በስልጤ ዞን የምሥራቅ አዘርነት በርበሬ ወረዳ ክርስቲያኖች የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ነው፤ ሓላፊነት በማይሰማቸው ጽንፈኛ ባለሥልጣናት በደል ‹‹ወረዳው ሊቢያ ኾኖብናል፤ ለእኛም አልቅሱልን›› እያሉ ነው
- ክርስቲያን መምህራን እና የመንግሥት ሠራተኞች ተመርረው እና ተሠቃይተው ወረዳውን እንዲለቁ ከሥራ ማባረርን ጨምሮ እስራት፣ ያለበቂ ምክንያት የደመወዝ ቅጣት፣ ያልተገባ የሥራ ምደባ እና ዝውውር እንዲኹም ‹‹እናርዳችኋለን›› በሚል የግድያ ዛቻ ይደረግባቸዋል፤
- የሚያስቀድሱበት እና የሚቀበሩበት ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ ያገኙት በብዙ ውጣ ውረድ ነው፤ የቂልጦ ጎሞሮ ቅድስት ማርያም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ለመሥራት በኮሚቴ የተሰባሰቡ ምእመናን በአንድነት ባሉበት ቤት በምሽት ቤንዚን በማርከፍከፍ እሳት ተለቆባቸዋል፤
የወረዳው ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን፣ የጽንፈኛ እና ዓምባገነን ባለሥልጣናትን በደል ተቋቁመው የሚያሠሯት የቂልጦ ጎሞሮ ቅድስት ማርያም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን
- እየተሠራ ባለው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ላይ ‹‹ጉልላት ለምን አስቀመጣችኹ›› ሦስት ጊዜ የማቃጠል ሙከራ ተደርጓል በዞኑ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሚወቀሱት የወረዳው አስተዳደርና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ጉዳዩን በውይይት ስም እያድበሰበሱ ክርስቲያኖችን በማይመለከታቸው ጉዳይ በደመወዝ ከመቅጣት፣ ከሥራ ከማባረር እና ከመኖርያቸው ከማሳደድ ውጭ መፍትሔ ሰጭ የእርምት ርምጃ እየወሰዱ አይደለም፤
- የሚደርስባቸውን በደል ለዞኑ ያሳወቁ እና በጠንካራ ሠራተኝነታቸው ከዐይን ያውጣችኹ የተባሉ የወረዳው ክርስቲያን መምህራን እና የመንግሥት ሠራተኞች ‹‹አስወቅሳችኹን›› ባሉ የወረዳው አስተዳደር እና የድርጅት ጉዳይ ሓላፊዎች፥ ያለበቂ ምክንያት ከሥራ ተባርረዋል፤ የትምህርት ዝግጅታቸውን እና የሞያ ልምዳቸውን በማይመጥን ቦታ በማዛወር ሞራላዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፤ ‹‹ሀገራችኹ ሥራ ቢኖር እዚኽ አትመጡም ነበር›› በሚል ተዘብቶባቸዋል፤
- በዛሬው ዕለት ለሦስተኛ ጊዜ ከቤቱ ተወስዶ የታሰረው የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና ምስጉኑ የቂልጦ ኹለተኛ ደረጃ መሰናዶ ት/ቤት መምህር የማርያም ወርቅ ተሻገር በፖሊስ ጣቢያ እንግልት እና ድብደባ እየተፈጸመበት እንዳለ ተዘግቧል፡፡ የዋስ መብቱ ተጠብቆ ሊፈታ እንደማይችልም ከወረዳው ኢንስፔክተር መገለጹን የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
* * *
የወረዳው ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን፥ ለወረዳ፣ ለዞን፣ ለክልል እና ለፌዴራል መንግሥት የአስተዳደር፣ የፍትሕ እና የጸጥታ አካላት እንዲኹም ለወረዳው ቤተ ክህነት እና ለሃዲያ እና ስልጤ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤቶች ያሰራጩት የድረሱልን ጥሪ





