በደ/ብሥራት ቅ/ገብርኤል በአለቃው ላይ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አይሏል፤ ‹‹ጸሎተ ምሕላ ይዘናል፤ ሕዝብ የሚወደው ኦርቶዶክሳዊ አባት እስክናገኝ ተቃውሟችን ተጠናክሮ ይቀጥላል››/ምእመናን/

  • ትላንት እሑድ ከጸሎተ ቅዳሴው ፍጻሜ በኋላ ለኹለተኛ ጊዜ ደብሩ፣ በአለቃው ‹‹የመንግሥት ያለኽ›› ጩኸት እና በምእመናን ‹‹ኃይል የእግዚአብሔር ነው፤ አንፈራም፤ አንሰጋም›› መዝሙር እና ተቃውሞ ውሏል

*           *           *

Melake Birhan ZeMenfes

፸ዎቹ መጨረሻ የሚገመተው ዕድሜአቸው ሊያስከብራቸው ሲገባ የመንፈሳዊነት ምልክት ከማይታይበት ዕርግናቸውና ኦርቶዶክሳዊ ወገናዊነት ከሌለው የቀማኛና የእብሪት አስተዳደራቸው የተነሣ ከሳምንት ሳምንት የፖሊስና የደኅንነት ያለኽ በሚለው ጩኸታቸው እየቀለሉ የሚገኙት አለቃው መልአከ ብርሃን ዘመንፈስ ቅዱስ

  • የቤተ ክርስቲያንን ነገር አደራ ብለው መባረኪያ መስቀላቸውን የሰጡ እንደ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ እና ብፁዕ አቡነ መልከ ጸዴቅ ያሉ ደጋግ አባቶችን ያየ ምእመን በምን አእምሮው ይቀበላቸው? በፍቅር የኖረ፣ ክርስትናውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሕዝብ ነው፤ አኹን የመጣበት አስተዳዳሪ ግን የመንፈሳዊነት ምልክት የሌላቸው እብሪተኛ ናቸው፤ ካህናትን ይበትናሉ፤ ምእመናንን ያሳድዳሉ፤ ሰበካ ጉባኤን ያፈርሳሉ፤ ቤተ ክርስቲያንን ይዘርፋሉ፤ እናንተን ልክ ካላስገባኹ እኔ ትግራይ አልተወለድኹም እያሉ ጎጠኝነትን ያስፋፋሉ፤ ቤተ ክርስቲያንን እያጠፉ ስለኾነ ኦርቶዶክሳዊነታቸውንም እንጠራጠራለን፤

Bisrate Gabriel Church00

  • እየተመደቡ የሚላኩ ሓላፊዎች ኦርቶዶክሳውያን ናቸው ወይ የሚል ጥያቄ አለን፤ በማንፈልገው አለቃ አንተዳደርም፤ ሕዝብ የሚወደው አለቃ ነው መሾም ያለበት፤ የሚገባው ክፍል መንፈሳዊ አባት እስኪመድብና መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ ከጸሎት ጋር ተቃውሞው በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል፤ ሰላምን የምንሻ የሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች ነን፤ የሀገረ ስብከቱ ነገር አታካች ኾኖብናል፤ መፍትሔ ካልተሰጠን የአካባቢው ሰላም እየታወከ፣ በየሰንበቱ ቅዳሴው በፖሊስ እየተጠበቀ መቀጠል ስሌለበት ሕዝቡ ተወያይቶ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጀውን ይወስናል፤ ተወልደን ያደግንበት፣ አግብተን ልጅ ያሳደግንበት ቤተ ክርስቲያን ነው፤ እነርሱ ልክ እንደ መሥሪያ ቤት በፔይሮል ፈርመው ደመወዝ የሚወስዱበት ቢሮ አድርገው ቢያዩትም ለእኛ በሐዘንና በደስታ ልመናችንንና ምስጋናችንን የምናቀርብበት የሥርዐተ አምልኮ ቦታ ነው፤ ለማንም የምንተወው ጉዳይ አይደለም፡፡