የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በአሜሪካ (ESFNA) እንኳን ደስ አላችሁ!
ካለፉት 32 ዓመታት አንስቶ የተለያዩ እንቅፋቶችንና ችግሮችን በማለፍ ኢትዮጵያውያንን ካለምንም ልዩነት በማገናኘት እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ (ESFNA) የዘንድሮውን ዝግጅት ሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ እ.አ.አ. ከጁን 28, 2015 እስከ ጁላይ 4 ድረስ ይካሄዳል። ወያኔ በባዕዳን ዕርዳታ ኢትዮጵያን በወረራ ከያዘበት ጊዜ አንስቶ ይህንን ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ፍቃድና ውሳኔ የሚያስተዳድሩትን ተቋም በማዳፉ ስር ለማስገባት ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። አልተሳካም እንጅ።
ወያኔ በዚህ ተቋም ውስጥ ከመስራችነት አንስቶ ይሳተፉ የነበሩ አንዳንድ ሆዳም አባላትን በገንዘብ እንደ ሸቀጥ በመግዛት ከውስጥ ሆነው ለእኩይ አላማው አስፈጻሚ እንዲሆኑለት ለማድረግ ለብዙ ዓመታት ያደረግው ሙከራ ሊሳካለት አልቻለም። እነዚህ በወያኔ የተሰማሩ የውስጥ አርበኞች ተቋሙ በሙሉ ኃይሉ እንዳይቀሳቀስ ቀስፈው በመያዝ ሲፈጽሙ የነበረው ደባና አሻጥር በቆራጥና ጽናት ባላቸው የፌዴሬሽኑ አባላት እልህ አስጨራሽ ትግል ምክንያት ሊከሽፍ ችሏል። ። ወያኔ ፌዴሬሽኑን እንዲያስረክቡት ያሰማራቸው መርዘኞች ከተቋሙ ከተወገዱ በኋላ አንዳንድ የተረፉ የወያኔ ኮሶ የተጣባቸው ርዝራዦች ድርጅቱን መቆጣጠር እንማይችሉ በማወቅ ሌላ የጦር ግንባር በፍርድ አደባባይ በመክፈት ጠበቃ ገዝተው ሙግት በመክፈት በቀላሉ የማይገመት ጉዳት አድርሰዋል። በመጨረሻም እነዚህም እንደበፊተኞቹ በህግ አደባባይ ተንደባለው በመውደቃቸውና ከነሰንኮፋቸው በመነቀላቸው ምክንያት በአሁን ሰዓት ድርጅቱ ጤነኛ አየር በመተንፈስና ተረጋግቶ ስራ በመስራት ላይ ይገኛል። ስለሆነም ወያኔና ተላላኪዎቹ ተነቅለው ከፌዴሬሽኑ ስለወጡ ሁሉም ይህንን ተቋም የሚወድና የሚደግፍ ኢትዮጵያዊ ሊደሰት ይገባዋል።
የወያኔ ተላላኪዎች ከፌዴሬሽኑ ተነቅለው በመውጣታቸው የሽንፈት ጽዋቸውን ቢጎነጩም፤ በገንዘቡ ሁሉንም ነገር ለመግዛት የሚችል የሚመስለው አላሙዱ በረጨላቸው ገንዘብ በመጠቀም “All Ethiopian Sport Federation (AESAONE)” የሚባል ህዝብን ለማምታታትና ለማደናግር ተለጣፊ ፌዴሬሽን ቢያቋቁሙም በተከታታይ ያደረጉት ዝግጅት በከፍተኛ ሁኔታ በተመልካች ማጣት ምች ተመቷል። በተለይም በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን ትልቁን RFK ስታዲዮም በከፍተኛ ገንዘብ አስቀድመው ኮንትራት በመክፈል ተመልካቾችን ከክፍያ ነጻ እንዲገቡ በማድረግና የተለያዩ መስተንግዶዎችን በነፃ በማቅረብ ታዳሚዎችን ለማማለል ጥረት ቢያደርጉም በጣት ከሚቆጠሩ ወያኔዎች በስተቀር ድርሽ ያለ ኢትዮጵያዊ አልነበረም። በመሆኑም ትልቁ እስታዲዮም በሰው ማጣት ዶሮ በጋን ሆኖባቸው ቢቸግራቸው ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎችን በማስገባት በነጻ የራፕና ሌሎችም ዘፋኞችን ብዙ ሽህ ዶላር ከፍለው በማስመጣት የታዳሚዎችን ቁጥር ጨምረው ለማሳየት ጥረት ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለም። በዝግጅታቸው ላይ የተመልካች ቁጥር ለመጨመር በነጻ የአውሮፕላን ትኬት፣ የሆቴል፣ የምግብና የኪስ ገንዘብ እየተሰጣቸው እስቴዲዮሙ ውስጥ እንዲታዩ ከተለያዩ የአሜሪካ እስቴቶች፣ከካናዳና ከአውሮፓ ጭምር የመጡ ቢኖሩም የተሰጣቸውን ገንዘብ ይዘው ወደ ESFNA እየሄዱ በመቀላቀላቸው ምክንያት ወያኔ ተቆጥቶ ESFNA ከሚያደርገው ከተማ በራቀ ከተማ እንዲካሄድ ወስነዋል። በዚህም መሠረት ዘንድሮ ESFNA ሜሪላንድ ስለሚያደርግ የወያኔ AESAONE ደግሞ እጅግ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን ብቻ በሚኖሩበት ኮሎራዶ ውስጥ ይካሄዳል። የዘንድሮውም ካለፉት በባሰ በጣት የሚቆጠሩ ወያኔዎችና ከፍተኛ ገንዘብ የተከፈላቸው ብቻ እንደሚገኙበት ሳይታለም የተፈታ ነው።
የዘንድሮው በሜሪላንድ የሚካሄደው ዝግጅት ደማቅና የተሳካ እንደሚሆን ይገመታል። በዚህም ዝግጅት ላይ ኢትዮጵያዊያን በመነቂስ በውጣት ለፌዴሬሽኑ ያላቸውን ድጋፍ መግለጽ ይገባቸዋል እንላለን።