ሚስ ዌንዲ ሸርማን በቅርቡ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ የስጡት አስተያየት የተሳሳተና ጎጂ ነው ሸንጎ

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ ከብዙ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ፣እንዲሁም ነጻ ከሆኑት የሰብአዊ መብት ድርጅቶች፣ ከፍሪደም ሃውስ፣ከሂውማን ራይትስ ዋች፣ከአምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ከኢንተርናሽናል ሪቨርስና ከሌሎቹ ጋር በማበር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የፖለቲካ ቢሮ ም/ሃላፊ የሆኑት ዊንዲ ሸርማን በቅርቡ ባደረጉት የአዲስ አበባ ኦፊሴላዊ ጉብኝት ወቅት በ16-04-2015 የሰጡት አስተያየት እውነትን የማያንቀባርቅ በመሆኑ ከማዘናችንም በላይ የአሜሪካንንም ሆነ የኢትዮጵያን መሰረታዊ ጥቅም ሊያሰከብር የሚችል እንዳልሆነ መግለጽ ይወዳል፡፡

ካሁን በፊት የአሜሪካ መንግስት በተደጋጋሚ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣እስራት፣ማሳደድ፣የሃይማኖትና የፖለቲካ አፈና፣በግዳጅ መሰወር፣የአካል ጉዳትና ስቃይ ማድረስና ሕዝቡን ለባርነት አሳልፎ መስጠት አሁን በስልጣን ላይ ባለው መንግስት የሚፈጸም እለታዊ ተግባር እንደሆነ አረጋግጧል።ይህንኑም ግፍና በደል ያሜሪካን ባለስልጣናት ራሳቸው በአካል በማየት መንግስት ከዚህ አይነቱ ተግባር እንዲታቀብና ጋዜጠኞችና ጦማርያንም እንዲፈቱ ጠይቀዋል ጨቋኝ ህግጋትም እንዲለወጡ አሳሰበው ነበር።

ይህ አይነቱ ግፍና ወንጀል የሚፈጽም መንግስት ባለበት አገር፣ሚስ ሸርማን “ኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው ዲሞክራሲ በየቀኑም እየጎለበተ ነው፣የሚመጣውም አገር አቀፍ ምርጫ ሁሉን አቀፍ በሚያደርግ መንገድ እየተዘጋጀ ነው”ብለው ማለታቸው ከብዙሃኑ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካ መንግስት በጽሁፍ ካሰፈራቸው መረጃወችና መግለጫወች ጋር የሚቃረን ነው ብለን እናምናለን።

የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች በሕገወጥ መንገድ በገዥው ፓርቲ ቀጥተኛ ጥቃት እንዲፈራርሱ በሚደረግበትና የፖለቲካ ምህዳሩ በተዘጋበት ሁኔታ ፣በየጊዜው በሚደረገው የግብር ይውጣ ምርጫ እድገትና መሻሻል እየታዬ መጥቷል ብሎ መመስከር መሰረተቢስ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ አመለካከት በመናቅና በማኳሰስ ብቻ ሳይገታ አሜሪካም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ውስጥ የሚኖራትን ቋሚ የጥቅምና ጤነኛ ግንኙነት የሚበክል ነው።

የዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው ሁኔታ የሚብስ እንጂ የተሻለ አይደለም።እራሳቸው ሚስ ሸርማን የሚወክሉት ተቋም በ29-01-2015 ዓ.ም.እ.አ.አ.(ከሶስት ወር በፊት)”የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማጥበብ፣ተቃዋሚዎቹን እያሳደደና እያሸበረ፣የሲቪል ማህበረሰቡን በመቆጣጠር፣የነጻ ሚዲያ ዘርፎችን በማፈን ሁሉንም እንዳይንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል”ሲል መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው።ባለስልጣኗ ለኢትዮጵያ መንግስት በይፋ ድጋፋቸውን ሲሰጡ ያላገናዘቡት ነገር ቢኖር የከሰሱትና የሚያወግዙት የወንጀለኛውን መንግስት ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን የራሳቸውንም መንግስትና ተቋም ጭምር መሆኑን ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ሌላ ሆኖ ሳለ፣ሚስ ሸርማን የአንድ ነጠላ ፓርቲ የበላይነት በሰፈነበት ስርዓት፣ሃሳብ መግለጽን፣የመሰብሰብና ሰላማዊ ተቃውሞን ወንጀል አድርጎ የሚቀጣ ጨቋኝ መንግስት ለዴሞክራሲ የቆመ ነው ብሎ እውቅና መስጠታቸው እጅግ ጊጂ ሆኖ አግኝተነዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ነጻ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ በመላው አለም ቁንጮ ከሚባሉት ሀገሮች ውስጥ አንዷ ነች፡ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ደጋፊዎች በእስር ቤት እንደሚሰቃዩ ፣ እንደሚሰደዱና ታፍነው የት እንደደረሱ የማይታወቅበት ሀገር እንደሆነች ብዙ ነጻ አለምአቀፍ ድርጅቶች የመዘገቡት እውነታ ነው። በሺወች የሚቆጠሩ ዜጎችም በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ በየእስር ቤቱ ይሰቃያሉ፡ሌሎችም ይሰደዳሉ፡፡

ላለፉት 23 ዓመታት በጉልበት በስልጣን ላይ የተቀመጠው ነጠላው የጎሳ ድርጅት የምርጫ ቡርዱን በመቆጣጠሩ ሕብረ ብሔርም ሆኑ የአካባቢ ፖለቲካ ድርጅቶች በነጻ እንዳይንቀሳቀሱ አግዷቸዋል ። አስመራጭ ተብየው የመንግስት አካል የሆነው የምርጫ ቦርድ፣ፖሊስና የፍትህ ተቋምም የተቃዋሚ ማፈኛ መሳሪያዎች ሆነዋል።ሆኖም ግን ተቃዋሚው ክፍል በሚችለው መንገድ እነዚህን ግንቦች በሰላማዊ ትግል ለማለፍ ጥረት ከማድረግ አልተቆጠበም።

እንደሚታወቀው “የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር”ኢሕአዴግ የተባለ የጎሳ ስብስብ በመፍጠርና በመቆጣጠር ብዙ መስሎ ቀርቦ በማምታታት ላይ ነው።ይህ በብዙ ስም የሚነግድ ነጠላ ፓርቲ ሌሎቹን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያላካተተ “ምርጫ” ቢያካሂድ የሚወዳደረው ከራሱ ጋር ስለሆነ አሸነፍኩ ብሎ የሚወጣውም እራሱን እንደሆነ መታወቅ አለበት።

እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ የባለስልጣኗ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሰፍኗል ብሎ ተገቢ ያልሆነ ለአምባ ገነን ስርዓት እውቅና መስጠት የአሜሪካንን መንግስት ከትዝብት ውስጥ የሚከት ብቻ ሳይሆን 100 ሚሊዮን የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጎዳና በዝቅተኛ ደረጃ የሚያስቀምጥ ነው፡፤ይህን የተዛባ አቋም የአሁኑ ትውልድ ለሚመጣው ትውልድ በታሪክ መጽሃፉ አስፍሮ ያወርሰዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ የአሜሪካ መንግስት ለአጭርና ውስን ለሆነ “ለጸረ ሽብር አጋርነት”ሲል ከአሸባሪና የሕዝብ ድጋፍ ከሌለው አምባገነን ቡድን ጋር ያለውን ትስስርና የሚሰጠውን ድጋፍ እንዲመረምረውና እንዲያስተካክለው ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ አሸባሪነትን አጥብቆ የሚያወግዝ እንደሆነ እየገለጸ በሀገራችን ውስጥ በየጊዜው ለሚታየው የፖለቲካ አክራሪነት በዋናነት አመች ሁኔታ የሚፈጥረው አግላይ እና ግፈኛ የሆነው የገዥው የህወሀት/ኢህአዴግ ፖሊሲና ተግባር እንደሆነ ሊያሰምርበት ይሻል።

በሀገራችን ውሰጥም ሆነ ባካባቢያችን የሚታየውን አደጋ ለማሰወገድ ሽንጎው በዋናነት ሁሉንም አሳታፊ የሆነ፣ የህዝብ መብትና የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ፖለቲካዊ ስርአትን እውን ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል። ይህንንም እውን ለማድረግ በተደጋጋሚ እንዳሳሰብነው ሁሉንም ባለድርሻወች ያሳተፈ ብሄራዊ መግባባትና እርቅ ሊተገበር ይገባል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ