በቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት አባላት በዋና ሥራ አስኪያጅ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ጥያቄ እየታሰሩ ነው

  • በጥያቄአቸው፣ በአስተዳደር ይኹን በልማት ሥራ ምንም ችግር የለም ብለዋል በሌለ ልማት!
  • ምእመናኑንም ‹‹ምንም ዓይነት ድርሻ የሌላቸውና ማንነታቸው የማይታወቅ› ሲሉ ገልጸዋቸዋል
  • የታሰሩት ምእመናን በፖሊስ ጣቢያ ‹‹ማዕተባችኹን በጥሱ መስቀላችኹን አውልቁ›› ተብለዋል
  • የቀድሞው የደብሩ አለቃ ዘካርያስ ሓዲስና ኃይሌ ኣብርሃ ከውዝግቡ ለማትረፍ እያሰሉ ነው

bole bulbula medየቤተ ክርስቲያን ይዞታ ከቤተ ክርስቲያን አቋም ጋር በሚስማማ እና ሀብቷን በሚያስጠብቅ አኳኋን እንዲለማ በመጠየቅ በቅንጅት የተንቀሳቀሱ የቦሌ ቡልቡላ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ደብር ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት አባላት በሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥያቄ እየታሰሩ እና ለእንግልት እየተዳረጉ ነው፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ለቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና በክፍለ ከተማው ለወረዳ 12 ፖሊስ ጣቢያ በጻፉት ደብዳቤ፣ በምእመናኑ እና የሰንበት ት/ቤት አባላቱ ተበይዶ የታሸገው የደብሩ ቢሮዎች በፖሊስ ርምጃ እንዲከፈቱ ምእመናኑም በወንጀል ድርጊት እንዲጠየቁ አመልክተዋል፡፡

ጥያቄአቸውን ተከትሎ ባለፉት ኹለት ቀናት ከኻያ የማያንሱ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት አባላት መታሰራቸው ታውቋል፡፡ ትላንት እና ከትላንት በስቲያ ታስረው ከተለቀቁት ውጭ እስከ አኹን በእስር የሚገኙ ስምንት ምእመናን (አራት ምእመናን እና አራት የሰንበት ት/ቤት አባላት) በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተገልጧል፡፡ ከታሳሪዎቹ መካከል ደብሩን በስብከተ ወንጌል ሲያገልግሉ ቆይተው በጡረታ የተገለሉ የ70 ዓመት ሕመምተኛ አዛውንት ይገኙበታል፡፡ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሲገቡ በአዛዡ ‹‹ማዕተባችኹን በጥሱ፤ መስቀላችኹን አውልቁ›› መባላቸውን ከእስር የተፈቱት ምእመናን ተናግረዋል፡፡

በደብሩ የልማት እና የመካነ መቃብር ይዞታዎች የሚገኙ የንግድ ቦታዎች እና ሱቆች ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ግለሰቦችን በሚጠቅም አኳኋን በከፍተኛ ዋጋ እየተከራዩ ባለበት ኹኔታ የደብሩ ገቢ እና ልማት እየተዳከመ መምጣቱ በምእመናን እየተገለጸ እና ይኸውም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የአስተዳደር ጉባኤ በተሠየመ አጥኚ ቡድን ተረጋግጦ እርምት እንዲደረግ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቢሰጥም፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ በደብሩ የአስተዳደር ይኹን የልማት ሥራዎች ምንም ዐይነት ችግር እንደሌለ ነው በደብዳቤአቸው የጠቀሱት፡፡

በሌላ በኩል ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹ችግር አለ ተብሎ የሚታሰብ ከኾነ ሊፈታ የሚችለው በሀገረ ስብከቱ ነው›› ቢሉም በትላንትናው ዕለት በጽ/ቤታቸው ላነጋገሯቸው 12 የምእመናን ተወካዮች፣ ‹‹አያገባኝም፤ የጻፍኹትም ደብዳቤ የለኝም፤ ሰንበት ተማሪ አድርግ የሚባለውን ከማድረግ በቀር ሌላ ሥልጣን የለውም›› ብለው እንደመለሷቸው ምእመናኑ በከፍተኛ ሐዘን ገልጸዋል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ፣ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የምእመናን እና የሰንበት ት/ቤቶች ሚና yemane zemenfes‹‹አድርጉ የተባሉትን ብቻ ከማድረግ ያለፈ አይደለም፤ ልካቸውን ሊያውቁ ይገባል››በሚለው ንቀት የተመላበት ንግግራቸው ይታወቃሉ፡፡ በዚኽም ደብዳቤአቸው ምእመናኑን ‹‹በቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ምንም ዐይነት የሥልጣን ድርሻ የሌላቸውና ማምነታቸው የማይታወቅ›› ሲሉ ነው የገለጧቸው፡፡ አካሔዱን አላርምም ባለው የደብሩ አስተዳደር ላይ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ለማስጠበቅ እና ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ በማስገዳጃነት የወሰዱትንም ርምጃ፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያንን መብት የሚጋፋ እና በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመ በደል ነው›› ብለውታል፡፡

በዋና ሥራ አስኪያጁ ‹‹ማንነታቸው አይታወቅም›› የሚባሉት ምእመናን ግን የደብሩ አስተዳደር በየምክንያ የሚጠይቀውን ድጋፍ ከመስጠት የማይሰስቱ እና በበጎ አድራጎታቸው የሚታወቁ ናቸው፡፡ ልማት በሚል ለሦስተኛ ወገን እየተላለፈ በአስተዳደሩ የሚሰበስበው በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠር ወርኃዊ ገቢም ሓላፊዎቹንና ግለሰቦችን ከመጥቅም በቀር በተጨባጭ የሌለ ለመኾኑ ‹‹በደብሩ አካውንት ያለው ተቀማጭ ማሳያ ነው፤ ባዶ እጁን የመጣ መኪና ገዝቶ እየወጣ ነው›› ይላሉ – ምእመናኑ፡፡

ምእመናኑን በመረዳት ችግሩን በትክክለኛ ገጽታው ተመልክቶ ከመፍታት ይልቅ ‹‹ልማቱን ለማስቀጠል›› በሚል እንዲታሰሩና በወንጀል ድርጊት እንዲጠየቁ ዋና ሥራ አስኪያጁ የወሰዱት ርምጃ ከአማሳኞች ጋር በተግባር ያልተፋቱ ለመኾናቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ ለዚኽም ነው የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስጠበቅ ከተንቀሳቀሱት ምእመናን ይልቅ በእንቅስቃሴው ጥቅማቸውን ካጡ ተከራዮች ጋር ዳኝነት የተቀመጡትንና በውዝግቡ አጋጣሚ እንዴት እንደሚያትርፉ የሚያሰሉትን አማሳኝ ባለሟሎቻቸውን – የቀድሞው የደብሩ አስተዳዳሪ ዘካርያስ ሐዲስን እና ቀንደኛው ሌባ ኃይሌ ኣብርሃን እየሰሙ የሚገኙት፡፡