድጋፍ ኢትዮጵያ ነጻ ትወጣለች ብለህ አትድከም፣ ይልቅ ሻብያ ሳይበላህ አሁን እንደወጣህ በእዚሁ ቅርና ሌላ አማራጭ ፈልግ በማለት ቢለምኑት፣ የሰጣቸው መልስ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ “ኢትዮጵያ ለእኔ ብቻ አይደለችም” እያለ ጥሏት ከሸሸ የጎርቤት ሀገር ዜጋ መጥቶ ሊታደጋት ነውን? ወያኔ ውሎ ካደረ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አትኖርም፣ እናም ቢሆን ከጥፋት አድናታለሁ፣ ካልሆነም ጥፋቷን ሳላይ ማንም ያጥፋኝ፣ እኔ ቀድሜያት ልጥፋ። ሞት እንደሁ ፈራንም ደፈርን የማይቀር የተፈጥሮ እዳችን ነው። የሚል እንደነበር ካነጋገሩት ሰዎች መካከል አንዱ በቁጭት አጫውተውኛል።
የኮ/ል ታደሰ ሙሉነህ የመሰወሩ ምክንያት
ነገሩ እንዲህ ነው፣ በኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ፡ የሰከነና በእውቀት ላይ የተመሰረተ አመራር፣ በእነ ቱሗት፣ በእነ ጁማ፣ በእነ ዮሴፍ፣ በእነተ ስፋዬ ትጋትና የዓላማ ጽናት፡ ያልተለየው የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር በአጭር ጊዜ ተጠናክሮ፡ ጥቃት መሰንዘር ከሚያስችለው ደረጃ ላይ እየደረሰ ሲመጣ አመራሩ ብዙ ኩነቶችን ከዳሰሰና ካጠና በኋላ የውጊያ እቅድ ሲነድፍ፡ አንድ መደምደሚያላይ ይደርሳል። እሱም የትግሉ መሰረት የጎረቤት ሀገር ሳይሆን ሃገር ቤት መሆን አለበት። የወደቀው ወድቆና ያለቀው አልቆ፡ ሀገራችን ላይ ነጻ መሬት ሊኖረን ይገባል፣ የሚለው ተወስኖ ጠቅልሎ ለመግባት የ6 ወር ጊዜ ገደብ ተቀምጦለት ዝግጅት ይጀመራል። ይህን ውሳኔ ሻቢያ ይቃወማል። ከዚያም እነ ኮ/ል ታደሰ በሻብያ ሰራዊት ተከብበው አመራሩ እንዲበተን ይደረጋል። ከዚህ በኋላ ኮሎኔል ታደሰ ከአስመራ እንዳይወጣ ሲደረግ ቱሗት ፖልና ጁማ እሩፋኤል ከኤርትራ እንዲወጡ፣ ዮሴፍ ሁነኛው ከተሰነይ ከተማ እንዳይወጣ፣ ሲደረግ ተስፋዬ ጌታቸው ሃሪና በርሀ ውስጥ እንዲታሰር ተወስኖበት በእስር ላይ ባለበት ወቅት በደረሰብት ድብደባና ዘግናኝ እንግልት ህይወቱ አለፈ። የሻዕቢያ እርምጃ በዚህ አላበቃም። ግንባሩን የደቡብ፣ የትግራይ፣ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል ወ.ዘ.ተ. በሚል ከፋፈለው።
ከእነ ታደሰ ሙሉነህ በኋላ ያለው ሻቢያ ተስፋዬ ጌታቸውን ብቻ አይደለም የገደለው። ወደፊት ታሪክ የሚያወጣቸው ለመታገል ወደ ኤርትራ የገቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን እንክት አድርጎ በልቷል።
እኛስ ስለ እሱ ምን ብለናል?
ኮሎኔል ታደሰ ሙሉለነህ ከህዝብ እይታ ከተሰወረ በኋላ እኛ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹስ የት እንዳለ ለማወቅ ወይንም ለማስፈታት ያደረግነው ጥርት ነበረ ወይ? ቢባል በጣም ጥቂት ሰዎች በግል ካደረጉት ሙከራ በቀር እንደህዝብ የቁርጥ ቀን ልጅነቱ ታስቦበት በተደራጀና በተቀናጀ፡ መልኩ የተከናወነ ነገር የለም። ጉዳዩ የኢትዮጵያውያንን ስሜት ሳይቆነጥጥና፡ በግልም ሆነ በቡድን፡ ሳይነሳ ቀርቶ ግን አይደለም። ኮሎሌል ታደሰ ሙሉነህ ከታሰረ ወዲህ በሚደረገው፡ የሃሳብ ልውውጥ፡ ሁሉ ቀድሞውንም ቢሆን ሻብያ ለኢትዮጵያ ነጻነት አስቦ ይደግፈናል ማለት ቂልነት ነው የሚለው ኢትዮጵያዊ በጣም ብዙ እየሆነ ነው። በዚህ ሰው መታሰር ምክናያትም ኤርትራ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ከመደገፍ የተገቱ ኢትዮጵያውያንም ጥቂት ቁጥር ያላቸው አይደሉም። ይህ ጥላቻ አድማሱ እየሰፋና እየከፋ በመሄድ ላይ ስለሆነ በዚያች ሀገር በኩል በሚሞከረው የነጻነት ትግልም ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ የሚናቅ አይሆንም።
የሻብያና የወያኔ ጸባቸው የእውነት ነው፡ የዛሪ መነጋገሬያችን ሻብያ ስለሆነ፡ የወያኔን አመለካክት ላቆየውና፡ በተለይም ሻብያ፡ ወያኔ እንዲወገድ ይፈልጋል፡፡ ችግሩ ግን በሻብያ እምነት፡ ከወያኔ ውድቀት በኋላ የምትመሰረተዋ ኢትዮጵያ በምንም አይነት መንገድ ለኤርትራ ስጋት የማትሆንበትን ሁነኛ ማረጋገጫ መገኘት አለበት፡፡ ወይንም ስጋት በማትሆንበት መልክ መዋቀር መቻል አለባት። ያ እስኪረጋገጥ ግን ሻብያ፡ ከወያኔ የባሰ ጠላት እንዳይመጣበት ሰለሚፈራ እራሱ ወያኔ ባለበት ሁኔታ እንዲቆይ ይፈልጋል።
እራሴን በሻብያ ባለስልጣናት ቦታ አስቀምጨ ሳየው ይህ ስሌታቸው ትክክልም የሚሆንበት እውነት አለው። ምክናያቱም አንድ ሀገር በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሀገር ለመቀጠል አቀሟ የፈቀደላትን ሁሉ በማድረግ የስጋት ምንጯን ማድረቅ አለባት። ለኤርትራ ደግሞ ከአጎራባቾቿ ሀገራት መካከል ስጋቷ ኢትዮጵያ ብቻ ነች። መንስኤውም ሌላ ሌላውን እንተወውና የኢትዮጵያ ታሪካዊም፣ ህጋየም አካሏ የሆነውን የባህር በር ያለህግ አግባብ በወያኔ እንደተቸራት ታውቃለች። ወሎ ይደር እንጅ ኢትዮጵያዊ መንግስት በመጣ ጊዜ ኢትዮጵያ የወደብ የባለቤትነት ይገባኛል ጥያቄን ማንሳቷ የማይቀር መሆኑን ሻቢያ ይገነዘባል። በበኩሌ ያለውን ተጨባጭ እውነታ፣ እስካሁን ሻቢያ እያደረገው ካለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጋር በማዛመድ ሳየው ስለ ኢትዮጵያ ሶስት የፖሊሲ አቅጣጫዎችን የሚከተል ይመስለኛል። እነሱም፣
1ኛ/ ኢትዮጵያን እንደጎርቤት ሀገር ሶማልያ ስርዐት አልበኝነት የሰፈነባት፣ ያለመንግስት የምትኖር ሀገር እንድትሆን በማድረግ ባሻገር፣ ያለከልካይ በፈለገው ጊዜና በሚያስፈለገው አካበቢ በመግባት ጥሪ ሃብቷንና የጥሪት ክምችቷን መዝረፍ።
2ኛ/ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ጠፍታ ቋንቋን መሰረት ባደረጉ በርካታ መንግስታት እንድትከፋፈል በማድረግ አሁን በወያኔ እንደሚፈጸመው ለስሙ በመሪነቱ ቦታ ላይ ኤርትራ ውስጥ የሚኖሩና በብሄር የተደራጁ ተቃዋሚዎች እንዲቀመጡ ተደርጎ ቁልፍ ቦታዎች በሻብያ ካድሬዎች እንዲያዙና ከአስመራ በሚተላለፍ ቀጭን ትእዕዛዝ በእጅ አዙር ቅኝ የምትተዳደር ሀገር እንድትሆን ማድረግ፡፡
3ኛ/ ሁለቱ ካልተሳኩና የአንድነት ሃይሉ ከአየለ፣ በምንም መንገድ ይሁን ተስማምቶ መልካም ጎረቤት በመሆን መኖር የሚሉት ናቸው።
ስለዚህ እቅድ አንድና ሁለት ተሞክረው አለመስራታቸው ሳይረጋገጥ እንደ እነ ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ አይነት በጽኑ ኢትዮጵያዊነት የሃገር ፍቅር የተጠመደ ዜጋ ማበረታታት ለዓላማቸው መሳካት የማይመች ስለሚሆን ይህንን ሰው ገለል እንዲል ማድረጉ በሻቢያ በኩል የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን ከሀገር እንዲወጣ ማድረግ እንጅ በፈቃድ የገባን የሌላ ሀገር ዜጋ፣ ለዚያውም ከአንድ ሃገር ዲፕሎማት፡ የማይተናነስ ህዝባዊ እውቅና ያለውን ሰው ማሰር ተገቢ አልነበረም ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ መናቅና፡ የፖለቲካ ጥበብም የጎደለው ነው ባይ ነኝ።
ሻብያ እንዴት የአስተዳድርና፡ የዲፕሎማሲ ጥበብ የሚባል ነገር አይታየውም? ኮሎኔል ታደሰን እኮ በምርኮ አልያዘውም። ለምኖና ሊያታግለው ቃል ገብቶለት ነው ወደ ሀገሩ ያስገባው። ከገባም በኋላ ብዙ ሰዎቹን በተዎጊ ጀት አብራሪነት ያሰለጠነ ባለውለታው ነው። እንኳን መንግስትን ያህል ተቋም ይቅርና ግለሰብ እንኳን ቃሉን ያከብራል። ይህ ሰው እንኳን ያላጠፋውንና ቢያጠፋና ሺህ ክስ ቢቀርብብትም፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከረሁት፣ ቃል ገብቶ እንዳስገባው ሁሉ በሰላም ከሃገር እንዲወጣ ይደረጋል እንጅ እንዴት ይታሰራል? ወደፊት ለሁለቱ ሃገር ህዝቦች ግንኙነትስ እንዴት አያስብም? ነው ወይንስ ከምር ወደፊት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንዳትኖር ማድረግ እችላለሁ ከሚል መደምደሚያ ላይ ደርሶ ይሆን?
“በፊት የተናገረን ሰው ይጠላው፣” “በፊት የደረሰን ሰብል ወፍ ይበላው፣” እንዲሉ ሆኖ እነኮሎኔል ታደሰ ቀድመው በመገኘታቸው የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ሆነዋል። እኛ ኢትዮጵያውያንም እየከፈሉ ያሉትን ዋጋ በአይናችን እያየን፣ በጆሮአችን እየሰማን ብዙ ማድረግ ስንችል ምንም ነገር ሳንሞክር ዝም ብለን ተቀምጠናል። ዝም ማለታችን አሳዛኝም አሳፋሪም ነገር ነው። ለመሆኑ ለትናንት ጀግኖቻችን፡ ስራ እውቅና ካልሰጠን፡ ለዛሬ ጀግኖቻችን፡ በችግሮቻቸው ካልደረስንና ገድላቸውን በመተረክ አርያነታቸውን አጉልተን ለተተኪው ትውልድ ካላሳየን፣ እንዴት ነው ለወደፈት ሀገርን ከጥፋትና ህዝብን ከውርደት፡ ሊታደግ የሚችል ጀግና የምናፈራው? የምንተካውስ??