የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ እና ኤልያስ ተጫነ: በሥልጠና ስም፣ የመዋቅርና የአሠራር መመሪያዎችን ባጠኑ ባለሞያዎችና በየሰንበት ት/ቤቶች ላይ የጥላቻ ቅስቀሳ እያካሔዱ ነው

  • በቅ/ሲኖዶስ ውሳኔና በፓትርያርኩ ቡራኬ ያጠኑትን በማያገባቸው የገቡ ደንቆሮዎች ብለዋቸዋል
  • የሰ/ት/ቤቶችን፣ ከኮብልስቶን ሥራ ይልቅ ከአፋችን ሙዳይ ምጽዋት የሚነጥቁ በሚል ዘልፈዋል
  • በሒሳብ አያያዝ፣ በመልካም አስተዳደርና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ያተኮረ ሥልጠና ተጀምሯል
  • አለቆችን፣ ጸሐፊዎችንና ሒሳብ ሹሞችን ጨምሮ የሀ/ስብከቱና የክፍላተ ከተማ ሓላፊዎች ይሳተፋሉ
  • ያለበቂ ዝግጅት የተጀመረው ሥልጠና ከወሬ ያላለፈ በሚል በተሳታፊዎች ክፉኛ ተተችቷል
  • ለሥልጠናው ድጋፍ ከንግድ ባንክ የተገኘው ብር መቶ ኀምሳ ሺሕ መመዝበሩን ያመለክታል

Lique Maemeran Yemane ZeMenfes Kidusዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፡-

ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት ፳፻፮ ዓ.ም. ውሳኔው ለሀገረ ስብከቱ የመዋቅር የአደረጃጀት እና የአሠራር ጥናት በሰጠው ይኹንታ እና የአፈጻጸም አቅጣጫ መሠረት በተዘጋጀው እና ከ96 በመቶ በላይ የማኅበረ ካህናት፣ የማኅበረ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤቶች ድጋፍ የተረጋገጠበትን የኹለት ቀናት ውይይት ለግማሽ ቀን ብቻ እንደተከታተሉ የመቆጣጠርያ ቅጹ ያስረዳል፡፡ በትላንቱ የሥልጠና መድረክ ግን፣ መመሪያውን በቤተ ክርስቲያን ጥሪ ተደርጎላቸው በበጎ ፈቃድ ያጠኑ ባለሞያዎችን እና ለዕቅበተ እምነት፣ ለመልካም አስተዳደር እና ለፍትሕ መስፈን በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ የሰንበት ት/ቤቶችን ሲዘልፉ ውለዋል)

  • ከዚኽ በፊት እናሠለጥናችኋለን ብለው የመጡ ሰዎች እናውቅላችኋለን ብለው ነበር የመጡት፤ ባለፉት ጊዜያት እኔ ታች ኾኜ ሥልጠና ሲደረግ አንዱ ማስተርስ ዲግሪ አለኝ፤ ከበቂ በላይ ዝግጅት አለኝ ብሎኛል፡፡ ይኼ ስድብ አለበት፤ ምን ማለት መሰላችኹ… እናንተ አትመጥኑኝም፤ ከእናንተ በላይ ነው ዕውቀቴ ማለት ነው፡፡ እንዲኽ ዐይነት ሰዎች ደንቆሮዎች ናቸው፡፡
  • ደብል ኢንትሪ በማለት ግራ ሲያጋቡን ነበር፤ እኛ ደብል ኢንትሪ ስለምንጠቀም ኦዲት አንደረግም ሲሉ ነበር፤ እኛ ባለዲግሪዎች ባለማስትሬቶች ነን ሲሉን አልነበር፤ እኛ በራሳችን ተምረን ልናስደምማቸው ይገባል፤ አኹን ሙሉ ብቁ ሰዎች አግኝተናል፤ እነርሱ ሲያሠለጥኑን አልገባንም ነበር፤ እኔ ራሴ ቁጭ ብዬ የተማርኩባት ቦታ ትታየኛለች፤ አኹን ግን በእኛው እየሠለጠንን ስለኾነ እየገባን ነው፡፡
  • ሒሳብ ሹሞቻችንና የተማሩትን የቤተ ክርስቲያንን ልጆች ከሥራ አፈናቅለው በእነርሱ ቦታ ሊተኩ ነበር፤ እንቀይራለን ብለው ነበር እነርሱ ያሰቡት፤ እኛ ደግሞ በምንም ተኣምር አንቀይራችኹም፤ ይኼ አይደረግም፤ እናንተ ራሳችኹ ናችኹ የምትሠሩት፤ እኛ ግን በመተካት ሳይኾን በማብቃት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ ነው የምናራምደው፤ በቀጣይም ጊዜያት ላይ እንደዚኽ ያሉትን በማያገባቸው እየገቡ እናውቅላችኋለን የሚሉትን አያገባችኁም ልንላቸው ያስፈልጋል፤ እኛ በበቂ መንገድ ዕውቀቱ እና ሞያው ያለን ሰዎች ነን፡፡
  • በአድማ አለቃ አይነሣም፤ ራሳችኹን አስከብሩ፤ ራሳችኹን አስንቃችኹ ከተባረራችኹ ምን እናድርግ፤ ቢሮ የሚያሽጉትን አንታገሥም፤ ጎበዞቹ በራቸውንና ቢሯቸውን ዘግተው እየጠበቁ ነው፤ ተከላክለዋል፤ ሰነፎቹ ደግሞ እያሳሻጉ እየመጡ ምን እንኹን ይሉናል እኛ ፖሊስ የለንም፤ ካህናት ናቸው ያሉን፤ ልትታገሏቸው ይገባል፤ እንደዚኽ ዐይነት ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ሊወገዱ ይገባል፤ አያገባችኹም በሏቸው፤ ለቤተ ክርሰቲያኒቷ እኛ ነን ልንቆምላትና ልንደርስላት የሚገባው፡፡

Lique Tebebit Elias Techaneየበጀት እና ፋይናንስ ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ (የሀገረ ስብከቱን የመዋቅር የአደረጃጀት እና የአሠራር ጥናት ውይይት በወቅቱ ባያጠናቅቁም አሞግሰዋል፤ ‹‹ማንም የፈለገውን ይበል፤ ጊዜው የኛ ነው›› ባሉበት የትላንት ንግግራቸው ደግሞ እጃቸው ክፉኛ እየተንቀጠቀጠ የሚከተለውን ተናግረዋል)፡-

  • እናሠለጥናኋለን ብለው መጡ፤ አሰይጥነውን ሔዱ፤ ሊያሠለጥኑን ሳይኾን ሊያሰየጥኑን ነው የመጡት፤ እኛ ብቻ እናሠልጥናችኹ የሚሉትን እነዚኽን ነው የማንፈልገው፤ እንደዚኽ ዓይነት ሰዎችን ነገም ተነገ ወዲያውም አንፈልግም፤ በምንም ዐይነት ተኣምር! … እኛ የተቸገርነው ባንክ ሔደን መብራት የለም በሚለው ሳይኾን የባንክ ሒሳብ አንፈርምም በሚሉት ነው፤ እኛ የተቸገርነው መቀየር ባለመቻላችን እኛ እንቀይራችኹ የሚሉ መጥተዋል፤ ኹሉን ነገር ወስደው ይህች ሙዳይ ምጽዋት ነው የቀረችን፤ ማንም ምንም የፈለገውን ይበል፤ አኹን ጊዜው የኛው ነው፤ ማኅበር ምን አገባው፡፡