ሰበር ዜና – በየማነ ዘመንፈስ ቅዱስ የተመሩ አለቆች: ‹‹ወጣቶቹን ሰብስባችኹ እሰሩልን›› ሲሉ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን ጠየቁ፤ ‹‹መጀመሪያ ራሳችኹን ፈትሹ››/ሚኒስቴሩ/
በዋና ሥራ አስኪያጁ ፍላጎት ብቻ የተመረጡትን እና የተመሩትን ኻያ አምስት ያህል አለቆች የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም እና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው አነጋግረዋቸዋል
- ወደ ሚኒስቴሩ ካመሩት 25 አለቆች 20 ያኽሎቹ በዋና ሥራ አስኪያጁ በተደረገባቸው ጫና ያለፍላጎታቸው እንዲሔዱ መገደዳቸውን እየተናገሩ ነው
- በየሰንበት ት/ቤቶቹ የዕቅበተ እምነት፣ የመልካም አስተዳደር እና የፍትሕ መነሣሣት ማኅበረ ቅዱሳንን ወንጅለዋል፤ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ልብሱን ለውጦ የመጣበት ነው›› /ኃይሌ ኣብርሃ/
- ‹‹እንዴት አድርገን መከላከል እንዳለብን አሠልጥኑን እንጂ ስለ ሰላም መወያየት ምን ያደርግልናል?›› /የደብረ መዊዕ ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ/
- ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ሕጋዊ ዕውቅና ያለው ማኅበር ነው፤ ማኅበር እያላችኹ በጅምላ መወንጀል አትችሉም፤ ሰው እሰሩ የምትሉት ጀግና መፍጠር ነው፤ ይልቁንስ መጀመሪያ ራሳችኹን ፈትሹ፤ ለምትመሯቸውም ምሳሌ ኹኑ›› /ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም/
* * *
- በቀጣዮቹ የኹለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሚኒስቴሩ በዘመናዊ አሠራር፣ በመልካም አስተዳደር እና በሰላም ጉዳዮች ላይ የቤተ ክርስቲያንን የተለያዩ አካላት እንደሚያወያይ ተጠቁሟል፤ ለውይይቱ ‹‹ዘመናዊ አሠራር፣ ዴሞክራዊነት እና ብዝኃነት›› የሚል ሰነድ መሰራጨቱ ተጠቁሟል
- ሚኒስቴሩ: በእነ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ ኹኔታዎች የሚመቻችላቸውን አማሳኝ አለቆች እና አድባርዮችን ብቻ ሳይኾን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የወሳኝነት እና የተሳትፎ ድርሻ ያላቸውን ማኅበረ ካህናት፣ ማኅበረ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮችንም ቀርቦ ያነጋግር!!!
ምንጭ፡- አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ ሰኔ ፲፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.
ሙሉ ዘገባውን ይከታተሉ
* * *
- የሃይማኖት ተቋማት የሰው ኃይል አስተዳደር እና የፋይናንስ አሠራር ሥርዐታቸው፤ ለተከታዩ ሕዝብ ያላቸው ግልጸኝነት እና የተጠያቂነት ጉድለት ለኪራይ ሰብሳቢነት ከፍተኛ ተጋላጭነት እየፈጠረ የሚገኝ ጉዳይ ነው፡፡
- ብልሹ አሠራሮች የሚፈጥሩት የተከማቸ ቅሬታ ተቋማቱ በተከታዩ ሕዝብ ዘንድ እምነት እንዲያጡ እና ከተለያዩ ጫፎች በመነሣት እንዲወገዙ ምክንያት ይኾናሉ፡፡
- የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ተከታዮች የሚተቹበት እና አስተያየት የሚሰጡበት መንገድ፤ የሃይማኖቶቹ የልማት ሥራም ይኹን ሌላ ለተከታዩ ቀርቦ ግልጽ ውይይት የሚደረግበት የግልጸኝነት እና የተጠያቂነት አሠራር የሚባል ጉዳይ የተተከለ አይደለም፡፡
/ከሚኒስቴሩ የሥልጠና ሰነዶች/