“ይሄስ እገጭ ይላል” የኢትዮጵያዊያንና የኤርትራዊያን የጋራ የዘፈን ምሽት

“ይሄስ እገጭ ይላል” የኢትዮጵያዊያንና የኤርትራዊያን የጋራ የዘፈን ምሽት

ደረጀ አሻግሬ

ነፍሷን ይማርውና አያቴ የማይመስል ነገር ሲገጥማትና የማይሆን ወሬ ስትሰማ “ይህስ እገጭ ይላል” ትላለች። የሰማችው ነገር ፍሬ ከርስኪ ወይም እጅግ መናኛ ሆኖ ተስምቷት እያለ ያወራላት ሰው እንዴት ደፍሮ ተናገረው፣ አደባባይ አዋለው ማለቷ ነው። ይህንን ለማንሳት የፈለኩበት ምክንያት ሰሞኑን በኢሳትና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢሳት ጥገኛ የሆነው በዲሲ አካባቢ የሚሰራጨው “ነጻነት ለኢትዮጵያ ሬዲዮ” (የጥገኝነቱ መንስዔ የገንዘብ ጉዳይ ነው የሚሉ አሉ) በማስታወቂያ በመነገር ላይ ያለው የኢትዮጵያና የኤርትራ የጋራ የዘፈንና የዳንኪራ መርሃ ግብር ነው።
ሊቢያ ውስጥ የተገደሉብን ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን (ጥቂት ኤርትራውያንም አሉበት ይባላል) ገና አርባቸው ሳይወጣና የሟች ወላጆችና ቤተሰቦች እንባቸው ሳይደርቅ ምን ዓይነት የጭፈራ ዝግጅት ነው በአሁን ሰዓት የሚደረገው? እንዴ እየተስተዋለ? ምን ዓይነት ልበ ደንዳናነትና ጭካኔ ነው ይሄ? አስተዋይነትና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ሊያደርገው ይገባ የነበር እኛ ኢትዮጵያዊያን በቅርቡ በተደጋጋሚ እጅግ ተጎድተና እነሱም ኤርትራዊያን መከራቸው እየጨመረ ነው የመጣው ባለፈው ሳምንት ሜድትራንያን ባሕር ውስጥ ከሰጠሙት ስደተኞች መካከል አብዛኛዎች ኤርትራውያን መሆናቸው ይነገራል። ስለሆነም ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ማድረግ ያለብን አብረን መጸለይና ማልቀስ እንዲሁም ፈጣሪያችንን መማጸን እንጅ አሁን የምንጨፍርበት ጊዜ አይደለም።
በማናቸውም መመዘኛ ቢለካ አሁን የምንገኝበት ወቅት ለሁለታችንም ለኢትዮጵያውያንና ኤርትራዊያን የሐዘንና የዋይታ እንጅ የጭፈራና የዳንኪራ ጊዜ አይደለም። ደግሞ የሚገርመው ዝግጅቱ “ታላቅ የሙዚቃ ዝግጅት የኢትዮጵያና የኤርትራ ሙዚቀኞች በጋራ የሚያዘጋጁት በዓይነቱ ልዩና የመጀመሪያ የሙዚቃ ምሽት” ተብሎ የተሰመ ቢሆንም ቁጥራቸው 9 የሆነ ኢትዮጵያውያን ድምጻዊያንና የመሳሪያ ተጫዋቾች ከነሙሉ የሙዚቃ ባንዳቸው ጋር እንደሚገኙ የስም ዝርዝራቸው ቢገለጽም ዝግጅቱ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ብቻ ቢቀረውም የኤርትራ የኪነጥበብ ባለሞያዎች የስም ዝርዝርና እነማን እንደሚገኙ በቀጣይ ቀናት እናስታውቃለን እየተባለ ቢነገርም እስከ አሁን እነማን እንደሆኑ አልታወቀም። ዝግጅቱ የሚደረግበት ጊዜ ተቃርቧል። ምናልባት የሙዚቀኞችን ዝርዝር የሚያጸድቁት ጋሽ ኢሳያስ አፈወርቂ ይሆኑ እንዴ? እሳቸው ደግሞ ስራ ይበዛባቸዋል። ወይንስ በርካታ ኢትዮጵያውያኖች የምንወደውንና የምናከብረውን የፈረደበትን አቶ ሻምበል በላይነህን የትግሪኛ ዘፈን አስጠንተው ሊያዘፍኑ ይሆን? በጣም የሚገርም ነው።
“የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማዳበር” በማለት የተሰጠው ምክንያት በጣም የሚያስቅ ነው። ኤርትራና ኢትዮጵያ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙት የሌላቸው ማለትም እርስ በርስ ያልተጋቡ፣ ክርስትና ያልተነሳሱ፣ ጓደኝነትና ወዳጅነት የሌላቸው ሆነው ነው አዲስ የማስተዋወቂያ የዳንኪራ በዓል ያስፈለጋቸው? እውነትም ይህስ እገጭ ይላል።