የግንቦት ሰባት የሃሰት ጦርነት

ከኤሊያስ ክፍሌ (ትርጉም በ አንባቢ)

ግንቦት ሰባት በወያኔ ፋሺስት ሁንታ ላይ ወታደራዊ ድል እየተቀናጀሁ ነው በማለት በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ሃገር ወዳዱንና የድርጅቱን ደጋፊዎች ለማጭበርበር እና አምታቶ ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ እንዲሁም ሕዝብ እየተገደለ እየታሰረ ለምን ዝም ይባላል? ምን እየሰራቹ ነው? ያላቸውን የአባላቶች ቁጣ አረጋግቶ ገንዘብ ለመሰብሰብ አሰፍስፎ በወያኔ ላይ ጦርነት አወጅኩ፣ ፊሽካ ነፋሁ፣ በሚል ሰበብ በዲያስፖራው ኪስ ላይ የብዝበዛ ጦርነት ለማካሄድ የተቀናበረ ፕሮፓጋንዳ ነው። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አስፈላጊ የተባሉ መረጃዎች ዝርዝር እንደሚከተለው ይቀርባል።

ላለፉት በርካታ ወራቶች በወልቃይት ጠገዴ ገበሬዎች እና በወያኔ ሚሊሻ መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ በሁመራ ዙሪያ የተኮስ ልውውጦች እና ተደጋጋሚ ግጭቶች እንደተከሰቱ ሲታወቅ አሁን ድረስ አከባቢው በውጥረት ነው። አልፎ አልፎ የተለመዱ የቶክስ ልውውጦች ይደረጋሉ። በወያኔ ሰራዊት የሚደገፉ ሰሊጥ አምራች ነጋዴዎች በሃይል ዘልቀው የአከባቢውን ገበሬዎች ከመሬታቸው በገፏቸው ቁጥር የቶክስ ልውውጦች በአከባቢው ይሰማሉ። ይህም የተለመደ እና አሁንም ያለ ውጥረት ነው። ከተለያዩ የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች የተሰበሰበው መረጃ እንደጠቆመው በዳንሻ እና በሁመራ አከባቢ የሚገኙ ሰፋፊ ለም መሬቶች የአከባቢውን ገበሬዎች በማስገደድ በማፈናቀል እንዲሁም በምእራብ ኢትዮጵያ ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል የተፈጸመው አይነት ተመሳሳይ የመሬት ቅርሚያ በማድረግና በተለያየ ዘዴ መሬቶቹን የሕወሓት ነጋዴዎች ወስደዋል። የወያኔው ስርአት በተጨማሪ በቀሪ ገበሬዎች ላይ ከፍተኛ ግብር በመጫን አከባቢውን እንዲለቁ ያደርጋል። የወልቃይት ጠገዴን ሕዝብ በሃይል ማፈናቀል አከባቢውን በትግሪኛ ተናጋሪዎች በማስወረር ማንኛውም ጉዳዮች ስብሰባን ጨምሮ በትግሪኛ እንዲደረጉ ጫና በመፍጠር ሕዝቡ እንዲያምጽ አድርጎታል። ይህ ጭቆና ያንገፈገፈው የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ወያኔ የዘር ማጽዳት ዘመቻ እንደከፈተበት ስላመነ በትጥቅ ትግል ገጥሞት ይገኛል። ይህንን የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ትግል የግንቦት ሰባት ድርጅት የራሱ ወታደራዊ እርምጃ አድርጎ በመሳል ሻእቢያ በሚሰራው ፕሮፓጋንዳ በጣት የሚቆጠሩ የግንቦት ሰባት ታጋዮች እንዳደረጉት አድርጎ ውዥንብር በመፍጠር በሃሰት የገቢ ማሰባሰቢያ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።

የጦርነት ዜናው በኢሳት አንደተሰራጨ በማግስቱ ወያኔ አስተባብሎ ነበር፣ ሆኖም ወያኔ ሪፖርቱን እንደ ፖለቲካ ሽፋን በመጠቀም ከወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጋር ያለውን ግጭት ለመሸፋፈን ወያኔ ከኤርትራ መንግስት ጋር እንደተጋጨ አድርጎ ለማቅረብ የፖለቲካ ስራ ሰርቶበታል። ግጭት ነበረባቸው በተባሉ ቦታዎች ቤተሰቦቻቸው ካሉ ከበርካታ ኢትዮጵያውያን በቃልመጠይቅ የሰበሰብኩት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሁለት ግለሰቦች ውጪ በርካታዎቹ የሚሉት በአካባቢው ያለው ግጭት በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብና በወያኔ መካከል አንጂ የግንቦት ሰባት ወታደራዊ አንቅስቃሴ አለመሆኑን አረጋግጠዋል። የግንቦት ሰባት ወታደራዊ እንቅስቃሴ በወልቃይት ጠገዴ አከባቢ መኖር አለመኖሩን የጠየኩት አንድ ሌላ የአካባቢው ተወላጅ በጥያቄዬ ከት ብሎ ክሳቀ በኋላ ሀሰት መሆኑን ገልጾልኛል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በአሁን ሰአት ክንዱን አስተባብሮ በመነሳቱ ወያኔ የግንቦት ሰባት-ሻአቢያን ጥቃት ለመመከት በሚል የፖለቲካ ሽፋን ከፍተኛ የሆነ የዘር ማጥፋት ወንጀል ህዝቡ ላይ እንዳይፈጸምበት ፍርሃት እንዳደረበት ግለሰቡ ጨምሮ ገልጿል።

በቅርቡ ተዋሃድን ያለው አርበኞች ግንቦት ሰባት 100 የማይሞሉ ተዋጊዎችን በኤርትራ ውስጥ ይኖሩታል ተብሎ ይገመታል። ማንኛውንም አይነት ወታደራዊ ኦፕሬሽን መፈጸም የማይችሉ እጅግ በበሽታ እየተጠቁ ያሉ እና በውሃ ወለድ በሽታ እና በወባ እየተሰቃዩ መድሃኒት ለማግኘት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ሲገኙ ሻእቢያ የሚንከባከባቸውን የትግራዩን ደምሕት ታጋዮች ፎቶ እና ቪድዮ እያሳየ ሊያጭበረብር ይሞክራል። ሻእቢያ እና ግንቦት ሰባት ዋጋው በሳንቲም የሚገመት የውሃ ማጣሪያ ክኒኖችን እንኳን ለተዋጊዎቹ ለማቅረብ ፈቃደኞች አይደሉም። ግንቦት ሰባት የታጋዮቼ ናቸው ብሎ የሚያቀርባቸው ቪድዮዎች እና ምስሎች በደንብ ሰልጥነው እንክብካቤ የሚደረግላቸውን የዴምሕት (የትግራይ ሕዝብ ዴሞክራቲክ እንቅስቃሴ) ተዋጊዎችን ሲሆኑ እነዚህ የዴምሕት ታጋዮችን ከማንም በተለየ ከሻእቢያ አትኩሮት የሚሰጣቸው መሆናቸው አስመራ ካሉ ምንጮች ለማረጋገጥ ተችሏል።

ግንቦት ሰባት ያላደረገውን አደረኩ ሲል ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ለምሳሌ ያህል በ2009 በወያኔ መንግስት ላይ ያመጹ ወታደራዊ መኮንኖች የሞከሩትን የመፈንቅለ መንግስት ያቀናበርኩት እኔ ነኝ በማለት ግንቦት ሰባት ሊያጭበረብር ፈልጎ ነበር። በወቅቱ ወታደራዊ መኮንኖቹ በሰራዊቱ ውስጥ በወያኔ የተገነባውና የተስፋፋው የዘረኝነት ድርጊት እና የጎሳ አካሄድ አንገብግቧቸው ስርዓቱን ለመናድ ተነስተው እንደነበር በጊዜው አምልጠው የነበሩ የአመጹ ተባባሪዎች ተናግረዋል። አምልጠው ወደ እርትራ የገቡት እንደ ኮሎኔል አለበል አማረ የመሳሰሉት በመፈንቅለ መንግስቱ ተሳታፊ የነበሩት ማንኛውም ወታደራዊ መኮንኖች ከግንቦት ሰባት በሙከራው ውስጥ ምንም ሚና እንዳልነበረው ይመሰክራሉ።

አርበኦች ግንቦት ሰባት እና ፈብራኪው ሻእቢያ የተለያዩ የሃሰት ዜናዎችን በመፍጠር ወታደራዊ ግጭቶች ተደርገው ድሎች እንደተገኙ በመደስኮር ከተለያዩ በዲያስፖራው ዘንድ ካሉ በወያኔ ድርጊቶች ከተማረሩ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ኪስ ገንዘብ ለመመንተፍ እየተራወጡ ሲሆን የግንቦት ሰባት የገቢ ማሰባሰቢያ የስብሰባ ወራቶች ሲደርስ ይህንን የሃሰት ዜና መፈብረክ ግዴታ ስለሆነ እንዲሰራጭ የተደረገ ሲሆን ምን ያህል በተቃዋሚ ሃይሎች ጎራ ውስጥ የሻእቢያ ተጽእኖ እያረፈ እንደሚገኝ በገሃድ እየታየ ነው::

የሚሰበሰበው ገንዘብ ኤርትራ ለሚገኙት የግንቦት ሰባት ተዋጊዎች የሚሄድ ቢሆን ኖሮ የሃሰት ፕሮፓጋንዳውን አይቶ እንዳላየ ማለፍ ይቻል ይሆናል። ግን ጉዳዩ ይህ አይደለም። ገንዘቡ በበርሃ ላሉት ለተዋጊዎቹ አይደርስም። ላለፉት 3 ወራት ብቻ አርብኞች ግንቦት ሰባት ከአውሮፓ እና አውስትራሊያ ከሰበሰበው 200 ሺህ ዶላር በኤርትራ ለሚገኙ ለተባሉት ለታረዙና ለሚሰቃዩ ታጋዮች አንድም ፍሬ መድሃኒት፣ ምግብ እና የተለያዩ አቅርቦቶች መግዣ አልዋለም። ከዳያስፖራ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በመዋጮ የሚገኘው ገንዘብ በአውሮፓ እና አሜሪካ ለሚገኙ የግንቦት ሰባት አመራሮች ደሞዝና የጉዞ መሸፈኛ (በአሜሪካ እና አውሮፓ ከተሞች ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ ማረፊያ) ወጪ እንደሚውል ይታወቃል። በትግል ስም የሚሰበሰበው ገንዘብ ለትግል ሳይሆን ለግንቦት ሰባት መሪዎች ምቾትና ድሎት ላይ ይውላል ማለት ነው። ከነዚህ ወጪዎች የተረፈው ገንዘብ በኤርትራ ለሚገኙ ታጋዮች ለምግብ፣ ለቫይታሚንና ለመድሃኒት መግዣ አንዲውል ቢደረግ ዝም ማለት ይቻል ነበር። ግን ይህ እየተደረገ አይደለም ሲሉ የደርጅቱ የውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።

በሚቀጥለው ጽሁፍ የአርበኞች ግንባርን እና የግንቦት ሰባትን እየተፍረከረከ ያለ ውህደት እና የፖለቲካ አሻጥሮችን እንዳስሳለን።