ሰበር ዜና – ቅዱስ ሲኖዶስ: በሊቢያ ክርስቲያን በመኾናቸው የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ‹‹የዘመኑ ሰማዕት›› እንዲባሉ ወሰነ፤ ‹‹የ፳፩ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰማዕታት›› በመባል በአንድነት ይታሰባሉ!!!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት ጀምሮ ለአራት ቀናት ያካሔደውን የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ኹለተኛ ዓመታዊ ቀኖናዊ ጉባኤ ሲያጠናቀቅ ባወጣው ባለዐሥራ አንድ ነጥቦች መግለጫው÷ በሊቢያ ራሱን እስላማዊ መንግሥት(ዳኢሽ) እያለ የሚጠራው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ስለ ክርስቲያንነታቸው በግፍ እና በአሠቃቂ አኳኋን የገደላቸውን ኢትዮጵያውያን እና ግብጻውያን ኦርቶዶክሳውያን የሰማዕትነት ሥያሜ በመስጠት በሰማዕትነት ክብር ማክበሩን አስመልክቶ፣ ተከታዮቹን ኹለት ዐበይት ውሳኔዎች መስጠቱን ዛሬ፣ ሚያዝያ ፴ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. አስታውቋል፡-
-
ምንም ጥፋት እና በደል ሳይኖርባቸው ክርስቲያኖች በመኾናቸው ብቻ በሊቢያ ሀገር አይ ኤስ በተባለ የአሸባሪ ቡድን በግፍ እና በሚዘገንን ኹኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች እና የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በሟቾቹ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ተወያይቶ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ያለውን ኹኔታ በጥልቀት ከተረዳ በኋላ ሟቾቹ የዘመኑ ሰማዕት እንዲባሉ ተስማምቶ ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ እና የግብጽ አኃት አብያተ ክርስቲያን ቅዱሳን ሲኖዶሶች በሰማዕትነት ክብር ያከበሯቸው 30 ኢትዮጵያውያን እና 21 ግብጻውያን ኦርቶዶክሳውያን የ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት
2. እንዲኹም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ሚያዝያ ፲፩ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በሊቢያ የተሠዉት 30 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ልጆቻችን እና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የካቲት 15 ቀን 2015 በሊቢያ የተሠዉት 21 የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ክርስቲያኖች በኹለቱም አብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶስ የሰማዕትነት ክብር የተሰጣቸው ስለኾነ፣ የኹለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የ፳፩ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት ተብለው በአንድነት እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡