ራቁቱን የቆመ ፌደራሊዝም – አደፍርስ ተሰማ
የወያኔው አለቃ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ሲናገሩ “ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ አንድነት መቀጠል ረድቶናል” ብለዋል። ይህ አባባል ተጨፈኑና ላታላቹህ የማለት ያህል ነው። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የተዋቀረችው በአንድ አናሳ ቡድን በሚመራ የፓለቲካ ፓርቲ ህወሃት ብቻ ነው። ሌላው ሁሉ ከዚህ የቀን ጅብ ቡድን ፍርፋሬ ተጠቃሚ ነው። ከትንሽ የንግድ ቅርንጫፍ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የመንግስትና የህዝብ መስራቤቶች የተሰገሰጉት ወያኔዎች ብቻ ናቸው። ሌላው የሃገሪቱ ዜጋ በየክልልህ ተብሎ እንደ ከብት ከታጎረ ቀናት አልፈዋል። ህብረት፤ ስለአንዲትና የተጠቃለለች ሃገር ማሰብ አይፈቀድም። ሁሉም ነገር ለትግራይ ከትግራይ የሚለው ጠማማ የወያኔ ሃሳብ አንድን የስርዓቱ ተጠቃሚ ሌላውን ለጥቂቶች አገልጋይ በማድረግ ካዋቀረው ዘመን አልፍዋል።
በጣም የሚያሳዝነው ለወያኔው ስርዓት በማደር እንጀራ የሚፈልጉትን የስራ ባልደረቦቻቸውን ሳይቀር እንደ ሁለተኛ ዜጋ መቁጠራቸው ነው። በአንድ መስራቤት ውስጥ ከገዥው መንግስት ወሬ ሲመጣ መጀመሪያ ሹክ የሚባለው የትግራይ ተወላጆች ለሆኑት ነው። ይህ የሚከናወነው ወያኔ በዘረጋው ጥምር የኢኮኖሚና ፓለቲካ የድርጅት መስመሩ ነው። ጠበንጃ አንግተው አብረዋቸው ለተሰለፉት ዘራቸው ከትግራይ ያልሆኑ ሁሉ የሚደርስባቸው ግፍ በቃላት አይገለጥም። መተናፈሻ በሌለው የስለላ አውታሩ ወጥሮ ስለያዛቸው ችግራቸውን ሰሙልኝ ማለት አይችሉም። ሲጠፉ ከተያዙም ያለምንም ፍርድ በሞት ይቀጣሉ።
አቶ መለስ በፌደራሊዝም የቆመ አንድነት የሚሉትም እውነታ ትግራይን የሚያገለግለውን ለህወሃት የቆመውን መርህ ነው። ዛሬ በየዓለማቱ በኢትዮጵያ ስም አምባሳደር እየተባሉ የሚላኩት ለወያኔ አዳሪዎችና ወያኔዎች የወያኔ ጥቅም አስጠባቂዎች ብቻ ናቸው። የአቶ ስዪም መስፍን በቻይና መመደብ ይህኑ የምዝበራ ሃሳብ ጉልህ ያደርገዋል። ወያኔ አሁንም ቢሆን ትግራይን የብቻ ሃገር ለማረግ ሃሳቡን አልሰረዘም። ለዚህም ነው ሁሉም ነገር ወደ ትግራይ በማለት ያለ የሌለ የማሃል ሃገር አንጡራ ሃብትን ሌትና ቀን ወደ መቀሌ የሚያሸገጋግረው። የደቡብ ሱዳን ከሰሜኑ ሱዳን መገንጠልም የበለጠ የወያኔ ህልም ያጎለብተዋል። ይህ ስጋው ተበልቶ በአጥንቱ ብቻ የቆመውን ፌደራሊዝም ነው ለኢትዮጵያ አንድነት ጠቀመ እየተባለ የሚለፈፍልን። በየትም አለም የፓለቲካ ቅመራ ሰው በየጎጥህ ተብሎ አንድ ሃገር ተመስርቶ አያውቅም። አእላፍ ኤርትራውያንን በቀንና በሌሊት እያፈሰ ከማሃል ሃገር ለሻብያ ያቀበለው ወያኔ ስብዕና የሌለው ተልካሻ ቡድን ነው። ለኢትዮጵያ አንድነት ተቆርቁሮ አያውቅም። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ነውና ፍልስፍናው።
ወያኔ ህገ-መንግስት ብሎ ባሰፈረው ረቂቅ ላይ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝን ያከለበት ለራሱ የማምለጫ ብልሃት ነው። ብሄር ብሄረሰቦች የመገንጠል ስልጣን እንዳላቸው ይጠቁማል። ተገንጥሎ ሰላም ያገኘ ሃገር የለም። አሁንና በፊት የኤርትራ መገንጠልን ስትደግፍ የኖረችው ፓኪስታን ራስዋ ከህንድ የተቆረስች ናት። እንኳን ሰላም የሰላምም ለነፋስ ነፍሶባት አያውቅም። በቀድሞው ምስራቅ አውሮፓ በፈረሰቸው ሶቪየት ህብረት አንድ ላይ ይኖሩ የነበሩ ሁሉ ከተሽረፉ በህዋላ የገጠማቸው ሃበሳ ለመዘርዘር ወረቀት አይበቃውም። ከኢትዮጵያ ኮሎኒያሊዝም ነፃ የወጣችው ሃዳሽ ኤርትራም ሰው የማይኖርባት አረመኔ መሪዎች የሚፈላሰፉባት ሆናለች። ታዲያ የመገንጠል ጥቅሙ የቱ ላይ ነው? የሰላሳ አመት የእርስ በርስ ፍጅትስ ትርፉ የቱ ነው? ነገስ እንደዛሬው ከሆነ መሻሻላችን የቱ ላይ ነው?
የወያኔ የጎሳ ፌዴራሊዝም ነፋስ እንዳነሳው የብድር ድቄት የሚበተን እንጂ የተበተነውን ህዝባችንን በአንድ የማሰርና የማስተባበር ባህሪ የለውም። የወያኔው አለቃ የጎሳ ፌደራሊዝም አንድ አረገን እያሉ ለህዝባችን የሚለፉት ዘይቤም ከአመልካች እጣታችን አውራ እጣት ይበልጣል እንደማለት ነው። ከእጣት እጣት አይበልጥም። ሁሉም የየራሳቸው አገልግሎት አላቸው። ሥጋው ተበልቶ አጥንቱ ብቻ የቀረ ፌደራሊዝም ለሃገራችን አይጠቅምም። ወያኔ በዘር ያዋቀረውን የላዕላይና ታህታይ መዋቀር ሁለገብ እስካላደረገ ድረስ እውነተኛ ፌደራሊዝም በሃገራችን ሊስፍን አይችልም። የወያኔው አለቃ ፌደራሊዝም አጣመረን እያሉ በሰበኩበት ወቅት በሳቸው የተጣመመ ፓለቲካ በተሰመረው የጎጥ አጠር የተነሳ በደቡብ የሃገሪቱ ክፍል ሰዎች ተጋደሉ ይለናል የወቅቱ ዜና።
ኃይለስላሴ ደስታ የተባለ ጸሃፊ “ኦ ሰላም በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ” በሚል ርዕስ ማንበቤ ትዝ ይለኛል። በዚሁ መጽሃፍ ላይ ሰለ ደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ አሰራር በጥቁሮች ላይ ያሳደረውን መከራና ግፍ ዘክሮልን ነበር። ይህ ጸሃፊ ዛሬ አንገት አልባ የሆነችውንና በጎሳ የተለጣጠፈችውን የወያኔ መጨፈሪያ ውድ ሃገራችንንን ቢመለከት ምን ይለን ይሆን።
ሰንበተን እንይ…ቀን የሚያመጣው አይታወቅምና!