እኮ ለምን? (አትክልት አሰፋ)
ይሄ ሁሉ ናዳ ይህ ሁሉ ውርጅብኝ
እንደ ዝናብ ወርዶ የሚቀጠቅጠኝ
ህሊናን አስቶ የሚደበድበኝ፤
ተስፋየን አሟጦ፡
በጭካኔ ረግጦ፤
ሙቀትና ብርዱ
አዘቅቱ ንዳዱ፡
ችግር ቸነፈሩ
ስቃይ ግርግሩ
መከራው በርትቶ የሚያደናግረኝ
ምንድነው ነገሩ? ግራ ግብት አለኝ!?
እኮ ለምን ሆነ?በኔ ጠነከረ፤
ጥላቻና ክፋት እየተካረረ፡
ግድያና እስራት፡
ወከባና እንግልት፡
ምነው እንዲህ ሆነ?
ተደጋገመብኝ፡ በረታ ጨክነ፡፡
ዘመኑን አርዝሞ፡
ክንዱን አፈርጥሞ፡
በላዩ ላይ ቆሞ፤
ይሄ ሁሉ ናዳ፤ ይህ ሁሉ ውርጅብኝ
እንደዝናብ ወርዶ የሚቀጠቅጠኝ
ህሊናን አስቶ የሚደበድበኝ፤
እኮ ለምንድን ነው!?
በኔ ላይ የሆነው?
መካን ወላድ ሆኜ፡ በሃዘን ቆዝሜ
ዘመናት አለፉ በተስፋ ደክሜ፤
ልጆቼን እያየሁ በዘር ተከፋፍለው፡
መተማመን ጠፍቶ በመሃከላቸው፤
ማየት መመልከቱ፤
በቃኝ ምርር አለኝ፡
መታገስ አቃተኝ፡፡
የንጹሃንን ደም በውስጤ ማድረቁ፡
የእናቶችን እንባ መዋጥ መሰልቀጡ፡
ያባቶችን ቁጭት ቆሞ መመልከቱ፡
መሸከም አቃተኝ ከበደኝ እውነቱ፡፡
አንዱ በሌላው ላይ በግዴታ ነግሶ፡
ሲፈልገው ገድሎ፤ ሲፈልገው ከሶ
ሲያሻው አንገላቶ፤ ወይ ካገር አባሮ፡
ወንድም በወንድሙ በሃሰት መስክሮ
አሽቀንጥሮ ጥሎ እስር ቤት ወርውሮ፤
ይኖሩባት ምድር፤ የሚጠሯት ሀገር፡
መሆኑ ሰለቸኝ አረገኝ ድንግርግር፡፡
እምባ ውሃ ሆኖ፡ ወደ ውስጤ ሲፈስ፡
ላብና ንጹህ ደም ምድሬን ሲያረሰርስ፤
ዘመናት ተቆጥረው ዘመኑ ሲመለስ፡
ውርጅብኙ አልቆመም
እስከዛሬ ድረስ፡፡
ይሄ ሁሉ ናዳ፤ ይህ ሁሉ ውርጅብኝ፡
እንደዝናብ ወርዶ የሚቀጠቅጠኝ፡
ህሊናን አስቶ የሚደበድበኝ፤
አሁንስ በዛብኝ፡
መሸከም አቃተኝ፡፡
ንጹህ ደም አፍስሶ
ሜዳ ላይ አርክሶ
አንዳንዱንም ከሶ
ከርቼሌ አበስብሶ
ልጁን ሚስቱን አቅፎ በሰላም አዳሪ
ህሊና የሌለው እውነትን ቀባሪ
በደም የሚቀልድ፤
በእንባ የሚዝናና ደረቅ አይነ ሌባ
የ’ህዝብ ነኝ’ ብሎ ወጥቶ የሚገባ
ከንቱ የሞላባት የከንቱዎች ምድር
ተብሎ መጠራት የባለዶች ሃገር:
ይብቃ ይቁም አሁን
ከመሃል ይቀስቀስ
ክምሩም ይደርመስ
ግፉ ይብቃ ይፍረስ
ቀና ልበል ዛሬ፤ ይድረስ ለኔ ወጉ፡
ጨለማው ተገፎ ይጥራ ጥጋጥጉ፡፡
ሜይ 21/2015