ሰንበት ት/ቤቶች ከሥራ አስኪያጁ ጋራ ያደረጉት ውይይት ያለስምምነት ተቋጨ፤ በአማሳኞች እና በተሐድሶ መናፍቃን ላይ በየአጥቢያው የሚወስደው ርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል
- የታሸገው የሰሚት መድኃኔዓለም ሰንበት ት/ቤት ሳያውል ሳያድር መከፈት፤ የታሰሩት አባላት እና ምእመናን መፈታት በተሰላፊዎቹ ሰንበት ት/ቤቶች እና በዋና ሥራ አስኪያጁ መካከል ወሳኝ ልዩነት የፈጠረ ጉዳይ ኾኗል፤ ‹‹በአንድ ደብዳቤ እንዳዘጋኸው በአንድ ደብዳቤ ዛሬውኑ አስከፍት!››
- የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ውስጥ ለውስጥ በቤተ ክርስቲያን እና በአገልግሎቷ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ እንዳለ በማመን በትጋት እና በጽናት እንዲሠራበት በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እና በቅዱስ ሲኖዶስ ይፋዊ መግለጫ በተሰጠበት ኹኔታ፣ በራሳቸው ፍልስፍና የታጠሩት ሥራ አስኪያጁ ቁርጠኛ አቋም ለመያዝ ሲቸገሩ ተስተውለዋል
- የሰንበት ት/ቤት ተሰላፊዎች፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያን እና በሀገረ ስብከቱ አማሳኞች መካከል ስላለው ሥር የሰደደ የጥቅም ግንኙነት ያቀረቧቸውን ማብራሪያዎች ለማስተባበል የሞከሩት የሀገረ ስብከቱ ሒሳብ እና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ከጉባኤተኞች የከረረ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል
- ‹‹የታሰሩትን ልጆች ለመልቀቅ ከፖሊስ የተስፋ ቃል ተሰጥቶናል፤ ችግሩ ያለው ከደብሩ አስተዳዳሪ እና እናንተ ጋራ ነው፤ ወገባቸው ጠንቶ መቆም የማይችል፣ መድኃኒት የሚወስዱ እና የሚያጠቡ እናቶች አብረው ታስረዋል፤ ስለ መድኃኔዓለም ስለ ወላዲተ አምላክ ፍትሕ ስጡን!!››
/የሰሚት መድኃኔዓለም ሰንበት ት/ቤት አባል ሥራ አስኪያጁን የተማፀነበት ቃል/
