የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የቤተ ክርስቲያንን የተለያዩ አካላት በወቅታዊ ጉዳዮች እያነጋገረ ነው

  • ማኅበረ ቅዱሳንን በመወንጀል ‹‹ወጣቶቹን ሰብስባችሁ እሰሩልን›› ያሉ አስተዳዳሪዎች የፖሊስ እና የደኅንነት አካላትን በተባባሪነት ወቀሱ
  • ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንን እንደተቋም መወንጀል አትችሉም፤ ፖሊስ የእናንተ ብቻ አይደለም፤ መጀመሪያ ራሳችኹን ፈትሹ›› /ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም/
  • የቅድመ ውይይት ምክክሩና ውይይቱ፣ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የወሳኝነት ድርሻ ያላቸውን ማኅበረ ካህናትን፣ ማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮችን ሊያካትት ይገባል፡፡

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፭ ቁጥር ፰፻፭፤ ቅዳሜ ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)

MoFA Logo
በሙስና መንሰራፋት፣ በመልካም አስተዳደር እና በፍትሕ ዕጦት ሳቢያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ እየተደረገ ካለው የአገልጋዮች እና የምእመናን መነሣሣት ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የቤተ ክርስቲያኒቱን አካላት እያነጋገረ ነው፡፡

ብልሹ የሰው ኃይል አስተዳደር እና የፋይናንስ አሠራር በተከታዩ ዘንድ የሚፈጥረው የተከማቸ ቅሬታ፣ የሃይማኖት ተቋማቱ እምነት እንዲያጡ ምክንያት እየኾነ እንዳለ የሚገልጸው ሚኒስቴሩ፣ በቅርቡም የወሳኝነትና የተሳትፎ ድርሻ ያላቸው የተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር እና የአገልግሎት አካላት የሚሳተፉበት ተከታታይ ውይይት እንደሚያካሒድ ተጠቁሟል፡፡

በሚኒስቴሩ ጥያቄ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተመረጡ አድባራት አስተዳዳሪዎች ከትላንት በስቲያ ከቀትር በኋላ ከሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም እና ከሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሙሉጌታ ውለታው ጋር የውይይቱ ቅድመ ዝግጅት ነው የተባለው ምክክር አድርገዋል፡፡

በዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የተመሩ የኻያ አምስት አድባራት አስተዳዳሪዎች በተካፈሉበት በዚኹ ምክክር፣ ‹‹በማኅበራት ሰላማችንን እያጣን ነው፤ ሰንበቴ ሲከበን እናንተም የላችኹም፤ መንግሥትም የለም፤ አልደገፋችኹንም፤ አልረዳችኹንም›› የሚሉ ክሦች እና አቤቱታዎች ከአንዳንድ አለቆች መቅረቡ ተጠቅሷል፡፡

ካለፈው ሚያዝያ መጨረሻ ጀምሮ የሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች ሙስና እንዲወገድ፣ መልካም አስተዳደርና ፍትሕ እንዲሰፍን፣ እምነትና ሥርዐት እንዲጠበቅ በሰልፎችና በስብሰባዎች የሚያካሒዱት እንቅስቃሴም ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ልብሱን ለውጦ የመጣበት ነው›› ብለዋል – አስተዳዳሪዎቹ፡፡

የሰንበት ት/ቤት አባላቱ የመለያ ልብሳቸውን(ዩኒፎርሞቻቸቸውን) ለብሰው በመውጣት በሚያደርጓቸው ሰልፎች እና ስብሰባዎች መንግሥት የጸጥታ ርምጃ ሳይወስድ በዝምታ መመልከቱን የጠቀሱት አለቆቹ፣ የፖሊስ እና የደኅንነት አካላትን በተባባሪነት በመውቀስ ‹‹ወጣቶቹን ሰብስባችኹ እሰሩልን›› ብለው ሲጠይቁ ተሰምተዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ለግላቸው በማካበት ከገቢያቸው በላይ የሚኖሩ አለቆች በሥነ ምግባርና በፀረ ሙስና ኮሚሽን እየተመረመሩ በሀገሪቱ ሕግ እንዲጠየቁ የሰንበት ት/ቤቶቹ የሚያመለክቱ ሲኾን ዋና ሥራ አስኪያጅ እና አንዳንድ አለቆች በአንፃሩ፣ ‹‹ዶልፊን እና ሃይገር የሚያቆሙ ናቸው፤ ቢዝነስ አድርገውታል›› በማለት ይከሷቸዋል፡፡

the-heavily-corrupt-haile-abrehaበምክክሩ ወቅት ቃሉን መጥኖ እንዲናገር ቢመከርም ‹‹ብሶት ነው የሚያስጮኸኝ›› በማለት በከፍተኛ ድምፅ ሲናገር የነበረው መልአከ መንክራት ኃይሌ ኣብርሃ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ብሎ ብሎ አባላቱን የሰንበት ት/ቤት ዩኒፎርም አስለብሶ መውጣት ጀምሯል፤ እርሱስ ሕንፃውን ከየት አምጥቶ ነው ያቆመው?›› ሲል በሰንበት ት/ቤቶቹ መነሣሣት ማኅበሩን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ ‹‹ወጣቱን ዩኒፎርም እያስለበሱ ይልካሉ›› ያሉ ሌላው አስተዳዳሪ፣ ‹‹እንዴት አድርገን መከላከል እንዳለብን አሠልጥኑን እንጂ ስለሰላም ምን ያደርግልናል፤›› በማለት የሚኒስቴሩን ሓላፊዎች አስደምመዋል ይላሉ የስብሰባው ተሳታፊዎች፡፡

ፖሊስ እና የጸጥታ አካላት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የሚጠብቁ መኾናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም፣ ‹‹ፖሊስ ለእናንተ ብቻ ነው እንዴ?›› ሲሉ አለቆቹን ጠይቀዋቸዋል፤ ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና የተሰጠው ሕጋዊ ማኅበር መኾኑን ጠቅሰው፣ ‹‹ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ይኖራሉ እንጂ ማኅበር እያላችሁ በጅምላ መጥራት የለባችኹም፤ ተቋሙን በጅምላ መፈረጅ ወንጀል ነው፤›› ብለዋቸዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱን ጨምሮ አስተዳዳሪዎቹ በሚመሯቸው አድባራት መልካም አስተዳደርን በማስፈን ለምእመናንና ለሰንበት ት/ቤቶቹ ወጣቶች ምሳሌ መኾን እንደሚገባቸው የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሰው እሰሩ ያላችኹት ሌላ ችግር ነው የሚፈጥረው፤ ጀግና መፍጠር ነው፤ የምናስረው ሰው የለም፤ መጀመሪያ ራሳችኹን ፈትሹ›› በሚል ለአለቆቹ የእሰሩልን ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

State Minister Ato Mulugeta Wuletaw and Minister Dr Shiferaw

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም እና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው

በሚኒስቴሩ ዕቅድ መሠረት ይካሔዳል የተባለውና በቤተ ክርስቲያኒቱ ከሚታየው የአገልጋዮች እና የምእመናን የዕቅበተ እምነት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ጥያቄዎች መነሣሣት ጋር የተገጣጠመው የቅድመ ውይይት ምክክር፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር መዋቅር የወሳኝነት እና የተሳትፎ ድርሻ ያላቸውን ማኅበረ ካህናትን፣ ማኅበረ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤቶች ተወካዮችን ሊያካትት እንደሚገባው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

በሰላም፣ በዘመናዊ አሠራር እና በመልካም አስተዳደር ላይ የሚያተኩረው ዋናው ውይይት በሚቀጥሉት ኹለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር የሚኒስቴሩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ የውይይቱን አቅጣጫ ለማመቻቸት በሚል ከትላንት በስቲያ በሀገረ ስብከቱ ሓላፊዎች ከተመሩት የአድባራት አለቆች ጋር ከተካሔደው የቅድመ ውይይት ምክክር ፍጻሜ በኋላም ‹‹ዘመናዊ አሠራር ዴሞክራሲዊነት እና ብዝኃነት›› በሚል ርእስ በሚኒስቴሩ የተዘጋጀ የመወያያ ጽሑፍ እንደተሰጣቸውም ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡