የአድባራት ሠራተኞች: በሙስና እና በአድልዎ ላይ የተመሠረተው የሀገረ ስብከቱ የዝውውር አሠራር እንዳሳሰባቸው ገለጹ

  • በእገሌ ቦታ በጀትና መደብ በሚል ተገቢ ያልኾነ ጥቅም ይሰጣል፤ ተገቢ የኾነ ጥቅም ይነፈጋል
  • የሒሳብ ሹሞች ያለወቅቱ ዝውውር አጥፊዎችን በመከላከል ተጠያቂነትን እንዳያዳፍን ተሰግቷል
  • በግንኙነቱ መስተጓጎል ጠቅ/ቤተ ክህነቱ ለሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች አቤቱታ ምላሽ አይሰጥም
  • ‹‹አቤቱታችንን የት እና ለማን እንደምናሰማ ግራ ተጋብተናል››/የአጥቢያ ሠራተኞች/

(ኢትዮ-ምኅዳር፤ ሐምሌ ፬ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

A.A Diosces Head Office

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት፣ በበርካታ አድባራት የጽ/ቤት ሠራተኞች ላይ እያካሔደ የሚገኘው ዝውውር ‹‹አንዱን በመጥቀም እና ሌላውን በመጉዳት ላይ ያተኮረ ነው›› ያሉ አገልጋዮች አሠራሩ እና አፈጻጸሙ እንዳሳሰባቸው ገለጹ፡፡

በሀገረ ስብከቱ ገዳማት እና አድባራት የሥራ ዕድገት እና ዝውውር የሚጠይቁ በርካታ ሠራተኞች እንዳሉ የገለጹት አገልጋዮቹ÷ የዝውውር አሠራሩ የሥራ መዋቅርን፣ ዕውቀትን፣ ልምድንና በጀትን ያማከለ ሒደት መኾን ሲገባው በግለሰብ ቦታ እና በጀት ላይ ያነጣጠረ እንደኾነ ይናገራሉ፡፡

የሠራተኞች ጥያቄ በአመዛኙ ‹‹በእገሌ ቦታ በጀት እና መደብ አዛውሩኝ ወይም ለእገሌ የተመደበው ቦታ እና በጀት ይሰጠኝ›› እየተባለ እንደሚቀርብ አገልጋዮቹ ጠቅሰው፣ ይህም ተገቢ ያልኾነ ጥቅም የሚሰጥበትንና ተገቢ የኾነ ጥቅም ደግሞ የሚከለከልበትን፣ ሰብአዊ መብቶች የሚረገጡበትን አሳሳቢ የዝውውር አሠራር እያሰፈነ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ ሲያዘዋውር የሠራተኛው ደመወዝ እና ለቦታው የተመደበው አበል እንዲጠበቅ ቢያዝም ብዙውን ጊዜ ከአድባራቱ ደረጃ እና የመክፈል አቅም አንጻር ተፈጻሚ ባለመኾኑ አገልጋዮቹ ለረጅም ጊዜ በአቤቱታ እንደሚጉላሉ ገልጸዋል፡፡ በሚከፈላቸው ደመወዝ እና አበል፤ በልዩ ልዩ ገቢዎች የሚገኙ ሕጋዊ ጥቅማጥቅሞች እንዲኹም በትራንስፖርት እና መሰል ወጪዎች በአድባራት መካከል ያለው ልዩነት በአግባቡ ባለመመዘኑ የዝውውር አሠራሩ የኑሮ አቅማቸውን እየተፈታተነው እና ሞራላቸውን እየጎዳው መኾኑን አብራርተዋል፡፡

በአድባራት የአገልግሎት እና የአስተዳደር ክፍሎች መካከል በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት፣ ግጭትን ለማስወገድ እና ለማረጋጋት በሚል በሀገረ ስብከቱ ዝውውር እንደሚፈጸም አገልጋዮቹ ጠቁመዋል፡፡ ይኹንና ለአለመግባባቱ በመንሥኤነት የቀረቡ አቤቱታዎች ታይተው ውሳኔ ሳያገኙ ዝውውር እንደሚፈጸም፤ ይህም ለሥራው ከመቆርቆር ሳይኾን በማስረጃ እና በማጣራት የተረጋገጠውን አቤቱታ በማዳፈን አንዱን ለመጥቀምና ሌላውን ለመጉዳት የታሰበ እንደሚያስመስለው፤ ጥቂት በማይባሉ አጋጣሚዎችም የአንድ አካባቢ ተወላጆች እየተለዩ በደል የሚፈጸምበት እንደኾነ አልሸሸጉም፡፡

በዝውውሩ አፈጻጸም ከሒሳብ ሹሞች እና ከቁጥጥሮች አንጻር እየተካሔደ ያለው ዝውውር ከፍተኛ ትኩረት እንደሚያሻው አገልጋዮቹ ይጠቁማሉ፡፡ የዝውውሩ አፈጻጸም በተለይ ሒሳብ ሹሞች ኦዲት ሳይደረጉና አስፈላጊውን ክሊራንስ ለሀገረ ስብከቱ ሳያቀርቡ ያለወቅቱ እንዳይዘዋወሩ በሚያዝያ አጋማሽ ከተላለፈው የአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ ጋር ያልተግባባና የአስተዳደር ጉባኤውም የማያውቀው ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ የበጀት ካሌንደር፣ ከሰኔ ፴ እስከ ሐምሌ መጨረሻ የዓመታዊ ሒሳብ ምርመራ ወቅት ሲኾን ከሐምሌ አንድ ጀምሮ በኹሉም 52 ያህል አድባራት ኦዲተሮች ተመድበዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱም ኾነ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ደረጃ የነጠላ ሒሳብ አያያዙ የተሟሉ የሒሳብ መግለጫዎች ያልተዘጋጁበት እና ለውስጥ ምርመራ የማያመች በመኾኑ የሒሳብ ምርመራ ለማካሔድ እና አስተያየት ለመስጠት የማያስችል(Disclaimer) እንደኾነ በሪፖርቶች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

‹‹የነጠላ የሒሳብ ምዘገባ መርሕ እየተከተልን የሒሳብ ሥርዐቱ ግለሰብ እና ሰነድ ነጻ ኾነው እንዲሔዱ የሚያደርግ ሥርዐት አለው ወይ?›› በማለት አገልጋዮቹ ይጠይቃሉ፡፡ በአሠራሩ፣ ገቢው ለምን እንደገባ ወጪው ለምን እንደወጣ የሚያውቀው የሠራው ሰው በመኾኑ ሥርዐቱ ግለሰብን መሠረት ያደረገ እንደኾነና በምርመራ ወቅት እንደ ኹለትዮሽ የሒሳብ ምዘገባ መርሕ፣ ሰነድ ብቻ ስለ ገቢ እና ወጪ በበቂ ሊያስረዳ የማይችልበት ኹኔታ እንዳለ ያትታሉ፡፡ ከዚኽ አንጻር በአኹኑ ወቅት የአድባራት ሒሳብ ሹሞች ዝውውር ትዕግሥት ሊደረግበት ሲገባ በብዛት መፈጸሙ፣ ማስረጃን በማጥፋት እና ተጠያቂነትን በማዳፈን አጥፊዎችን ለመከላከል እና ንጹሐንን ለመጉዳት የታሰበበት ያስመስለዋል፡፡

በተለይ ሀገረ ስብከቱ በመደባቸው ልኡካን በአለቆች ላይ የቀረቡ ጥፋቶች በማስረጃ እና በማጣራት በተረጋገጠባቸው አንዳንድ አድባራት (እንደ ብሔረ ጽጌ ቅድስት ማርያም) አቤቱታ አቅራቢ ሒሳብ ሹሞች በዝውውር እንዲነሡ መደረጉ የዝውውሩ አፈጻጸም፣ ‹‹ከአገልግሎቱ ይልቅ ጥቅምንና ግለሰቦችን መሠረት ያደረገና ተጠያቂነትን የሚያዳፍን መኾኑን የሚያረጋግጥ ነው፤›› ይላሉ፡፡

በአጠቃላይ ሕገ ወጥ ጥቅሞችን በማስቀረት ሠራተኛው የሥራ ዋስትናው ተጠብቆ እና ተረጋግቶ ይሠራ ዘንድ ከአስገዳጅ ኹኔታዎች ውጭ ዝውውር እንዳይፈጸም በሀገረ ስብከቱ የአስተዳደር ጉባኤ በተደጋጋሚ የተላለፉ ውሳኔዎች መጣሳቸውን አገልጋዮቹ ይናገራሉ፡፡ ከዝውውር እና አዲስ ቅጥር ይልቅ ሀገረ ስብከቱ በየአድባራቱ እና በየገዳማቱ ያሉትን የአስተዳደር ሥራዎች በመገምገም እና እንዲሻሻል ድጋፍ እየሰጠ በዋናነት የልማት ፕሮጀክቶችን እየነደፈ በማልማት ላይ እንደሚያተኩር የወቅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በሥራቸው መጀመሪያ የሰጡትን ቃላቸውንም ያጠፉበት ነው  ብለዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ቀጥተኛ ትእዛዝ መሾማቸውን ተከትሎ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጋር ያለው ግንኙነት መስተጓጎሉን ያወሱት አገልጋዮቹ፣ በአኹኑ ወቅት አቤቱታቸውን የት እና ለማን ማሰማት እንዳለባቸው ግራ መጋባታቸውን በምሬት ተናግረዋል፡፡

በፓትርያርኩ የተመደቡት÷ ‹‹ሙስና እንዲወገድ፣ ፍትሕ ርትዕ እንዲሰፍን፣ መልካም አስተዳደር እንዲነግሥ›› እንደኾነ ቀደም ሲል ለኢትዮ-ምኅዳር  የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ለሌላ ሰው ዕድገት ለማስገኘት ሲባል የደመወዝ ቅናሽ እየተደረገባቸው ወደ ሩቅ ቦታዎች ጭምር የተዘዋወሩ እንዳሉ ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ ዝውውር መደበኛ አሠራር እንደኾነና እርሳቸውም ከ15 ጊዜ በላይ ተዘዋውረው መሥራታቸውን ያወሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹አጥፊ ሲገኝ እንደ ርምጃ የሚወሰደው ማዘዋወር ነው፤ ሰውዬውም ስለማያርመው ከፍተኛ የሰው ኃይል ዝውውር በሀገረ ስብከቱ ይካሔዳል፤በዚኽ የተነሣ ሠራተኛውም የተረጋጋ አይደለም፤ በመኾኑም አስፈላጊነቱ ካልታመነበት በቀር ዝውውርን በከፍተኛ ደረጃ ለማቆም ወስነናል፡፡ ዝውውሩ ታምኖበት ሲፈጸመም የሚነሣው፣ የሚዘዋወረው ሠራተኛው እንጂ ብሔሩ አይደለም፡፡›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡