ስንታየሁ ቸኮል የሁሉም ነው (በዳዊት ሰለሞን)
የአእምሮ ህመምተኛ የሆኑ ወላጅ እናት አሉት፡፡ወጥቶ እስኪገባ በስስት የሚጠብቁት ሁለት ልጆቹን በተመለከተ ቁጥር የሚወርሷት አገር ብዙ የችግር ቋጠሮዎችን እንደተሸከመች ያስተውልና ነገን ስለ ልጆቹ ‹‹ብሩህ ››ለማድረግ ስጋውን፣አእምሮውንና መንፈሱን ያድሳል፡፡በትግሉ ውስጥ የሚያደክሙ ‹‹ምን አገባኝን የሚያስመኙ››ብዙ መሰናክሎች ቢደቀኑበትም ስንታየሁ ለበቃኝ ‹‹ግንባሩን ››አያጥፍም፡፡
በአንድ ወቅት ኢመደበኛ በሆነ ጭውውት መሐል የእነ ናትናኤል መኮንን ጉዳይ ተነስቶ ‹‹እቤቴ ገብቼ ልጆቼን በናፍቆት ስስማቸው ይህንን ዕድል የተነፈጉት የትግል አጋሮቼ የሚያዝኑብኝ ይመስለኝና ልጆቼን መሳም አቆማለሁ››ብሎኝ ነበር፡፡
ስንታየሁ ቸኮል የቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራር ቢሆንም ራሱን በፓርቲ አጥር ውስጥ በመወሰን ሌሎችን የሚያሳንስ አይደለም፡፡ሌሎች ፓርቲዎች ለሚያነሷቸው የትግል ጥሪዎች የተሳትፎ ምላሽ የሚሰጥ ብቻም አይደለም፡፡ ስንታየሁ ፓርቲዎቹ ጽ/ቤት ድረስ በማምራት ‹‹ምን አይነት እገዛ ላበርክት››የሚል ሁሉንም የራሱ በማድረግ የሚቆጥር ጽኑ ነው፡፡
ሰማያዊና መድረክ ጠርተዋቸው በነበሩ ሰልፎች በመገኘት እንደ ፓርቲዎቹ አባላት የማስተባበር ሚና ተጫውቷል፡፡ለእርሱ ከፓርቲዎቹ በላይ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ትርጉም ነበራቸው፡፡
‹‹እነርሱ የተቃወሙት ወይም እንዲሆን የጠየቋቸው ነገሮች የእኔም እምነት በመሆናቸው ወደፊትም የትኛውንም ቡድን እተባበራለሁ››ዘወትር የሚሰጣቸው ምላሾች ነበሩ፡፡
ስንታየሁ ጋዜጠኛ አይደለም ወይም ብሎግ ከፍቶ ሲጦምር አታዩትም፡፡አንባቢ ግን ነው፡፡ያነባቸው የነበሩ የህትመት ውጤቶች ሲዘጉ የስንታየሁ ቁጣ ይገነፍላል፡፡ጋዜጣቸው ወይም መጽሔታቸው የተዘጋባቸውን ጋዜጠኞች ፈልጎ ‹‹ለምን አንባቢዎቻችሁን ጠርታችሁ ተቃውሟችሁን አታሰሙም ››ከማለት ወደኋላ አይልም፡፡
ሰማያዊ ባደረገው ሰላማዊ ሰልፍ የተሳተፈው ስንታየሁ መንግስት በህገ ወጥ መንገድ የዘጋቸውን ጋዜጦች ሳምፕል በመሰብሰብ ብዙም ትኩረት ላላገኙ ጋዜጠኞች ድምጹን አሰምቷል፡፡ስንታየሁ ጋዜጦቹን ሰብስቦ ወደ ሰላማዊ ሰልፉ ሲያመራ ፖሊሶች እንዳይነጥቁት በመስጋት ‹‹ታክሲ ኮንትራት›› መያዝ ግድ ብሎት ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ግን ስንታየሁ ከስራው ተፈናቅሎ ነበር፡፡
ስንታየሁን ፍትህ በተገፋችበት ቦታ ሁሉ ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ሰውን በአስተሳሰቡ መመዘን የሚወደው ሰላማዊው ታጋይ በብሄር ከተደራጁ ፓርቲዎች ጋር አንድነት ይከተል የነበረውን ስልት አጥብቆ ይደግፋል፡፡‹‹እነርሱን በማግለል የትም መድረስ አንችልም››የሚል እምነት ስለነበረው ተቀራርበው እንዲታገሉ ብዙ ታትሯል፡፡
ስንታየሁ ሰላማዊ ተቃውሞን የሰዎችን ትኩረት ሊስብ በሚችል መልኩ እንዲገለጽ ሁልገዜም ‹‹ምክረ ሐሳብ ››ያቀርባል፡፡አንድነት ባደረጋቸው ሰላማዊ ሰልፎች በወህኒ ቤት የተወረወሩ እስረኞችን ለማሰብ ቢጫ ቱታ እንዲለበስ ሀሳብ ያቀረበውና ለተግባራዊነቱም የተጋው እርሱ ነበር፡፡በሰልፉ ወቅትም የታሰሩ የእስልምና ሐይማኖት ተከታዩችን ለማስታወስ እጆቹን በካቴና አስሮ ሻርፕ አድርጎ ነበር፡፡
በድርጊቱ የተበሳጩ ደህንነቶች ስንታየሁን አስገድደው ለመውሰድ ያደረጉት ሙከራ የከሸፈው በሰልፈኞቹና በትግል አጋሮቹ ነበር፡፡ስንታየሁ ኦሮሞው ሲበደል ኦሮሞ፣አማራው ሲፈናቀል አማራ፣ትግሬው ያለ ስሙ ሲነገድበት የትግሬው ህመም የሚሰማው የሁሉ ሰው ነው፡፡
የቼጎቬራ መንፈስ የሚንጠው አዲስ አበባ ተቀምጦ የዳርፉር፣የአፍጋኒስታን፣የኤርትራ፣የጥቁር አሜሪካዊያን መብት ረገጣ እንቅልፍ የሚነሳው የሙጋቤ፣የአልበሽር፣የጋዳፊ፣የፑቲንና የሌሎች አገራት መሪዎች ሐሳብ ውስጥ የሚጥለው ስንታየሁ የሁሉም ነበር፡፡የምንኖርባት አለም የሁላችን እንድትሆን ሸገር የከተመው ዳርፉር ላይ የፈሰሰን ደም ለማፈስ እጁን መዘርጋት አለበት የሚል እምነት አለው፡፡
ሰዎቹ ስንታየሁን አስረውና አስፈርደውበት አይበቃውም በማለት ይግባኝ ጠይቀውበታል፡፡በእኔ እምነት በስንታየሁ ውስጥ የነበረውን የእኔነት ስሜት ሊያስሩት አይችሉም፡፡ይህንን ልናስረው የምንችለው ግን እኛ ነን፡፡የሌሎች ጥቃት ተሰምቶን የቻልነውን ኃላፊነት መወጣት ከቻልን ስንታየሁን ይሰሩት፡፡መንፈሱ ሲያሸንፍ ስጋው ነጻነቱን ይቀዳጃል፡፡ስለዚህ ራሳችንን ለሁሉም ለመስጠት እንነሳ፡፡
