ክብር ለአበበ በቂላ !!!! ሻምበል አበበ ቢቂላ (ነሐሴ ፴ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ/ም – ጥቅምት ፲፭ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም)
ክብር ለአበበ በቂላ !!!!
ሻምበል አበበ ቢቂላ (ነሐሴ ፴ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ/ም – ጥቅምት ፲፭ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም)
የሮሙ ጀግና የቶክዮዉ ኮከብ ጀግናዉ አትሌት አበበ ቢቂላ ነሐሴ ፴ ቀን ፲፱፻፳፭ ዓ/ም በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በደብረ ብርሃን አውራጃ፣ ደነባ ልዩ ስሟ ጃቶ ከምትባል ሥፍራ ላይ ከአባቱ አቶ ቢቂላ ደምሴና ከእናቱ ከወይዘሮ ውድነሽ መንበሩ ተወለደ። ወጣቱ አበበ እንደአካባቢው ልምድ በእረኝነትና በትምሕርት ተሰማርቶ በአሥራ ሁለት ዓመቱ የቄስ ትምሕርቱን አጠናቀቀ። በዚህ በጨቅላ ዕድሜው ስመ ጥሩ የገና ተጫዋች እንደነበር ይነገርለታል። በ፲፱፻፵፬ ዓ/ም አዲስ አበባ ሄዶ በክብር ዘበኛ በወታደርነት ይቀጠርና በገና ጨዋታ እና በስፖርት እየዳበረ ቆየ። ወዲያው በ፲፱፻፵፮ ዓ/ም የአራት ልጆቹን እናት ወይዘሪት የውብዳር ወልደጊዮርጊስን አገባ።
በኅዳር ወር ፲፱፻፵፰ ዓ/ም በአሥራ ስድስተኛው የሜልቡርንኦሊምፒክ ላይ የተሳተፈውን የኢትዮጵያን ቡድን ለመቀበል በተደረገው ሰልፍ ላይ ከጀርባቸው ላይ የአገራቸው ስም የተጻፈበትን መለያ ልብሳቸውን ለብሰው አገራቸውን ወክለው የተወዳደሩትን ወጣቶች ባየ ጊዜ ምን ያህል የኩራት ስሜት እንደተሰማውና ያን ጊዜ እሱም እንደነሱ ለመሳተፍ እንደወሰነ ይጠቀሳል። በዚሁ ዘመን አበበ በብሔራዊ የሠራዊቱ እርስ በርስ ውድድር ላይ ተሳተፎ፣ በ፭ ሺህ ሜትር እና በ፲ ሺህ ሜትር ሩጫ የብሔራዊውን ክብረ ወሰን የያዘው የጊዜው የስፖርት ጀግና ዋሚ ቢራቱ እና አበበ በማራቶን ውድድሩ ሲገጥሙ ተመልካቹ ሕዝብ ዋሚ ያሸንፋል ብሎ ነበር የሚጠብቀው። ከጥቂት ኪሎሜትሮች በኋላ አበበ ቢቂላ የተባለ ያልታወቀ ወጣት ቀድሞ ሩጫውን እየመራ እንደሆነ ሕዝቡ በራዲዮ ሰማ። አበበ በቀላሉ ይሄንን ውድድርም አሸነፈ። የዋሚንም የአምስት ሺ እና አሥር ሺ ሜትር ክብረ ወሰን በመስበር እየታወቀ መጣ። በዚህ ሁኔታ ነው አበበ ለ፲፱፻፶፪ ዓ/ም የሮማ ኦሊምፒክ በተወዳዳሪነት የተመረጠውና ካራት ዓመት በፊትም ያንን የአገሩን መለያ ልብስ በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ለብሶ ለመሳተፍ ያለመው ሕልሙን እውን ያደረገው።
በጦር ካምፕ ውስጥ አበበ የሚያደርጋቸውን ልምምዶች እና ውድድሮች በጥሞና ይከታተሉ የነበሩት ስዊድናዊ አሰልጣኝ ኦኒ ኒስካነን የአበበን ችሎታ በመገንዘባቸው ከሌሎቹ አትሌቶች ጋር ተቀላቅሎ ልምምድ እንዲሠራ ያደርጉት እና የሮም ኦሎምፒክ እስኪቃረብ ድረስ በሚል ከሁለት ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ባላቸው ተራራማ ቦታዎች ላይ የመሮጥ እና የሺህ አምስት መቶ ሜትር ተደጋጋሚ የፍጥነት ሩጫ ልምምዶችን እንዲሠሩ ያደርጓቸዋል።
ለኢትዮጵያና ጥቁር አፍሪቃ የመጀመሪያውን የኦሊምፒክ ማራቶን ወርቅን ከዓለም ክብረ ወሰን ጋር ያስገኘ ኢትዮጵያዊ ከመሆኑም ሌላ በሮማ የኦሊምፒክ ውድድር በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፉ፤ በተከታዩ የቶክዮ ኦሊምፒክ የራሱን የዓለም ክብረ ወሰን በማሻሻል ለሁለተኛ ጊዜ የወርቅ ሜዳይ በመሸለሙ ታሪካዊና ዝነኛ ለመሆን አብቅቶታል።ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ ጥቁር አፍሪካዊ አበበ ቢቂላ ነው። ይህም አጋጣሚ ለብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። የአበበ ቢቂላ ዝናም ከአለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተዳረሰ።አበበ ከውድድር በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰ በሁለት ወሩ በክብር ዘበኛ ሠራዊት ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል መንግሥቱ ንዋይ እና በወንድማቸው ገርማሜ ንዋይ ጥንሰሳ የተካሄደው ፲፱፻፶፫ ዓ/ም የታኅሣሥ ግርግር መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲከሽፍ፣ የሠራዊቱ አባል የነበረው አበበም ከሌሎች ወታደሮች ጋር በመጠርጠር ለጥቂት ጊዜ ታስሮ ነበር።ከታኅሣሡ ግርግር በኋላ እስከ ጥቅምት ፲፱፻፶፬ ዓ/ም ድረስ አበበ በ ግሪክ በ ጃፓን እና በኮሲቼ በ ቼኮስሎቫኪያ በማራቶን ተወዳድሮ በሁሉም አንደኛ በመውጣት አሸንፏል። በሚከተሉት ሁለት ዓመታት ግን በማናቸውም የዓለም አቀፍ ማራቶን ውድድር ላይ ሳይሳተፍ ቆይቶ በሚያዝያ ፲፱፻፶፭ በቦስተን ከተማ በተካሄደው ማራቶን ላይ ተሳትፎ አምስተኛ ሆኖ ነው የጨረሰው።
ሐምሌ ፫ ቀን ፲፱፻፶፮ ዓ/ም አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ማጣሪያ ውድድር በአበበ አሸናፊነት፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞማሞ ወልዴ እና ሦስተኛ የወጣው ደምሴ ወልዴ ወደ ቶክዮ እንደሚጓዙ ሲረጋገጥ በመላው ዓለም ኢትዮጵያ አንድ ብቻ ሳይሆን ሦስት ኃይለኛ ተወዳዳሪዎች እንዳላት ተሰማ።ሻምበል አበበ ቢቂላ ፤ “ሮማን የወረረው ብቸኛው ወታደር”፤ በተወለደ በ ፵፩ ዓመቱ፤ የሜክሲኮውን ሩጫ አቋርጦ መንገድ ዳር በወደቀ በስድስት ዓመቱ ጥቅምት ፲፭ ቀን ፲፱፻፷፮ ዓ/ም የሕይወት ትግሉን ጨርሶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ከተወዳደረባቸው አስራ አምስት የማራቶን ውድድሮች አስራ ሁለቱን በአንደኛነት የጨረሰው ኢትዮጵያዊው ጀግና ጉዞውን አከተመ።አበበ አዲስ አበባ በቅዱስ ዮሴፍ ቤተ ክርስቲያን ሲቀበር ዓፄ ኃይለ ሥላሴ በተገኙበት ዘመዶቹ ወዳጆቹ እና አድናቂዎቹ ጋር ከ፸፭ ሺህ በላይ የሚሆን ሕዝብ ተሰብስቦ እየተላቀሰ የመጨረሻ ስንብት አድርጎለታል። ዕለቱም በመላ ኢትዮጵያ የሐዘን ቀን ሆኖ እንዲውል ተደርጓል።
የበለጠ መረጃ :- https://am.wikipedia.org/wiki/%E1%8A%A0%E1%89%A0%E1%89%A0_%E1%89%A2%E1%89%82%E1%88%8B